ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታሪክ፣ አሠራር እና አወቃቀር
አዲስ አበባ ውስጥ አራት ኪሎ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕንጻ በርካታ ታሪካዊ ኹነቶች አስተናግዷል።
ከሰላሳ ባነሱ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ታውጆበታል፤ ዕርቅም ወርዶበታል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የቅንጅቱ አቶ ተመስገን ዘውዴ 'ፊስካል' እና 'ፊዚካል' በሚሉ ቃላት አተካራ ውስጥ የገቡትም በዚሁ ምክር ቤት ነው።
'ታሪካዊ' የተባለውን የሥልጣን ሽግግር በአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መካከል አስተናግዷል።
የፖለቲካ ቡድኖች በሽብርተኝነት ተፈርጀውበታል ነጻም ወጥተውበታል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አጽድቋል እንዲሁም አንስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "አሸባሪዎቹ እኛው እራሳችን ነን" የሚል ንግግር አድርገውበታል።
በአጠቃላይ በግልጽ ለሕዝብ በይፋ እና በዝግ በተካሄዱ ስብሰባዎች ምክር ቤቱ በአገሪቱ እና በሕዝቧ ላይ ጉልህ ውጤት የነበራቸው ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?
የምክር ቤቱ ታሪክ በወፍ በረር
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት/የእንደራሴዎች ፓርላማ ከመጀመሪያው ሕገ መንግሥት ጋር መንታ ነው። ሕገ መንግስቱ በ1923 ዓ.ም. ሲጸድቅ ነው አብሮ የተወለደው።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓርላማ፣ ጥቅምት 24 ቀን 1924 ዓ.ም. ቃለ መሃላ ፈጽሞ ሥራውን ጀመረ።
ሕገ መንግሥት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት እና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የተሰኙ ተቋማትን አቋቁሟል። የሕግ መምሪያ ምክር ቤት 30 አባላት ሲኖሩት፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ደግሞ 60 ነበሩ።
ዶ/ር ሜርሲ ፈቃዱ 'Parliament in Ethiopia' በሚለው መጽሐፋቸው "ይሁን እንጂ፣ የፓርላማውን ምርጫ እና ተግባር በተመለከተ [የ1923ቱ የሕገ መንግሥቱ] ድንጋጌዎች በጣም ገዳቢ በሆኑ መንገዶች ተቀርጸዋል" ይላሉ።
ብዙ ተንታኞች በጊዜው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተማረ እና ስለ የዴሞክራሲ ተቋማት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን በማንሳት ሕገ መንግሥቱ ከጊዜው የቀደመ ነው የሚል መከራከሪያ እንደሚያቀርቡ ዶ/ር ሜርሲ ይጠቅሳሉ።
ሕገ መንግሥቱም ለሕዝቡ ተመሳሳይ አመለካከት እንደነበረው ተመራማሪዋ ያነሳሉ። በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ ንጉሠ ነገሥቱ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላትን ከ"ልዑላን ወይም ሚኒስትሮች፤ ዳኞች ወይም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች" መካከል ይሾማሉ።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የሕዝብ ተመራጭ ናቸው።
ነገር ግን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 "ሕዝቡ ተወካዮቹን መምረጥ የሚችለበት ደረጃ እስከሚደርስ በጊዜያዊነት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በመኳንንቶች እና ሹሞች ይመረጣሉ" ይላል።
ንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ መሆናቸው የምክር ቤቶቹ የሕግ አውጪነት እና የቁጥጥር ሥልጣን ላይ ከፍተኛ ገደብ ጥሎባቸው ነበር።
ንጉሠ ነገሥቱ በሁሉም የመንግሥት ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሠጪነት ሥልጣን ስለነበራቸው የሕግ መምሪያ ምክር ቤት እና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶችን ወደ አማካሪነት ዝቅ አድርጓቸዋል።
ምንም እንኳን ፓርላማው የፓርላማ ቡድኖች ባይኖሩትም፣ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለመመርመር እና ለጉባኤው ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ እንደነበር ዶ/ር ሜርሲ መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።
በ1948 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣወስ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ካስተዋወቃቸው አዳዲስ ነገሮች መካከል የፓርላማ አባላት ያለመከሰስ መብት አንዱ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም አባላቱ ደመወዝተኛ እንዲሆኑ የተደረገው በዚህ በተሻሻለው ሕገ መንግሥት ነበር።
ማሻሻያው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በሕዝብ ድምጽ በከፊል እንዲመረጡ የሚያደርግ ድንጋጌም ተካትቶበት ነበር።
ይሁን አንጂ እንደ ዶ/ር ሜርሲ ገለጻ ምርጫ ለማካሄድ እና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕጋዊ ተወካዮች አድርጎ ለማቋቋም ሁለት ዓመታት ያህል ፈጅቷል።
የቀደማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ ሁለቱ የሕግ መምሪያ እና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች ደርግ ባቋቋመው ብሔራዊ ሸንጎ ተተክተዋል።
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
በፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ይመራ የነበረውን መንግሥት የጣሉት አማጽያን ለአራት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት በሽግግር ምክር ቤት እና መንግሥት ነበር።
በ1987 ዓ.ም. የወጣው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት 'ፓርላሜንታዊ' መሆኑን ይደነግጋል።
ከዚህ በተጨማሪም የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሯል።
በሕገ መንግስቱ መሠረት የፓርላማው አባላት "ሁሉ አቀፍ፣ ነጻ፣ ቀጥተኛ፥ ትክክለኛ በሆነ እና ድምጽ በምሥጢር በሚሰጥበት ሥርዓት" በየአምስት ዓመቱ ይመረጣሉ።
የአባላቱ "ቁጥር የሕዝብ ብዛትን እና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት በማድረግ" ከ550 መብለጥ የለበትም። አናሳ ብሔረሰቦች ከዚህ ውስጥ ከ20 የማያንስ መቀመጫ እንዲኖራቸው ሕገ መንግሥቱ ያዝዛል።
ምክር ቤቱ አሁን ላይ የዕለት ተዕለት ተግባራቱን የሚያከናውነው በ2008 ዓ.ም. በወጣ "የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት የሥነ ምግባር" ደንብ አማካኝነት ነው።
በዚህ ደንብ መሠረት ምክር ቤቱ በተዋረድ የምክር ቤቱን ጠቅላላ ጉባኤ፣ አፈ ጉባኤ፣ ምክትል አፈጉባኤ እና የተለያዩ ኮሚቴዎችን የያዘ አጠቃላይ አደረጃጀት አለው።
በምክር ቤቱ የሥራ ዘመን መጀመሪያ ላይ በሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ወይም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መድረክ መሪነት አፈ ጉባኤው ይመረጣሉ።
አፈ ጉባኤው ከተሰጣቸው ሥልጣን እና ተግባራት መካከል ምክር ቤቱን በበላይነት መምራት እና ማስተዳደር ቀዳሚው ነው።
በተጨማሪም የምክር ቤቱን ስብሰባዎች የመምራት እና አስቸኳይ ስብሰባዎችን የመጥራት ሥልጣን አላቸው።
በደንቡ መሠረት ምክር ቤቱ አራት የስብሰባ ዓይነቶች አሉት።
በሳምንት ሁለት ቀናት ዘወትር ማክሰኞ እና ሐሙስ የሚካሄደው መደበኛ ስብሰባ ቀዳሚው ነው።
ሌላኛው የስብሰባ ዓይነት አስቸኳይ ስብሰባ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ እረፍት ላይ እያለ የምክር ቤቱን ውሳኔ የሚሹ አስቸኳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የሚጠራ ነው።
የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በምክር ቤቱ ውስጥ ለዚሁ በተዘጋጀ የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን፣ አስቸኳይ ስብሰባው ግን "አፈ ጉባኤው አመቺ ነው ባለው ቦታ" ሊካሄድ ይችላል።
አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ሲያጋጥመው ከመደበኛው የስብሰባ ጊዜ ውጭ ባሉት ቀናት የሚካሄደው ልዩ ስብሰባ ሦስተኛው የስብሰባ ዓይነት ነው።
አራተኛው እና የመጨረሻው የስብሰባ ዓይነት ዝግ ስብሰባ ነው። የምክር ቤቱ ስብሰባ በዝግ እንዲካሄድ አንድ ሦስተኛ የምክር ቤቱ አባላት ወይም አስፈጻሚው አካል ሊጠይቁ ይችላሉ። ነገር ግን ስብሰባው በዝግ እንዲካሄድ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ሊደግፉት ይገባል።
ምክር ቤቱ የሚወያይባቸውን አጀንዳዎች በመንግሥት፣ በአፈ ጉባኤው፣ በኮሚቴዎች፣ በአባላት ወይም በምክር ቤቱ ቡድን ሊመነጩ እንደሚችሉ ደንቡ ላይ ሰፍሯል።
አጀንዳ መቅረጽ ሥልጣን የተሰጠው ለምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ነው።
ይህ ኮሚቴ አፈ ጉባኤ እና ምክትሉን፤ እንዲሁም የፓርቲ ተጠሪዎችን ጨምሮ በምክር ቤቱ ቡድኖች ባላቸው መቀመጫ መጠን የሚወከሉበት ሲሆን፣ የሚመራው በአፈ ጉባኤው ነው።
ኮሚቴው ምክር ቤቱ የሚወያይበትን አጀንዳዎች ከመቅረጽ በተጨማሪ የምክር ቤቱን ረቂቅ በጀት ያዘጋጃል።
የቋሚ ኮሚቴዎች ሥልጣን ምንድን ነው?
በ2008 ዓ.ም. በወጣው ደንብ መሠረት ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራላቸውን ረቂቅ ሕግ በመመርመር ለምክር ቤቱ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባሉ።
ይህ ማለት ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ ሕግ ላይ የመጨረሻ ወሳኝ አካል ቋሚ ኮሚቴዎች ናቸው። ከረቂቁ ሊወጣ ወይም ሊካተት ይገባል የሚሉት ክፍል ካለ ማስተካከያ ማድረግም ይችላሉ።
እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ ከ11 እስከ 25 አባላት ሲኖሩት፣ በአንድ ሊቀመንበር እና በምክትል ሊቀ መንበር ይመራል።
ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራላቸውን ሕግ ሲመረምሩ በረቂቅ ሕጉ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ። ይህ ውይይት በተለምዶ የአስረጂዎች መድረክ የሚባል ሲሆን የሚሳተፉትም ረቂቅ ሕጉ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ በማዘጃት ግብዓት ይሰበስባሉ። ይህ ሂደት ደግሞ የባለድርሻ አካላት መድረክ ይባላል። በዚህ ሂደት የሚመለከታቸው ማናቸውም አካላት እና ግለሰቦች በረቂቅ ውይይቱ ላይ በመሳተፍ አስተያየት መስጠት ይችላሉ።
ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራላቸው ረቂቅ ሕግ "መሠረታዊ ችግር አለበት" ብለው ካመኑ ጉዳዩን ለአፈ ጉባኤው በማሳወቅ ሕጉ ተስተካክሎ እንዲላክ ለሚመለከተው አካል ሊመልሱት ይችላሉ።
ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ ሕጎች በሦስት የተለያዩ የንባብ ደረጃዎች ሊያልፉ ይችላሉ።
የመጀመሪያው ንባብ ረቂቅ ሕጉን ያመነጨው አካል ስለ ረቂቅ ሕጉ ዓላማ እና ይዘት አጭር ማብራሪያ የሚሰጥበት ነው።
በዚህ የንባብ ደረጃ ላይ በረቂቁ ሕግ ዓላማ እና ይዘት ላይ ውይይት ይደረጋል።
በቂ ውይይት ተደርጓል ተብሎ አፈ ጉባኤው ሲታመን ረቂቁ ለዝርዝር ምርመራ ወደ ኮሚቴ ይመራል።
ሁለተኛው የንባብ ደረጃ ዝርዝር ውይይት የሚካሄድበት ነው።
በረቂቅ ሕጉ ላይ በቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ ዝርዝር ውይይት የሚካሄደው በሁለተኛ ንባብ ወቅት ነው።
በዚህ ደረጃ ላይ በቀረበው ረቂቅ ወይም ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ላይ የማሻሻያ ሞሽን መቅረብ ይቻላል።
የማሻሻያ ሞሽኑ ተቀባይነት ካገኘ ረቂቁ እንደገና ወደ ኮሚቴ ይመራል።
ረቂቅ ሕጉ ዳግም የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ የመጨረሻ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ የሚያቀርብበት ደረጃ ሦስተኛ ንባብ ይባላል።
እነዚህን ሁሉ ሂደቶች አልፎ የጸደቀ ሕግ ለሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ለፊርማ መቅረብ አለበት።
ቋሚ ኮሚቴዎች ያላቸው ሌላኛው ሥልጣን መንግሥታዊ አካላትን መከታተል እና መቆጣጠር ነው። ቋሚ ኮሚቴዎች የሚከታተሏቸውን የመንግሥት ተቋማት ሪፖርት በየሩብ ዓመቱ ይገመግማሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በተቋማቱ በአካል በመገኘት የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎቸን ሊያከናውኑ ይችላሉ።
ቋሚ ኮሚቴዎች ተቋማትን የሚከታተሉት እና የሚቆጣጠሩት በዘርፍ በዘርፍ ነው።
ለምሳሌ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንደ ምርጫ ቦርድ እና እምባ ጠባቂ ያሉ የዲሞክራሲ ተቋማትን ይከታተላል።
የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፋይናንስ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያከናውኑ የመንግሥት ተቋማትን የመከታተል እና የመቆጣጠር ሥልጣን አለው።
ከዚህ በተጨማሪም የፌደራል መንግሥት ታክስ እና ቀረጥ አስተዳደር እና ገቢ አሰባሰብ በአግባቡ መከናወኑን ይከታተላል።
የፌደራል መንግሥቱ ዓመታዊ እና ተጨማሪ በጀት በአግባቡ ተዘጋጅቶ መቅረቡን እና መጽደቁን መቆጣጠርም የዚሁ ቋሚ ኮሚቴ ኃላፊነት ነው።
የመንግሥት ሹመኞች የሚቀርቡበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
በ2008 ዓ.ም. የወጣው ደንብ ምክር ቤቱ "አስፈላጊ ሁኖ ባገኘው ጊዜ" የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናትን ለጥያቄ እንደሚጠራ ይደነግጋል።
ከመንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓመት ሦስት ጊዜ በምክር ቤቱ ቀርበው ከሕዝብ እንደራሴዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅድሚ የሚቀርቡት ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ዓመታዊ የጋራ ስብሰባ ማግሥት ነው።
በዚህ ስብሰባ ላይ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ ያቀርባሉ። በዚህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የመንግሥትን አቋም ለመግለጽ እና ለማስረዳት ይገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስተሩ "በሚያዝላቸው መረሃ ግብር መሠረት" በዓመት ሁለት ጊዜ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባሉ።
ምክር ቤቱ ማንኛውም መንግሥታዊ አካል በቀጥታ ሪፖርት እንዲያቀርብለት የማዘዝ ሥልጣን አለው።
በቀረበው ሪፖርት ላይ የምክር ቤት አባላት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ሪፖርት አቅራቢው አካል ምላሽ ይሰጣል።
በምክር ቤቱ አሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ የፓርላማ አባል ጥያቄውን ከአስር ቀናት በፊት ለአፈ ጉባኤው በጽሑፍ ማቅርብ አለበት።
አፈ ጉባኤው ጥያቄውን ውድቅ ሊያደርጉ ወይም ሊቀበሉት ይችላሉ።
ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ አፈ ጉባኤው የሚመለከተው ሚኒስትር መልስ የሚሰጥበትን ፕሮግራም ያዘጋጃል።