"በኢትዮጵያ ውስጥ እጁን ያስገባ ምላሹን በእጥፍ እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም"

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኤርትራ ሠራዊት ድንበር ተሻግሮ ባለፉት ቀናት በተካሄዱ ውጊያዎች ውስጥ መሳተፉን በመግለጽ የኢትዮጵያ ምላሽ ከባድ እንደሚሆን ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣን ተናገሩ።

ሁለት ሳምንት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀሩት ትግራይ ክልል ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች በሚዋሰንበት አካባቢ በተቀሰቀሰው ጦርነት የህወሓት ኃይሎች ከፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል።

ከጦርነቱ መቀስቀስ በፊት እና በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋዊ ባልሆነ ሁኔታ የኤርትራ መንግሥት እጁ እንዳለበት በመግለጽ ሲከስስ ነበር።

የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ ቅርብ ለሆነው ፋና ቴሌቪዥን ቅዳሜ ምሽት በሰጡት ቃለ ምልልስ የኤርትራ መንግሥት በውጊያዎች ውስጥ በቀጥታ መሳተፉን ገልጸዋል።

ይህም የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ስለመግባቱ እና እየተደረገ ባለው ጦርነት ላይ በቀጥታ ስለመሳተፉ የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን በይፋ ሲናገር የመጀመርያው ነው።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አብረሃም በላይ (ዶ/ር) የኤርትራ መንግሥት ጦር በጦርነቱ በቀጥታ መሣተፉን በመጥቀስ "እጁን እያስገባ የማያርፍ አካል ካለ ምላሹ ምን እንደሆነ በጣም ግልጽ ነው" ብለዋል።

የኤርትራ መንግሥት በተደጋጋሚ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ስለመሳተፉ ለሚቀርብበት ውንጀላ ሲያስተባብል ቆይቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ የሚገኘውን ኤምባሲውን በመዝጋት በአዲስ አበባ የሚገኙ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ማባረሩ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም ኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን አስታውቋል።

ዶ/ር አብርሃም "በዚህ ጦርነት ላይ የሻዕቢያ መንግሥት፣ የሻዕቢያ ሠራዊት ተሳትፏል። ከእነ ትጥቁ፣ ከእነ መሣሪያው ግንባር ወስዶ ማለት ነው። የሞተም መሣሪያዎቹም የተማረኩ መዓት ናቸው" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአፋር ክልል ባለሥልጣናት በክልሉ እየተዋጉ ነው ያሏቸው የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም ወታደራዊ ቁሳቁሶች መማረካቸውን ተናግረው ነበር።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ለቢቢሲ ትግርኛ በሰጡት ምላሽ ግን "የብልጽግና መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ካሉት በርካታ ግጭቶች ላይ ትኩረት ለማስቀየር ጎረቤት አገራትን መወንጀል ልማዱ ሆኗል" በማለት የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።

የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ኤርትራ ታደርገዋለች ላሉት ጣልቃ ገብነት "መልሱ እጥፍ ሆኖ እንደሚመለስ ምንም ጥርጥር የለውም። በሰው አገር ገብቶ ከመንግሥት በተቃራኒ ከሽፍታ እና ከባንዳ ጋር ሆኖ ተጣምሮ መምጣት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ምላሹን ያገኘዋል" ሲሉ ዝተዋል።

"አገር እየደፈረ ዝም ብሎ የሚመለከተው አካል የለም። ኢትዮጵያዊ እንደዚህ ዓይነት ባህሪ የለውም። መንግሥታችንም ይህንን አይቀበልም" በማለት "እጁ መሰብሰብ ያለበት አካል እጁን መሰብሰብ አለበት" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም. በተካሔደ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኤርትራ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ወግኖ ተሰልፎ ነበር።

የኤርትራ እና ኢትዮጵያ መንግሥት ግንኙነት መሻከር የጀመረው የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ ነበር።

ባለሥልጣኑ በተጨማሪም በትግራይ ክልል ዋና ከተማ በፌደራሉ እና በአጋር ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መግባቷን ተከትሎ በፍጥነት መረጋጋት እና ሰላምን ለማምጣት እንዲሁም ሕዝቡ ራሱን በራሱ የሚያስተዳደረው አካል የማደራጀት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ይህንን ያሉት የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል እና በትግራይ ሰላም ኃይሎች እጅ መግባቷ ቅዳሜ ከሰዓት ከተሰማ በኋላ ነው።

ከዚያ ቀደም ብሎ የህወሓት ኃይሎች መዲናዋን ለቅቀው መውጣታቸውን ኤኤፍፒ እና ሮይተርስ የዜና ወኪሎች ዘግበው ነበር።

አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ጦርነቱን "መንግሥት እናፈርሳለን" ብለው የጀመሩት ራሳቸው [ህወሓት] ናቸው ያሉ ሲሆን "መከላከል አድርገን እነርሱን በሄዱበት እና በገቡበት ቦታ እያጸዳን ነው" በማለት ዘመቻው መቀጠሉን አመልክተዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ኃላፊነት ወስዶ በፍጥነት የቀበሌ፣ የወረዳ የአስተዳደር መዋቅሮችን ሕዝቡን በማሳተፍ እንደሚያደራጅ ጨምረው ተናግረዋል።

ይህም ክልሉ በቶሎ ተረጋግቶ በፍጥነት በወራት ውስጥ ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶ/ር አብርሃም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ህወሓት ከፕሪቶሪያ "ማግሥት" ጀምሮ ስምምነቱን ለማፍረስ ሲሠራ ነበር ሲሉ ወንጅለዋል።

ህወሓት በሰላም እና በድርድር የሚያምን ቡድን አይደለም ሲሉ የከሰሱት ዶ/ር አብርሃም፣ በስምምነቱ ላይ የተቀመጡት ነገሮች መንግሥት ሙሉ በሙሉ ፈጽሟል ብለዋል።

ህወሓት በተደጋጋሚ ግጭት እና ትንኮሳ ፈጽሟል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ "ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ሠራዊት ሲያሰለጥኑ፣ ትጥቅ ሲያስገቡ ከአገር ውስጥ ግጭት ፈጣሪዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከባዕዳን ጋር ተሳስረው ሲሰሩ ፕሪቶሪያን በየቀኑ እያፈረሱት ነበር" ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

በጋራ የሚፈጸሙ ተፈናቃዮችን መመለስም ቢሆን "ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያነት" አስቁመውታል በማለት ተናግረዋል።

ዶ/ር አብርሃም ህወሓት ተፈናቃዮችን መያዣ አድርጎ ሲጠቀም ቆይቷል በማለት "አሁን ፈጣሪ ይመስገን ወደ ቤታቸው ይገባሉ ማለት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ለሁለት ሳምንት ያህል በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ በሁለቱም ወገኖች ወጣቶች መሞታቸውን የተናገሩት ዶ/ር አብርሃም፣ ብዙ ለልማት የሚውል ሃብት በዚህ ጦርነት እየፈሰሰ ነው በማለት "ይህም ለአንድ አገር ኪሳራ ነው" በቃለ መጠይቀቸው ወቅት አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኢትዮጵያ የኤርትራን እና የግብፅን ዲፕሎማቶች ካስወጣች በኋላ ባወጣው መግለጫ የተካረረው ውጥረት እንዳሳሰበው እና በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ አስታውቋል።

ሦስቱ የኅብረቱ አባል አገራት "ውጥረቱን ከሚያካርሩ እንዲሁም የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት ከሚያናጉ ድርጊቶች እና መግለጫዎች እንዲቆጠቡ" አሳስቧል።

ሦስቱ አገራት ልዩነታቸውን በአፍሪካ ኅብረት መርኅ መሠረት "በዲፕሎማሲያዊ መስመሮች እና በሰማላዊ ንግግር እንዲፈቱ" ኮሚሽኑ አሳስቧል።