ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚገኘው የፋሮ ሆሞሻ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት በዓለም አቀፍ ውድድር ለፍጻሜ ደረሰ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው "የፋሮ ሆሞሻ" የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት "ቲ-ፎር" የተሰኘ ተቋም በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ውድድር ምርጥ ትምህርት ቤት በመባል ለፍጻሜ ከተመረጡ 10 ትምህርት ቤቶች አንዱ እጩ ሆኖ ቀረበ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዲሳሳ ማሩ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ፋሮ ፋውንዴሽን በተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም የሚተዳደረው ይህ ትምህርት ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተወዳደሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ10 እጩዎች አንዱ መሆን ችሏል።
የፋሮ ሆሞሻ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ10 እጩዎች አንዱ መሆን የቻለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የላቀ ውጤት ማምጣት በሚለው ዘርፍ ነው።
በዚህ ልዩ ዘርፍ ከተመረጡት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች መካከል የቱርክ፣ የሶማሊያ፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል።
ዶ/ር ዲሳሳ እንደተናገሩት፤ ኮሞሻ ወረዳ የሚገኘው እና በፋሮ ፋውንዴሽን የሚደገፈው ትምህርት ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትምህርት የሚሰጥ ልዩ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ነው።
ተማሪዎቹም በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ተናግረዋል።
አምና የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች 100% ብሔራዊ ፈተናውን እንዳለፉ እና ዘንድሮ ደግሞ 90% የሚሆኑት ፈተናውን ማለፋቸውንም ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ የተመረጠው "አስቸጋሪ ሁኔታን ተቋቁሞ ትምህርትን በአግባቡ በመስጠት፣ የተማሪን ውጤት በማሻሻል ወይም ተማሪን ብቁ በማድረግ" እንደሆነም ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃም የተሻሉ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች አንዱ እንደሆነ በመጥቀስ "አስቸጋሪ ሁኔታን ተቋቁመው የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ትምህርት ቤቶች" በውድድሩ መካተታቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሚያገኙትን ትምህርት ቤቶች ለመለየት ድምጽ የመስጠት ሒደት ይከናወናል።
"በተሻለ ሁኔታ ስማችንን፣ አገራችንን ሊያስጠራ ይችላል" ሲሉም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።
'ቲ ፎር ኢዱኬሽን' የተባለው ተቋም አስቸጋሪ ሁኔታን ተቋቁሞ ትምህርት በመስጠት፣ በማኅበረሰብ ትብብር፣ ጤናማ ሕይወትን በመደገፍ፣ በፈጠራ እና በሌሎችም ዘርፎች የላቁ ትምህርት ቤቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተምራል።
አስቸጋሪ ሁኔታን ተቋቁሞ የመማር ማስተማር ሒደትን ማስቀጠል የሚለው አንደኛው የውድድር መስፈርት እንደሆነ ዶ/ር ዲሳሳ ተናግረዋል።
"የምጣኔ ሃብት ችግር ወይም የትምህርት ጥራት ውስንነት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ያሉ የተሻሉ ትምህርት ቤቶች ይወዳደራሉ" ብለዋል።
በፋሮ ፋውንዴሽን የተመሠረተው የፋሮ ሆሞሻ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቀዳሚው መሆኑን የትምህርት ቤቱ ድረ ገጽ ያትታል።
የኢትዮጵያን ሥርዓተ ትምህርት ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር አዋህዶ ትምህርት እንደሚሰጥም ተጠቅሷል።
ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ለአራት ዓመታት ሴት ተማሪዎች ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ ትምህርት ያገኛሉ።
ፋሮ ሆሞሻ የተከፈተው በአውሮፓውያኑ 2018 ሲሆን 240 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም አለው።
ሴቶች ትምህርት ለማግኘት የሚገጥማቸውን መሰናክል ማለፍ እንዲችሉ በሴቶች ላይ ብቻ ትኩረት እንደሚያደርግ በድረ ገጹ ተመልክቷል።
ትምህርት ቤቱ በአሶሳም ቅንጫፍ ያለው ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ውጭ በሩዋንዳ፣ ኬንያ እና ሶማሊያም ቅንጫፎች አሉት።
በአጠቃላይ በአራት አገራት በሚገኙ ስምንት ትምህርት ቤቶች 4700 ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።