በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሆሳዕና ከተማ 400 ገደማ ውሾች ለምን እና እንዴት ተገደሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሀዲያ ዞን፣ ሆሳዕና ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ውሾች በጅምላ ሲገደሉ የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ከተጋሩ በኋላ በርካቶችን አስቆጥቷል።
ቢቢሲ ያነገጋራቸው ሦስት ነዋሪዎች እና የከተማዋ ባለሥልጣን እንዳሉት ውሾቹን በጅምላ መግደል የተጀመረው ሦስት ታዳጊዎች ከእብድ ውሻ በሽታ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ነው።
ሆኖም ነዋሪዎች የራሳቸውን ውሻ እንዲገድሉ ጭምር የተገደዱበት እርምጃ ነዋሪዎችን እና የእንስሳት መብት ተሟጋቾችን አሳዝኗል።
በከተማዋ ከሚገኙ 10 ቀበሌዎች የአንዱ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ፣ እርሳቸው በሚኖሩበት ቀበሌ የጅምላ ግድያው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 18/2018 ዓ.ም. መጀመሩን ጠቅሰው፣ የእርሳቸው ውሻ በማግስቱ እንደተገደለባቸው ተናግረዋል።
አንድ የዐይን ምሥክርም የቀበሌ ተወካዮች የተከተበም ቢሆንም ውሻቸውን እንዲገድሉ ለነዋሪዎች ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገልጿል።
በዚህም ምክንያት የውሻ ባለቤቶች እንደ ቤተሰብ የሚያዩትን ውሻቸውን በገመድ አንቀው ወይም ደብድበው እንዲገድሉ መገደዳቸው ተናግሯል።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ ነዋሪም ግድያው የጀመረው ወንድም እና እህት የሆኑ ታዳጊዎች በውሻ ተነክሰው ከሞቱ በኋላ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ክትባት እየተሰጠ የነበረ ቢሆንም የአካባቢ ተወካዮች ውሾቹ ቢከተቡም ባይከተቡም እንዲገደሉ ዘመቻ ጀመሩ" ብለዋል።
የውሻ ባለቤቶችም የራሳቸውን ውሻ እንዲገድሉ እና ለአካባቢው ማኅበር እንዲያሳውቁ፣ ይህን ካላደረጉ 50 ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም እስር እንደሚገጥማቸው ሲያስገድዱ እንደነበርም ነዋሪው ተናግረዋል።
ይህንንም ለቀናት ሲያደርጉ ነበር ያሉት ነዋሪው፣ "በኋላ ላይ የከተማዋ አስተዳደር ለቀበሌዎቹ አስተዳዳሪዎች ደብዳቤ በመፃፍ እርምጃውን አስቆመ" ብለዋል።
ውሻቸው የተገደለባቸው ግለሰብ በበኩላቸው የቀበሌ ተወካዮች ሁለት ቀን ወደ ቤታቸው እንደሄዱና ውሻቸው እንደተከተበ በመንገር እንደመለሷቸው ያስታውሳሉ።
"ሆኖም በሁለተኛው ቀን ከሰዓት እኔ በሌለሁበት ወደ ቤት ሄደው 'በሽታው የተከተበ ውሻም አይመርጥም፤ በአየር ጭምር ነው የሚተላለፈው የግድ መግደል አለባችሁ' ብለው ባለቤቴን አስፈራሯት። ከዚያ ወደቤት ስመለስ እባክህ ከነልጆቼ ላልቅ ነው በቃ ይገደል ብላ ጮኸችብኝ፤ አለቀሰች" ይላሉ።
ከዚያም ወደ ቀበሌያቸው አስተዳዳሪ ሄደው ለማስረዳት መሞከራቸውን፤ ነገር ግን ምክንያታቸውን ሊቀበሏቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
"'እኔም የራሴን ገድያለሁ የግድ መግደል አለብህ' አለኝ። ውሻውን ያልገደለ ደግሞ 50 ሺህ ብር እና 3 ወር እስር እንደሚጠብቀው በተደጋጋሚ ስለሚነግሩን እንግዲያውስ እኔ ሳላየው ግደሉት ብዬ አሳልፌ ሰጠኋቸው እና ከሰፈር ትንሽ ራቅ ያለ ቦታ ላይ ገደሉት" ሲሉ የተፈጠረውን አስረድተዋል።
"በጣም ነው ያዘንኩት። አምስት ዓመት አብሮኝ የኖረ እና የቤታችን ድምቀት የነበረ ውሻ ነበር" ብለዋል በሐዘን።
ግለሰቡ በእነርሱ ቀበሌ ብቻ ቢያንስ ከ100 በላይ ውሻዎች መገደላቸውን እና ሁሉም ባለቤት ያላቸው ውሻዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በከተማዋ የእንስሳት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አልአዛር አየለ በበኩላቸው ክትባት መሰጠት ቢጀምርም የአካባቢ ተወካዮች ውሻዎች እንዲገደሉ ዘመቻ መጀመራቸው ገልጸዋል።
"ባለቤቶች የራሳቸውን ውሻ እንዲገድሉ ታዝዘዋል፤ ይህን አላደርግም ያሉም ታስረዋል" ብለዋል።
አልአዛርን ጨምሮ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ለቀናት በዘለቀው የጅምላ ግድያ ከ400 እስከ 450 የሚደርሱ ውሾች መገደላቸውን ተናግረዋል።
እንደ ከተማ አስተዳደሩ ከሆነ በሆሳዕና ከተማ 10 ሺህ ገደማ ውሻዎች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን 7 ሺህ ያህሉ ተከትበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Feven Melese
አልአዛር " ሰዎች ውሻዎችን እየጎተቱ በሚያሰቅቅ ሁኔታ ሲገድሏቸው እንደነበር ጠቅሰው" ይህ በክልሉ ባህል፣ ሃይማኖት እና ሕግ ከሞራል ያፈነገጠ እና ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
በሕግ ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባም አክለዋል።
ግድያው የተጀመረው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሲሆን ለቀናት ቀጥሎ ነበር ያሉት አልአዛር አሁንም እንዳልቆመ መረጃዎች እየደረሷቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
በጅምላ የሚገደሉትን ውሾች የማዘጋጃ መኪና እየተከታተለ ሲሰበስባቸው እንደነበረ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ ባለፈው ሳምንት ሦስት ታዳጊዎች በውሻ በሽታ መሞታቸው ለእርምጃው መንስኤ ነው ብለዋል።
"የአንድ ቤተሰብ ልጆች የሆኑ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሞተዋል። በኋላ ላይ የ14 ዓመት ታዳጊ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ አልፏል" ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ ራሱ ማኅበረሰቡ በሕገ ወጥ መንገድ ውሻዎችን መግደል እንደጀመረ አስረድተዋል።
ሌሎች ወደ 80 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ሕክምና እንደተደረገላቸውም ከንቲባው ጠቅሰዋል።
የከተማዋ አስተዳደር በእርምጃው ተሳትፎ እንደሌለው የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ አስተዳደራቸው የግድያ ዘመቻውን በግማሽ ቀን ውስጥ ማስቆሙንም ተናግረዋል።
"ግድያው የተጀመረው በአንድ አካባቢ ነው፤ ሆኖም በፖሊስ እና በፀጥታ ኃይሎች በአንድ ቀን ውስጥ እርምጃውን አስቁመናል" ሲሉም አክለዋል።
ከንቲባው ስለተገደሉት ውሾች ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበው በክስተቱ ላይ ምርመራ እንዲደረግ "ለፖሊስ ትዕዛዝ መስጠታቸውን" ተናግረዋል።
"አሁን ላይ በከተማዋ የትኛውም አካባቢ የሚፈፀም ግድያም የለም" ብለዋል።
ከንቲባው ይህን ቢሉም የእንስሳት መብት ተሟጋቿ ፌቨን መለሰ ግን አሁንም ግለሰቦች ቤት ለቤት እየሄዱ ያልተከተቡ ውሾችን እንዲገድሉ እያሳሰቡ መሆኑን መረጃ እንደደረሳት ገልጻለች።
አልአዛርም ግድያዎች መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ የእንስሳት መጠለያ ያላት ተሟጋቿ ፌቨን ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት በሕግ እንዲቀጡ ጠይቃለች።
"የአካባቢው የመንግሥት አካላት እኛ አላደረግንም፤ ትዕዛዝ አልሰጠንም ካሉ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ማድረግ አለባቸው" ብላለች።
ውሾች በአሰቃቂ ሁኔታ ታንቀው እና ተደብድበው መገደላቸውን የጠቀሰችው ፌቨን "በግድያው ላይ ሕፃናት መሳተፋቸው በራሱ ትውልድን መግደል ነው" ስትልም ኮንናለች።
የእንስሳት ሐኪሙ አልአዛር አየለም እርሳቸው አባል የሆኑበት 'ዘ ብሉ ቬት' የተባለ በእንስሳት ደኅንነት ላይ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመሆን የጅምላ ግድያውን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥረት መጀመራቸውን ተናግረዋል።















