የዓለምን ኢኮኖሚ ካናጋው የኢራን ጦርነት ቢሊዮኖች እያተረፉ ያሉት ኩባንያዎች

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ባስከተለበት በዚህ ወቅት፤ የተወሰኑ ኩባንያዎች እጅግ ከፍተኛ ትርፍ እያገኙ ነው።

በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው እርግጠኝነት ማጣት እና ኢራን የወሰደችው ሆርሙዝ ወሽመጥን የመዝጋት እርምጃ የሸቀጦች ዋጋ በመናሩ የኑሮ ውድነትን እያስከተለ ነው። የተቋማት፣ ቤተሰቦች እና መንግሥታት ኪስም በዚሁ ምክንያት ተፈትቷል።

ጦርነቱ አንዳንዶችን ወደ ገደል አፋፍ ቢያደርስም፤ ንግዳቸው በጦርነት ወቅት የበለጠ ትርፍ የሚያስገኝላቸው ወይም የኤነርጂ ዋጋ መናር የጠቀማቸው ተቋማት ግን ከዚህ በፊት ያልታየ ገቢ አስመዝግበዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት መቀጠል ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እያተረፉ ያሉ ዘርፎች እና ኩባንያዎች መካከል የተወሰኑትን እነሆ፦

1. ነዳጅ እና ጋዝ

እስካሁን ድረስ ጦርነቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫናውን ያሳደረው የኤነርጂ ዋጋን በማናር ነው። ከዓለም የነዳጅ እና የጋዝ ጭነት አንድ አምስተኛ ያህሉ የሚጓጓዝበት የሆርሙዝ ወሽመጥ፤ ከየካቲት መጨረሻ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የመርከቦችን ጉዞ ማስተናገድ አቁሟል።

ይህም የነዳጅ ዋጋ እንዲንር ያደረገ ሲሆን፣ ከዓለም ግዙፍ የነዳጅ እና ጋዝ ኩባንያዎች ውስጥም የተወሰኑት በዚህ ክስተትተጠቃሚ ሆነዋል።

ከፍተኛውን ጥቅም ያገኙት ግዙፎቹ የአውሮፓ የነዳጅ ኩባንያዎች ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች ሽያጭ የሚያከናውኑበት የንግድ ክንፍ ስላላቸው በዋጋ መናር ትርፋቸውን መጨመር ችለዋል።

'ቢፒ' የተባለው የብሪታኒያ የነዳጅ ኩባንያ በ2026 የመጀመሪያያዎቹ ሦስት ወራት ትርፉ ከእጥፍ በላይ አድጎ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የኩባንያው የንግድ ዘርፍ "ልዩ" አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጿል።

ሌላኛው የነዳጅ ኩባንያ 'ሼል' በበኩሉ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 6.92 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ተንታኞች ከጠበቁት በላይ ትርፍ አስመዝግቧል።

ግዙፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያ 'ቶታልኤነርጂስ' በበኩሉ በነዳጅ እና በኢነርጂ ገበያ ዋጋ መጨመር የተነሳ ትርፉ በአንድ ሦስተኛ ገደማ ጨምሯል። በሦስት ወራት ውስጥ ያገኘው ትርፍ 5.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ አስታውቋል።

የአሜሪካዎቹ ኩባንያዎች 'ኤክሶንሞቢል' እና 'ቼቭሮን' ግን በመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት ገቢያቸው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ብሎ ቢታይም፤ ያገኙት ትርፍ ከባለሙያዎች ግምት የበለጠ ነው።

የነዳጅ ዋጋ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከነበረው በእጅጉ የጨመረ በመሆኑ፤ የሁለቱም ኩባንያዎች ትርፍ እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

2. ግዙፍ ባንኮች

ከዓለም ትላልቅ ባንኮች መካከል የተወሰኑት በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ወቅት ትርፋቸው ጨምሮ ታይቷል።

የጄፒ ሞርጋን የንግድ ዘርፍ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ 11.6 ቢሊዮን ዶላር ታሪካዊ ገቢ አስመዝግቧል። ይህ ገቢ ባንኩ በታሪኩ ካገኛቸው ከፍተኛ የሩብ ዓመት ትርፍ ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው።

ዋናዎቹ ስድስት ግዙፍ ባንኮች የሚባሉት ባንክ ኦፍ አሜሪካ፣ ሞርጋን ስታንሊ፣ ሲቲ ግሩፕ፣ ጎልድማን ሳክስ፣ ዌልስ ፋርጎ እና ጄፒ ሞርጋን የዓመቱ መጀመሪያው ሦስት ወር ትርፋቸው በከፍተኛ መጠን አድጓል።

ባንኮቹ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የ47.7 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።

በዌልዝ ክለብ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ዳይሬክተር ሱዛና ስትሬተር "ከፍተኛ መጠን ያለው የንግድ ለውውጥ መኖሩ የኢንቨስትመንት ባንኮችን፤ በተለይም ሞርጋን ስታንሊን እና ጎልድማን ሳክስን ተጠቃሚ አድርጓል" ብለዋል።

እነዚህ የዎል ስትሪት ዋነኛ አበዳሪዎች በንግድ ልውውጥ ፍላጎት መጨመር ምክንያት ገቢያቸው አድጓል። ኢንቨስተሮች የመክሰር ስጋት ያለባቸውን አክሲዮኖች እና ቦንዶችን በመሸጥ ገንዘባቸውን አስተማማኝ መስለው ወደሚታዩ ሀብቶች ለማዛወር መጣደፋቸው ለባንኮቹ ትልቅ ዕድል ሆኗል።

ጦርነቱ በፋይናንስ ገበያው ላይ የፈጠረውን የዋጋ መዋዠቅ ተጠቅመው ለማትረፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶችም የንግድ ልውውጥ መጠኑ እንዲጨምር አድርገዋል።

የስትራቴጂ ዳይሬክተሯ ስትሬተር "በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው አለመረጋጋት የንግድ ልውውጥ እንዲጨምር አድርጓል። ውጥረቱ ይባባሳል የሚል ስጋት የገባቸው የተወሰኑ ባለሀብቶች አክሲዮኖቻቸውን ሲሸጡ፤ ሌሎች ደግሞ የዋጋ ቅናሹን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አክሲዮኖችን በመግዛታቸው ገበያው እንዲያገግም እገዛ አድርገዋል" በማለት አስረድተዋል።

3. መከላከያ

በኦዲት እና ታክስ ተቋሙ 'አርኤስኤም ዩኬ' ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ኤሚሊ ሳዊች እንደሚናገሩት፤ በየትኘውም ግጭት ውስጥ ቀዳሚው ተጠቃሚ የመከላከያ ዘርፍ ነው።

"ግጭቱ በአየር መከላከያ አቅም ላይ ያለውን ክፍተት በማሳየቱ በመላው አውሮፓ እና በአሜሪካ የሚሳዔል መከላከያ፣ የድሮን መከላከያ ሥርዓቶች እና የወታደራዊ መሣሪያዎች ላይ የሚወጣው ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ አድርጓል" ይላሉ።

ጦርነቱ የመከላከያ ኩባንያዎችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ አጉልቶ ከማሳት በተጨማሪ፤ መንግሥታት የጦር መሣሪያ ክምችታቸውን የመሙላት ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጓል። የመንግሥታቱ የመሣሪያ ፍላጎት፤ የግዢ ፍላጎትን ጨምሯል።

እንደ ኤፍ-35 ያሉ ተዋጊ ጄቶችን እና አካላትን የሚያመርተው 'ቢኤኢ ሲስተምስ' የተባለው ኩባንያ፤ ባወጣው መረጃ በዚህ ዓመት ሽያጩ እና ትርፉ ላይ ጠንካራ እድገት ይኖራል ብሎ እንደሚጠብቅ አስታውቋል።

በዓለም ዙሪያ "የደኅንነት ስጋት" እየጨመረ መምጣቱ የመንግሥታትን ወታደራዊ ወጪ ማሳደጉን የገለጸው ኩባንያው፤ ይህ ሂደት በምላሹ "ምቹ ሁኔታ" እንደሚፈጥርለት አስረድቷል።

ሎክሄድ ማርቲን፣ ቦይንግ እና ኖርዝሮፕ ግሩማን የተባሉት የዓለም ትላልቅ የመከላከያ ምርት አቅራቢዎችም በ2026 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከፍተኛ ትዕዛዝ እንደቀረበላቸው አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ መጠን ሲጨምር የነበረው የመከላከያ ኩባንያዎች አክሲዮን፤ ዘርፉ የተሰጠው ዋጋ ከሚገባው በላይ ነው የሚል ስጋት በመፍጠሩ ከመጋቢት አጋማሽ አንስቶ ወርዷል።

4. ታዳሽ ኃይል

ጦርነቱ ዓለም አማራጭ የኃይል አቅርቦትን በማስፋት በነዳጅ ላይ ያለን ጥገኝነት መቀነስ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማሳየቱን በዌልዝ ክለብ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ዳይሬክተር ሱዛና ስትሬተር ይናገራሉ።

እንደ ስትሬተር ገለጻ፤ የትራምፕ አስተዳደር የነዳጅ ቁፋሮን በከፍተኛ ደረጃ በሚያበረታታበት አሜሪካ ውስጥ ጭምር "የታዳሽ ኃይል ዘርፍ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ" ጨምሯል።

ጦርነቱ በታዳሽ ኃይል ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የኢነርጂ አቅርቦት የተረጋጋ እንዲሆን ለማድረግ እና ድንገተኛ ቀውሶችን የመቋቋም አቅምን ለመገንባት አፈስላጊ መሆኑ ይበልጥ እንዲታመን ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀውስ ተጠቃሚ ከሆኑ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው በፍሎሪዳ የሚገኘው 'ኔክስትኢራ ኤነርጂ'፤ በዚህ ዓመት የአክሲዮን ዋጋው በ17 በመቶ አድጓል። ይህ የዋጋ እድገት የታየው ኢንቨስተሮች በኩባንያው ዓላማ ላይ ያላቸው እምነት በመጨመሩ እንደሆነ ተገልጿል።

ግዙፍ የዴንማርክ የንፋስ ኃይል ኩባንያዎች የሆኑት 'ቬስታስ' እና 'ኦርስተድ' በበኩላቸው ከፍተኛ ትርፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። የኩባንያዎቹ ትርፍ መጨመር የኢራን ጦርነት ተፅዕኖ የታዳሽ ኃይል ኩባንያዎችን እያሳደገ መሆኑን ያመለከተ ሆኗል።

የዩናይትድ ኪንግደሙ 'ኦክቶፐስ ኤነርጂ' ደግሞ ከየካቲት መጨረሻ ጀምሮ የሶላር ፓናል ሽያጭ በ50 በመቶ ማደጉን አስታውቋል።

የነዳጅ ዋጋ መናርም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን፤ በተለይም የቻይና አምራቾች አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ነው።