ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አባቱን ገድሎ 12 ዓመት የተፈረደበት ልጅ ይቅርታ እንዲደረግለት የሚጠይቀው ቤተሰብ
ማስጠንቀቂያ፦ይህ ጽሑፍ ዝርዝር ወሲባዊ፣ አካላዊ እና የሥነ ልቦና ጥቃቶችን የያዘ ስለሆነ የተወሰኑ አንባቢዎችን ሊረብሽ ይችላል።
ሳራ ማርቲኔዝ የ28 ዓመቱ ወንድሟ ከአባቷ ጋር እንዳይጋጭ ትለምነው ነበር። በርግጥ አባት በተደገጋሚ ልጁ ላይ ጥቃት መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ለረዥም ጊዜ የቆየ አለመግባባት በመካከላቸው ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ ግንቦት 2025 የኡራጓይ ዋና ከተማ በሆነችው ሞንቴቪዴዮ ዳርቻ ላይ ሞይሰስ አባቱ ካርሎስ እናቱና ሁለት እህቶቹ ላይ ጾታዊና አካላዊ ጥቃት ያደርስ እንደነበር ተረዳ።
በማግስቱ ሞይሰስ አባቱን 14 ጊዜ በጥይት ተኩሶ በመግደል ለሁለት ቀናት ከአስከሬኑ አጠገብ ከቆየ በኋላ እጁን ለፖሊስ ሰጠ።
አሁን ሞይሰስ የኡራጓይ ነዋሪዎች በዩቲዩብ ስርጭት በቀጥታ በተከታተሉት እና የሕዝብ ቁጣን በፈጠረው የፍርድ ሂደት የ12 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።
የሞይሰስ ወንድሞችና እህቶች ይቅርታ ሊደረግለት እንደሚገባ ያምናሉ። እናም በጥፋተኝነት ውሳኔው ላይ ይግባኝ ለማለት ጥረት እያደረጉ ነው።
የ27 ዓመቷ ሳራ ከእንባዋን ጋር እየታገለች ለግድያው ምክንያት የሆነውን አሳዛኝ ክስተት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ካርሎስ ለዓመታት ሞይሰስን እንደደበደበና አካላዊ ጥቃት እንደፈጸመበት የሰማችው ያኔ ነበር።
"የደረሰበትን እና የተሸከመውን የስሜት ቀውስ መጠን ሙሉ በሙሉ አልተረዳሁትም" ስትል ገልጻለች። "በችሎቱ ወቅት ብቻ የተረዳናቸው ብዙ ነገሮች አሉ" ስትል አክላለች።
ሳራ እንደገለጸችው ሞይሰስ እና እህቶቿ አባታቸውን በጣም ይፈሩ ነበር። "እሱ ሁሉም ቦታ የሚገኝ ሰው ነበር። እሱ በአካባቢው ባይኖርም እንኳ ፍርሃትን ይፈጥራል" ትላለች።
"ጎህ ሲቀድ ተነስቶ ወደ መጸዳጃ ቤት ይወስደናል፣ ሻወር ይከፍትና ለሰዓታት በቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ይተወናል።"
ሳራ አባቷ ካርሎስ እሷንና ታላቅ እህቷን አናን ጾታዊ ጥቃት እንደፈጸመባቸው ትናገራለች።
ከእያንዳንዱ ጥቃት በኋላ አባቷ እያለቀሰ ይቅርታ እንድታደርግለት እንደሚለምናት፣ የምትወደውን ጣፋጭ ምግብ፣ ከቸኮሌት እና ከካራሚል የተሠራ ተወዳጅ የዳቦ ኩኪስ ይዞላት እንደሚመጣ ለሞይሰስ ነግራዋለች።
"አሁን እነሱን እንኳን መብላት አልችልም" ትላለች። "ጥፋተኛነት ተሰማኝ፤ ጣፋጭ ምግቡን ለመብላት ስል ብቻ እንዲበድለኝ እየፈቀድኩለት እንደሆነ ተሰማኝ።"
ሳራ አባቷ እናቷ ሥራ በሄደችበት ሌሊት ወሲባዊ ጥቃት የፈጸመባቸውን 60 አጋጣሚዎች እንደቆጠረች ትናገራለች።
"እኔ የቆጠርኳቸው አንድ ቀን ስለእርሱ ለመናገር ድፍረት እንደሚኖረኝ ለራሴ ስለነገርኩት ነው።"
ሳራ በ12 ዓመቷ አባቷ ካርሎስ አና ላይ ጾታዊ ጥቃት ሲፈጽም ከተመለከተች በኋላ ለትምህርት ቤቷ ተናገረች።
"በወረቀት ላይ 'የጾታዊ ጥቃት' በማለት እንደጻፍኩ አስታውሳለሁ፤ በወቅቱ ለቅርብ ጓደኛዬ ሰጠኋት" ትላለች፤ ከዚያም ሌላ የክፍል ጓደኛዋ ወረቀቱን ወደ ርዕሰ መምህርቷ መውሰዷን ገልጻለች።
ሳራ ከዚያ በኋላ የተከሰተውን ነገር ስታስታውስ በተለይም ፖሊስ ያቀረበላት የምርምራ ጥያቄ አሰቃቂ ተሞክሮዎችን እንድታሳልፍ ማድረጉን ትገልጻለች፥።
ምርመራውን ተከትሎ ካርሎስ የሦስት ዓመት እስራት ቢፈረድበትም አንድ ዓመት ብቻ ታስሮ ተለቀቀ።
ሳራ "አባቴ ከሦስት ዓመት በላይ ጥቃት እንደፈጸመብኝ ስለማውቅ፣ በጣም ትንሽ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር" ትላለች።
"አባቴ ጭራቅ ነበር። ለትምህርት ቤቱ በነገረው ታሪክ ውስጥ አባቱ እህቱ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከቤት የወጣ ድሃና አቅመ ቢስ ሰው አድርጎ ራሱን ገልጾታል።"
ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ ቤተሰቡ ካርሎስ ወደ ቤታቸው እንዲመለስ ፈጽሞ እንዳልፈቀዱለት ይናገራሉ።
ሳራ ግን አባቷ በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለች በትምህርት ቤቷ እና ትልቅ ሰው ከሆነች በኋላ ደግሞ ሥራ ቦታዋ ይመጣ እንደነበር ትናገራለች።
ሳራ የቤተሰብ አባላቱ በአባታቸው ስለተፈጸመባቸው የጥቃት መጠን ተነጋግሮ እንደማያውቅ ትናገራለች።
ሞይሰስ አባቱ ከእስር ቤት ከተፈታ በኋላ ያለውን ግንኙነት ለመቀጠል ፈልጎ እንደነበር ሳራ ታስታውሳለች።
ነገር ግን እናታቸው መርሴዲስ ፔሬራ ካርሎስ እያስፈራራት እንደሆነ ተናገረች። ለዓመታት የተፈፀመውን በደል ስትገልጽለት ሞይሰስ ወዲያውኑ እህቶቹን ለማግኘት ሄደ።
ሳራ እንደምትለው በጉዳዩ ላይ አባቱን ካነጋገረው በኋላ ነው ተኩሶ የገደለው።
"አባታችንን ለማየት የፈለገው ይቅርታ እንዲጠይቀን፣ ማብራሪያ እንዲሰጠን እና ዳግመኛ እንደማይመጣ እንዲነግረን ነው" ትላለች።
"አባታችን ምን ማድረግ እንደሚችል ለመግለጽ በዚያ ቀን ለሞይ [ሞይሰስ] ብዙ ነገሮችን ነገርኩት። ዓላማዬ እንዳይሄድ ማድረግ ነበር። ግን ለማንኛውም ሄደ። እናም ያኔ ነው ሁሉም ነገር የተፈጠረው።"
ዳኛዋ ማሪያ ኖኤል ኦድሪዮዞላ በጉዳዩ ላይ ውሳኔያቸውን ባሳወቁበት ወቅት በኡራጓይ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ የተቀመጠውን ይቅርታ ከመስጠት መቆጠባቸውን ገልጸዋል።
ይህ የሕግ አንቀጽ ግድያው የተፈጸመው "በቤት ውስጥ በሚደርስ ጥቃት ምክንያት በተፈጠረ ከባድ ስቃይ" ምክንያት ከሆነ ይቅርታ መስጠትን ይፈቅዳል።
ለ15 ዓመታት ማንም ሰው ካርሎስ ማርቲኔዝን ስለፈጸመው ወንጀል ለሕግ አካል ስላላሳወቀ ዳኛዋ ቤተሰቡ "እንደ ዋና መፍትሄ ያሉትን የመከላከያ ዘዴዎች ለመጠቀም አልመረጠም" ማለታቸውን የሞይሰስ ጠበቃ ሮድሪጎ ሬይ ተናግረዋል።
የሞይሰስ ፍርድ በኡራጓይ ውስጥ መንግሥት በቤት ውስጥ ጥቃት ጉዳዮች ላይ ስላለው ሚና ሰፊ ክርክርን እና የሕዝብን ቁጣ ቀስቅሷል።
የኡራጓይ ፕሬዝዳንት ያማንዱ ኦርሲ፣ አና እና ሳራን ጠርተው እንዲያነጋግሯቸውም አድርጓል።
ሳራ ወንድሟ በተያዘበት ቀን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ስትሄድ የአባቷን አስከሬን እንዲሁም ወንድሟን እንዳላየች ተናግራለች።
"ቃላችንን እንድንሰጥ ወደ መርማሪዎች ክፍል ሲወስዱን ወንድሜን ልናየው አልቻልንም። ነገር ግን 'አሁን የምወደውን ጣፋጭ በሰላም መብላት እችላለሁ' የሚል መልዕክት ላከልኝ።"