ዌስትሃም ከአርሰናል፡ ስለአወዛጋቢው የቫር ውሳኔ የቀድሞ ተጫዋቾች እና ዳኛ ምን አሉ?

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ትልቁ የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (ቫር) ውሳኔ 4 ደቂቃ 11 ሰከንዶችን ፈጅቷል።

ይህ ውሳኔ የአርሰናልንም ሆነ የዌስት ሃምን ታሪክ ሊቀየር የሚችል ነው።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አናት እና በወራጅ ቀጠና ለሚገኙት ሁለቱ ክለቦች የውድድር ዓመቱን የሚወስንላቸው አጋጣሚ ፈጥሯል።

አርሰናል በ83ኛው ደቂቃ ሊያንድሮ ትሮሳርድ ባስቆጠረው ጎል አንድ ለምንም እየመራ ነው። የዌስት ሃሙ ካሉም ዊልሰን ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

በዚህ ወቅት ነው የመሐል ዳኛው ውሳኔው በተመለከተ በቫር ታግዘው እንዲወስኑ ሃሳብ የቀረበላቸው።

ዳኛው በአርሰናሉ ግብ ጠባቂ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በማለት ጎሉን ሽረውታል። ይህ ውሳኔ ለውዝግብ ምክንያት ሆኗል።

የቀድሞው የእንግሊዝ እና የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ዋይኒ ሩኒ ውሳኔውን "ምርጥ ውሳኔ" በማለት ገልጾታል።

"ግልጽ ጥፋት ተፈጽሟል" ብሏል የቀድሞው አጥቂው።

ውሳኔውን የሚደግፉ እና የሚነቅፉ ቢኖሩም "ግልጽ ጥፋት ተፈጽሟል። እጁ [የግብ ጠባቂውን] ፊት በመሸፈኑ ኳስ የመያዝ ዕድሉን ገድቦታል። ስለዚህ ትክክለኛ ውሳኔ ነው" ብሏል።

"ቫር ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን በመሰለው ትልቅ ጨዋታ ላይ ተገቢ ውሳኔ አስተላልፏል" ሲል አክሏል።

ሩኒ ውሳኔውን ቢያደንቅም ለግብ ጠባቂዎች የሚሰጠው ከለላ ግን እንደማያስደስተው ገልጿል።

"ወደ ግብ ጠባቂው ብትሄድ ጥፋት ነው ይባላል። በተጫዋችነት ዘመኔ በሙሉ ለግብ ጠባቂዎች ጥላቻ የነበረኝ በዚህ ምክንያት ነው። እኔ እንደማስበው (...) እጆቻቸውን ዘርግተው መዝለል ስለሚችሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ለእነሱ ነው" ብሏል።

ሌሎች ተንታኞችስ ምን አሉ?

የቀድሞው የፕሪሚየር ሊግ ረዳት ዳኛ ዳረን ካን "ማንም ሰው ከዳረን ኢንግላንድ ጋር ቦታ መለዋወጥ ይፈልጋል ብዬ አላስብም። ማንም ሰው በዚያ ወንበር ላይ መቀመጥ አይፈልግም። ቆፍጠን በማለት ትክክለኛውን ውሳኔ አስተላልፏል። ይህም በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የቫር ውሳኔ ነው።"

የቀድሞው የኒውካስል ግብ ጠባቂ ሼይ ጊቨን "በዚህ የውድድር ዘመን አርሰናል በተለያዩ ጊዜያት ግብ ጠባቂዎች እና ተከላካዮች በመከላከል ጎል ሲጸድቅ አይተናል። ሁሉም ሰው በዳኝነት ውሳኔው ወጥነት ዙሪያ ተበሳጭቷል። አንዳንድ ጎሎች እንዲጸድቁ ተደርጎ ለምንድን ነው ይኼኛው የተከለከለው?" ሲል ጠይቋል።

"ሌላው ጉዳይ ደግሞ በራያ ላይ ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ጋብርኤል፣ ኦዴጋርድ እና ትሮሳርድ ተጫዋቾችን ይዘው ነበር። ዳኛው እሱ ጥፋት ያለውን የመረጠውን እና ቀድመው የተሠሩትን ለመተው የወሰነው መቼ ነው?"

"ዌስትሃም ጎል አለመሰጠቱ ውዝግብ የፈጠረው አርሰናል ስለሆነ ነው። ባለፉት ጊዜያት ለወሰኗቸው ውሳኔዎች ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም" ያለው የቀድሞ የሊቨርፑል አማካይ ዳኒ መርፊ ነው።

"የቫር ተቆጣጣሪዎች የሚያዩትን መናገር አለባቸው እና ግልጽ የሆነ ጥፋት ነው የተፈጸመው። አርሰናል ስለሆነ ብቻ ነገሩን ማዛባት የለብንም" ብሏል

የቀድሞው የዌስትሃም ግብ ጠባቂ ሮብ ግሪን በበኩል "ጥፋት ነው። ግብ ጠባቂውን ሁለት ተጫዋቾችን ሲይዙት እያየን ነው። በዚህ የውድድር ዘመን ተመሳሳይ ነገሮች በጣም ብዙ ነበሩ" ብሏል።

"ቫር የውድድር ዘመኑ ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል።"

"በተመሳሳይ ጊዜ አምስት ወይም ስድስት ጥፋቶች ቢከሰቱም ዋናው ነገር ግን ኳሱ ያረፈበት ቦታ ነው። ከዚያ ወጥነትበተመለከተ ግን ምንም ነገር የለም" ሲል ተናግሯል።