ያለ ዕድሜ ጋብቻን ያመለጡት የሴራ ሊዮን ቀዳማዊት እመቤት

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ለንደን ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂ መሆን ምን ስሜት ይሰጣል? የሚለው ጥያቄ ለፋጢማ ባዮ ሲቀርብላቸው ትንሽ አሰብ አደረጉ።

"ከሽማግሌ ተንኳሽ ጋር ተጋብቶ ከመኖር ይሻላል" ብለው እየሳቁ መለሱ።

ተንኳሽ ሽማግሌ የሚሉትን ግለሰብ እንዲያገቡ የተወሰነው ያለ ፈቃዳቸውነው። ገና ታዳጊ ሳሉ አባቷ ለሽማግሌው ሊድሯት አሰቡ።

የአሁኑ የፋጢማ ሕይወት የታዳጊነት ዘመናቸውን አይመስልም። መጀመሪያ ተዋናይት ሆኑ። ከዚያም ለንደን ውስጥ አንድ ሰው ተዋወቁ።

በሴራ ሊዮን ያሉ ዳያስፖራዎች ስለሚፈጥሩት ተጽዕኖ ቃለ ምልልስ ሊያደርጉ ነበር የተገናኙት። ጁሊየስ ባዮ ይባላል።

ጁሊየስ እና ፋጢማ በትዳር ተጣምረዋል። ጁሊየስ ደግሞ አሁን የሴራ ሊዮን ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

ስለ ቀዳማዊት እመቤት ፋጢማ የሚቃረኑ አስተያየቶች ይሰማሉ። ወጣቶች አዲስ የፖለቲካ ድምጽ አድርገው ይወስዷቸዋል። ለሴቶች መብት የሚታገሉም ይሏቸዋል።

በሌላ በኩል በባለቤታቸው ፓርቲ ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ፣ አስተያየት የሚያበዙ ብለው የሚተቿቸውም አልታጡም።

የሕዝብ እንደራሴዎች ተቃውሟቸውን ያሰሙት ፋጢማ ላይ በመጮህ ነበር።

ፋጢማ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ አቅርበዋል ተብለውም ይታማሉ። እሳቸው ግን ግለሰቡን አላውቀውም ብለዋል።

በሴራ ሊዮን ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው እንዳይዳሩ የሚከለክል ሕግ እንዲወጣ ከፍተኛ ንቅናቄ አድርገዋል። ሕጉ የጸደቀው በአውሮፓውያኑ 2024 ነው።

ንቅናቄውን የጀመሩት ከራሳቸው ታሪክ ተነስተው ነው። 13 ዓመት ሲሞላቸው እንዲዳሩ ተወሰነ።

አባታቸው በካኖ ግዛት አልማዝ ቆፍሮ በማውጣት ነበር የሚያስተዳድራቸው።

ፋጢማ በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው እንዲያገቡ ሲወሰን ገና ልጅ ነበሩ። ሰውየውን እንደ አጎታቸው እያዩት ነበር ያደጉት።

"ጋብቻው ለውይይት የቀረበ ጉዳይ ሳይሆን በቁርጥ የተወሰነ ነበር" ይላሉ ፋጢማ።

በ1966 ፋጢማ 16 ዓመት ሞላቸው። የሠርግ ድግስ ሲጀመር ግን የእርስ በርስ ጦርነት ተነሳ። ከግርግሩ ተጠቅመው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተሰደዱ።

ካናቴራ ብቻ አድርገው በገና በዓል ዋዜማ አገራቸውን ጥለው ወጡ። ምን ያህል በርዷቸው እንደነበር ዛሬም ያስታውሳሉ። ለንደን ገብተው ከሩቅ ዘመድ ጋር መኖር ጀመሩ።

"እንግሊዝ ድንቅ አገር ናት። እንግሊዝ ስገባ ድምጼን አገኘሁ፤ ነጻነቴን አገኘሁ፤ ለራሴ መታገል ቻልኩ። አሁን ደግሞ ለብዙ ወጣቶች እታገላለሁ" ሲሉ ይገልጹታል።

በማዕከላዊ ለንደን ይኖሩበት የነበረው ቤት አሁንም ድረስ የልጆቻቸው መኖሪያ ነው።

አቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች በማኅበራዊ ማዕቀፍ ከሚሰጡ ቤቶች አንዱ ነው።

ፋጢማ ቀዳማዊት እመቤት ሆነውም ቤቱን አለመልቀቃቸው ያስተቻቸዋል።

በመዲናዋ ፍሪታውን ቅንጡ ፕሬዝዳንታዊ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። የለንደኑን ቤት በተመለከተ የሴራ ሊዮንም የእንግሊዝም መገናኛ ብዙኃን ትችት አዘል ዘገባ አውጥተዋል።

በማኅበራዊ ማዕቀፍ ቤት ለማግኘት የሚጠባበቁ ሰዎች 18,000 ደርሰዋል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ግን "ልጆቼ እንግሊዛውያን ናቸው። ለቤቱ እከፍላለሁ። የፈጸምኩት ወንጀል የለም" በማለት ይከራከራሉ።

ቤቱን የሚያስተዳድረወ ሳውዝዋክ ካውንስል ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ "ስለ ግለሰቦች ጉዳይ አስተያየት አንሰጥም። ተከራዮች ስምምነት ከጣሱ ግን ምርመራ ይደረጋል" ሲል መልሷል።

የፋጢማ ቤተሰብ ከፍሪታውን በቅርብ ርቀት የሚገኝ የእርሻ መሬት አለው። ከባለቤታቸው ጋር አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ቤት ያሳልፋሉ።

ባለቤታቸው ቀድሞ ወታደር ነበሩ። በአውሮፓውያኑ 2018 ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። በ2023ም በድጋሚ ሥልጣን ይዘዋል።

ፋጢማ ማሳ ውስጥ ሲሆኑ ቀለል ያለ መንፈስ ይታይባቸዋል። የአርሰናል ማሊያ እና ጂንስ ለብሰው ማሳውን ያስጎበኛሉ። ዶሮ እና ፍየልን ጨምሮ የተያዩ እንስሳትን ያረባሉ።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለ ሴራ ሊዮን ሲዘግቡ ታዳጊ ወታደሮች እና ደም የሚያፋስስ የአልማዝ ፍለጋ ላይ ያተኩራሉ። የቀዳማዊት እመቤቷ ሕይወት ከዚህ የተለየ ነው።

ማሳቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ በማስተዋወቅ ብዙዎችን ለማነቃቃት ይሞክራሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ገጻቸውን ይከታተላሉ።

ቀዳማዊት እመቤቷ እየደነሱ ቪድዮ ይለጥፋሉ፤ በቀጥታ ከተመልካቾቻቸው ጋርም ይነጋገራሉ።

በማኅበረሰቡ ዘንድ ለማውራት የሚያሳፍሩ የሚባሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሳሉ። ለምሳሌ በድህነት ምክንያት የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ማጣት ስለሚያስከትለው ጫና ያወራሉ።

ሴራ ሊዮን ለሴቶች ነጻ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ አታቀርብም። እንደ ኬንያ፣ ቦትስዋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ ባሉ አገራት ግን የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በነጻ ይሰጣል።

ዩኒሴፍ ባወጣው መረጃ መሠረት በሴራ ሊዮን በርካታ ሴቶች የወር አበባቸው ሲመጣ ከትምህርት ቤት ይቀራሉ።

"በወር አበባ ምክንያት ሴቶች በዓመት ውስጥ ቢያንስ 80 ቀን ከትምህርት ቤት ይቀራሉ። አንድ የትምህርት ክፍለ ዘመን ያመልጣቸዋል ማለት ነው" ይላሉ ፋጢማ።

ሴቶች እኩልነታቸው እንዳልተከበረ የሚናገሩት ቀዳማዊት እመቤቷ፤ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ነጻ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ያከፋፍላሉ።

"ሴቶች እንዲማሩ እፈልጋለሁ። ሴቶች ሲማሩ ለራሳቸው ይወስናሉ" ይላሉ ፋጢማ።

የአፍሪካ ቀዳማዊት እመቤቶች ማኅበር የፋጢማን ንቅናቄ በይፋ ይደግፋል።

በሌላ በኩል ፋጢማ "ቀዳማዊት እመቤት ማድረግ ካለባት በዘለለ" እየሠሩ ብለው የሚተቿቸውም አሉ።

የሴራ ሊዮን ገዢ ፓርቲ ኤስኤፒፒ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። የሚወዷቸውን ፖለቲከኞች በይፋ በመደገፍ ይታወቃሉ። ባለቤታቸው ባይኖሩም በተለያዩ ቦታዎች ንግግር ያደርጋሉ።

አፈ ጉባዔውን ጨምሮ በፓርቲው ያሉ ፖለቲከኞችን የሚነቅፉ ንግግሮች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ያጋራሉ።

አምና ምክር ቤቱ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ሲያደርግ የሕዝብ እንደራሴዎች ፋጢማ ላይ እየጮሁ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

የሴራ ሊዮን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የሕዝብ እንደራሴዎቹ በወሲብ ንግድ ላይ ለተሠማሩ ሴቶች የተዘፈነ አዋራጅ ሙዚቃ አዚመዋል።

ፋጢማ ሄድፎን አድርገው ሙዚቃ በመስማት የሕዝብ እንደራሴዎቹን ችላ ብለዋል። ብዙም እንዳልተበሳጩም ይናገራሉ።

"ሁሉም ወንዶች አለመማራቸውን ያሳያል። በሴቶች ብቁነት እና እኩልነት ሁሉም ወንዶች አያምኑም። ለረዥም ጊዜ የመብት ተሟጋች ነበርኩ። ሚስት ብቻ ሆኜ ለመቅረት አልፈቅድም።"

ማኅበረሰቡን በማዳመጥ ለመንግሥት ግብዓት እንደሚሰጡ ይናገራሉ። የመንግሥትን ምላሽ ደግሞ ለሕዝቡ የማድረስ ኃላፊነትን ይወጣሉ።

ፋጢማ አገራቸው የምትሣልበትን መንገድ መለወጥ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

ቾይታራም ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ ቀዳማዊት እመቤቷን የክብር እንግዳ አድርጓል።

ፋጢማ ለተማሪዎቹ ዲግሪያቸውን ሲሰጡ እያንዳንዳቸውን እያናገሩ ነበር።

ቾይታራም ከሰሃራ በታች ለሴቶች ብቻ የተሠራ የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ነው።

ቀዳማዊት እመቤት ፋጢማ ሴራ ሊዮን የሃይማኖት መቻቻል የሰፈነባት አገር እንድትሆን ይፈልጋሉ።

እሳቸው ሙስሊም ሲሆኑ ባለቤታቸው ክርስቲያን ናቸው። ጥንዶቹ መስጊድም ቤተ ክርስቲያንም እንደሚሄዱ ይናገራሉ።

ቀዳማዊት እመቤቷ ቤተ ክርስቲያን በመሄዳቸው ቅሬታ ያሰሙ አልጠፉም። የአገሪቱ 77% ዜጎች ሙስሊም፤ 21% ክርስቲያን ናቸው።

ጆስ ሊክከርስ የተባለ በአውሮፓ የሚፈለግ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ በቀዳማዊት እመቤት ፋጢማ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታይቷል የሚል ዘገባ ሮይተርስ የዜና ወኪል ያወጣው በ2025 ነው።

ፋጢማ ቤተ ክርስቲያን ሳሉ ጆስ በቅርብ ርቀት ቆሞ ይታያል። ግለሰቡ ኮኬይን በማዘዋወር በኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት በሌለበት የ24 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

ፋጢማን ያስተቻቸው ቪድዮ ከገጻቸው ጠፍቷል። ቢቢሲ ቪድዮውን በገለልተኛ ወገን አላጣራም። ግለሰቡን እንደማያውቁትም ተናግረዋል።

"ወንጀለኛ ስላልሆንኩ አላውቀውም። ክርስቲያን አይደለሁም፤ ስለዚህ ሰዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን አልወስድም። ሙስሊም ስለሆንኩ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን ሰዎች አላውቅም። እናም ስለማላውቀው ሰው ማውራት አልፈልግም።"

የፋጢማ የእንጀራ ልጅ እና ጆስ ልጅ ወልደዋል የሚለውን ጭምጭምታም ሐሰተኛ ሲሉ አስተባብለዋል።

በአውሮውያኑ 1930 የእግሊዝ ጂኦሎጂስቶች አልማዝ ማውጣታቸውን ተከትሎ ሴራ ሊዮን ሰላም ርቋታል።

ከ1991 እስከ 2002 የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት የተባባሰውም በአልማዝ ምክንያት ነው።

የላይቤሪያ የቻርልስ ታይለር ኃይሎች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲገድሉ፤ በሚሊዮኖች የሚገመቱ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

የ2014ቱ የኢቦላ ወረርሽኝ፣ የኮሮራ ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው የነዳጅ እና ምግብ ዋጋ ንረትም ሴራ ሊዮንን ይፈትናሉ።

በ2022 የኑሮ ውድነት ባስከተለው ተቃውሞ በፍሪታውን 20 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል።

የዕለት ከዕለት ኑሮን መግፋት ከባድ በሆነባት ሴራ ሊዮን የፋጢማ ቤተሰብ ሃብት ዋነኛ መነጋገሪያ ነው።

ጋምቢያን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ንብረት እንዳላቸው ቢነገርም ቀዳማዊት እመቤቷ ግን ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

"ማመንም መካድም አያስፈልገኝም። እውነትነቱን የሚመሰክር ማስረጃ ካመጡ ግን መነጋገር እንችላለን።"

ፋጢማ ለወደፊት ለፕሬዝዳንትነት ይወዳደራሉ ብለው የፖለቲካ ተንታኞች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ከ2023 ምርጫ ጋር በተያያዘ ባለቤታቸው የግልጽነት ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።

ፋጢማ በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ስለመሆን ሲጠየቁ እንደሚከተለው መልሰዋል።

"ፕሬዝዳንት ለመሆን አልጓጓም። የፈጣሪ ፈቃድ ነው። ፈጣሪ የፈለገውን ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። ፈጣሪ የሚፈልገውን ሰው አያስቆመውም።"