"ሙስሊም ነኝ፤ እንዳትተኩሱብኝ": ከሆርሙዝ መዘጋት ቀጥሎ በሶማሊያ ያገረሸው የባሕር ላይ ውንብድና

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ባለፈው የሚያዝያ በአንዱ ዕለት የምሽት ጸሎት እንደተጠነቀቀቀ፤ ሳንቲ ሳናያ ስትፈራው የነበረውን መጥፎ ዜና ያረዳት መልዕክት ወደ ስልኳ ገባ።

የኢራን ጦርነት በተፋፋመት በዚያ ወቅት ባለቤቷ የሚመራው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በመላው መካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ እያጓጓዘ ነበር።

መጋቢት 24/2018 ዓ.ም. ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተነሳው ካፒቴን አሻሪ ሳማዲኩን በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ለጥቂት ቢያመልጥም፤ በመጨረሻ ግን የባሕር ላይ ወንበዴዎች ወደሚንቀሳቀሱበት ቀጣና ገባ።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው የመርከቧ ካፒቴን በኢንዶኔዥያ ሱላዌሲ ደሴት የሚኖሩትን ቤተሰቦቹን በሚያነጋግርበት ወቅት ስጋት እንዳይገባቸው ለማድረግ ይጥር ነበር። የመንግሥትን ነዳጅ እንደጫነ በመግለጽ "እንደ ፈጣሪ ፈቃድ፤ ምንም አይፈጠርም" ይላቸው ነበር።

ሚያዝያ 13 ላይ ግን ""መርከቤ በባሕር ወንበዴዎች ጥቃት እየተፈጸመበት ነው" የሚል የድምጽ መልዕክት ወደ ባለቤቱ ላከ።

ከሶማሊያ ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ክላሽንኮቭ እና ሮኬት ማስወንጨፊያ የታጠቁ ወንበዴዎች ወደ ሞቃዲሾ እየቀዘፈች በነበረችው 'መርቸንት ታንከር ኦነር 25' የተባለች መርከብ ላይ የደፈጣ ጥቃት ፈጸሙ። የመርከቡን 17 ሠራተኞች እና ጭኖ የነበረውን 18,500 በርሜል ነዳጅ ያዙ።

ይህ የተሳካ ጠለፋ በአንድ ወቅት የአፍሪካ ቀንድን ስጋት ውስጥ ከትቶ የነበረው ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት እና በኃይል የተሞላው ውብድና ዳግም ማንሰራራቱን የሚጠቁም ክስተት ሆኗል።

ሳንቲ እንደምትናገረው የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ ወደ መርከቡ መውጣት እስከሚጀምሩ ድረስ ባለቤቷ መርከቡን አላወቀም ነበር።

አሻሪ "እባካችሁ አትተኩሱብኝ፤ ሙስሊም ነኝ" ሲል አንድ የሚያደርጋቸውን እምነት ጠቅሶ ተማጸናቸው። "ከዚያ በኋላ የመርከቧ ሠራተኞች በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ታዘዙ፣ ስልኮቻቸውም በሙሉ ተወሰዱ" ስትል ሳንቲ ትናግራለች።

ለዓመታት ጠፍቶ የነበረው በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ የሚፈጸም የባሕር ላይ ዝርፊያ በኢራን ጦርነት በተፈጠረው ቀጣናዊ አለመረጋጋት ምክንያት በድጋሚ አገርሽቷል።

ታጣቂዎቹ 'ኦነር 25' በያዙ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሲሚንቶ የጫነ 'መርቸንት ቬስል ስዋርድ' እንዲሁም የኤምሬቶች ንብረት የሆነውን ነዳጅ ጫኝ 'ዩሬካ' መርከቦችን አግተዋል።

ታጣቂዎቹ መርከቦቹን ከጠለፉም በኋላ በሶማሊያ የባሕር ወንበዴዎች መናኽሪያ ወደ ሆነችው ከፊል ራስ ገዟ የሰሜን ምሥራቅ ክልል ፑንትላንድ ወስደዋቸዋል።

ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይል ጥበቃዎች ይህንን ዓይነቱን ስጋት ካስቆሙ አሥር ዓመታት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ቡድኖች ሦስት የንግድ መርከቦችን እና ሠራተኞቻቸውን አግተዋል።

መርከቦቹ ላይ የነበሩት ባሕርተኞች ከግብፅ፣ ከሕንድ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከፓኪስታን እና ከሶሪያ የመጡ ናቸው።

ቀጣናዊ ፀረ የባሕር ላይ ውንብድና ዘመቻዎችን የሚመራው የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል "የባሕር ላይ ውንብድና ቡድኖች በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለውን ቀውስ ሕገ ወጥ ተግባራቸውን ዳግም ለመጀመር እንደ አዲስ ምቹ አጋጣሚ ወስደውት ሊሆን ይችላል" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

የሶማሊያ የባሕር ውንብድና መመለስ ለዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ "እጅግ አስከፊ" እንደሚሆን በአቴንስ ፓንቴዮን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕፅ እና የወንጀል ጽሕፈት ቤት የዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት ወንጀል ፕሮግራም አማካሪ የሆኑት ሶፊያ ጋላኒ ይናገራሉ።

"ሁቲዎች በቀይ ባሕር ከደቀኑት ስጋት እንዲሁም መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በዙሪያው ከሚያጋጥማቸው አደጋ ጋር ሲዳመር፤ ከአረቢያን ባሕር እስከ አፍሪካ ቀንድ ያለውን ቀጣና ለመንቀሳቀስ እጅግ አደገኛ ወደሆነ ካባቢ ሊቀይረው ይችላል" ሲሉ የስጋቱን መጠን አስረድተዋል።

"ይህም የኢንሹራንስ ክፍያዎችን እና የመርከብ ጉዞ ወጪዎችን ከፍ ስለሚያደርግ በመጨረሻም በምርቶች ዋጋ እና በሸማቾች ላይ ጫና ያሳድራል" ብለዋል።

የሶማሊያ የባሕር ውንብድና አነሳስ እና ውድቀት

ሠፊው የሶማሊያ የባሕር ዳርቻ እና የባሕር ውንብድና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ ውስጥ ነው።

በወቅቱ የውጭ አገር አሳ አጥማጆች በአገሬው ኅልውና ላይ ስጋት ደቅነው ነበር። ይህንን አጋጣሚ የተጠቀሙበት የወንጀል ቡድኖች ለሚያካሂዱት ጀልባዎችን የማገት እና ማስለቀቂያ የመቀበል ተግባር ከማኅበረሰቡ ድጋፍ ማግኘት ችለዋል።

የሚፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በአውሮፓውያኑ 2011 ነበር። በዚያ ዓመት ብቻ 237 ክስተቶች መመዝገባቸውን የዓለም አቀፉ የባሕር ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ ያሳያል።

በጥር 2011 የሶማሊያ የባሕር ወንበዴዎች እስከ 32 የሚደርሱ መርከቦችን እና 736 ታጋቾችን በአንድ ጊዜ ይዘው እንደነበር የአውሮፓ ባሕር ኃይል ገልጿል።

ታጋቾቹን ማስለቀቂያ የሚከፈል ከሆነ የሚገኘው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው። እንደ የዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ ከ2005 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ውስጥ 413 ሚሊዮን ዶላር የሚደረስ ማስለቀቂያ ገንዘብ ተከፍሏል።

ይህ ድርጊት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት፤ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በዓመት እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ያደርስ እንደነበር ዓለም ባንክ ግምቱን አስቀምጧል።

ኡመር ማሕሙድ በ'ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ' የሶማሊያ እና የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተንታኝ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የባሕር ውንብድና ላይ የተሰማሩ የወንጀል ቡድኖች አልጠፉም ነበር።

ይህ ዓይነቱን ተግባር ከመፈጸም "አስቆሟቸው የነበረው በባሕር መስመሮቹ ላይ ጥበቃ የሚያደርጉት የቀጣናው የባሕር ኃይሎች የሚወስዱት የኃይል እርምጃ ስጋት ነበር" ይላሉ።

በሌላ በኩል ግን "ለባሕር ውንብድናው መፈጠር ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች ባሉበት ቀጥለዋል" ሲሉ አክለዋል።

ከየመን ሁቲ ጋር ግንኙነት አላቸው?

የባሕር ላይ ውንብድናው ዳግም እያንሰራራ ስለመሆኑ ምልክቶች መታየት የጀመረው፤ ከሦስት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይሎች ትኩረታቸውን በሁቲዎች ወደሚፈጸሙት የቀይ ባሕር ጥቃቶች ባዙሩበት ወቅት ነበር።

በአሁኑ ሰዓት ሶማሊያ በመርከቦች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ብዛት ከዓለም ቀዳሚዋ አይደለችም። ቀዳሚነቱን የያዘው በአብዛኛው አነስተኛ ደረጃ ያላቸው ዝርፊያዎች የሚፈጸሙበት የሲንጋፖር ወሽመጥ ነው።

የደኅንነት ኃይሎች በመላው መካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት ውስጥ በገቡበት በአሁኑ ጊዜ፤ የባሕር ላይ ወንበዴዎች በድጋሚ ጥቃት መፈጸም ጀምረዋል። ይህ ሁኔታ የዩናይትድ ኪንግደም ማሪታይም ትሬድ ኦፕሬሽንስ የተባለው ተቋም በሶማሊያ ዙሪያ ያለውን የስጋት ደረጃ "ከፍተኛ" ወደሚል ምድብ እንዲያሳድግ አድርጎታል።

አደጋው ወደ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ እየተስፋፋ የመጣ ይመስላል። ይህም በሁቲዎች እና በባሕር ወንበዴዎቹ መካከል ትብብር ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

'ኤምቲ ዩሬካ' የተሰኘው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ሚያዝያ 24 ቀን በየመን መንግሥት ቁጥጥር ስር ቃና ከተባለ ወደብ አቅራቢያ መልሕቁን ጥሎ ባለበት ጥቃት ከተከፈተበት በኋላ ወደ ሶማሊያ ተወስዷል።

ይህ መርከብ በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች የአገሪቱን ሰሜናዊ ክፍሎች በስፋት በሚቆጣጠሩባት እና የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለችው የመን አቅራቢያ የተፈጸመ እገታ እንደሆነ በተጠረጠረ ክስተት ከተጠለፉ አራት መርከቦች አንዱ ነው።

ሰንዓ በሚገኘው 'ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ስተዲስ' የምርምር አስተባባሪ የሆኑት ያዚድ አል ጀዳዊ፤ "እነዚህ ክስተቶች ከተናጠል የባሕር ላይ የውንብድ ደርጊቶች ይልቅ ይበልጥ ሰፊ እና የተደራጀ አካሄድ አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳዩ የመጀመሪያ ደረጃ ምልክቶች አሉ" ይላሉ።

"ይህ ዓይነቱ ቅንጅት እንደነበረ ኋላ ላይ የሚረጋገጥ ከሆነ፤ ከኢራን ጋር ግንኙነት ላላቸው ተዋናዮች ወይም ለሁቲዎች የገንዘብ ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂክ ጥቅም የማስገኘት ዕድል አለው" ሲሉም ያስተዳሉ።

የባሕር ጉዞ ላይ የሚፈጠሩ ስጋቶችን ከየመን ባሻገር ማስፋፋት፣ የአሜሪካን የባሕር ኃይል በቀጣናው ያለውን አሰላለፍ ማወሳሰብ እና በኢራን ወደቦች ላይ ያለውን ጫና መቀነስ ሊገኙ ከሚችሉ ስትራቴጂክ ጥቅሞች መካከል እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።

"በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያዎች አንዱ በሆነው በዚህ መስመር አቅራቢያ የደኅንነት ክፍተቶች እንዲሁም ለሰፊ ቀውስ የሚያጋልጥ ዕድል መኖሩን የሚጠቁም ምልክት ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

"ስር የሰደዱ ችግሮች ምልክት"

በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረው አለመረጋጋት የሶማሊያ የባሕር ወንበዴዎች ድርጊታቸውን መፈጸም የሚያስችላቸው የደኅንነት ክፍተት ብቻ አይደለም፤ የችግሩ መንስኤዎችንም እያባባሰ ነው።

"የባሕር ውንብድና በምድር ላይ ያሉ እንደ አለመረጋጋት፣ ድህነት እና ደካማ መንግሥት ያሉ ጥልቅ ችግሮች ምልክት" መሆኑን የዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት ወንጀል ፕሮግራም የአካዳሚክ አማካሪ የሆኑት ሶፊያ ጋላኒ ይናገራሉ።

ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ እና የተራዘመ የእርስ በስር ጦርነት ያስተናገዱት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ቤተሰቦቻቸውን መመገብ እያቃታቸው ነው።

የኢራን ጦርነት ደግሞ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ በሆነችው አገራቸው ውስጥ ያለውን የምግብ እና የነዳጅ አቅርቦት አስተጓጉሏል። ይህም ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ በሚባል ደረጃ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አድርጓል።

በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት 'ፋሚን ኧርሊ ዋርኒንግ ሲስትምስ ኔትዎርክ' የተሰኘው የረሃብ ክስተትን የሚከታተለው ተቋም "በርካታ ደሃ ቤተሰቦች ምግብን ለማቅረብ የተፈጠረባቸውን ጉድለት ለመሙላት ሲሉ ምርት የሚሰጡ እንስሶቻቸውን ወደ መሸጥ ወይም ወደ ልመና ጭምር ሊያዘነብሉ ይችላሉ" ሲል አስጠንቅቋል።

የባሕር ላይ ውንብድና መናኸሪያ የሆነችው ፑንትላንድ አንድ የደኅንነት ባለሥልጣን፤ ዳግም እያንሰራራ ያለው ይህ ድርጊት "ብዙዎች ከሚገምቱት በላይ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ መሆኑን እና በመላው የባሕር ዳርቻ የታጠቁ ቡድኖች እንቅስቃሴ እየጨመረ" መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የባሕር ላይ ውንብድና ላይ ለረጅም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ዘመቻ ማካሄዱን" የሚገልጸው የፑንትላንድ መንግሥት በበኩሉ፤ በአገሪቱ ገጽታ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመጥቀስ፤ የዚህን ድርጊት ፈጻሚዎች ለፍርድ እንደሚያቀርብ ቃል ገብቷል።

እገታ ላይ ያለው መርከብ

የባሕር ላይ ወንበዴዎች በሚገኙባቸው መስመሮች ለመጓዝ የሚደፍሩ መርከበኞች ጥቃቶችን ለመከላከል የተቀመጡ የደኅንነት መመሪያዎችን እንዲከተሉ ይመከራሉ።

የታጠቁ ጠባቂዎችን እንዲቀጥሩ እንዲሁም መርከቦቹ ላይ መውጣትን አስቸጋሪ የሚያደርጉ መከላከያዎችን እንዲገጥሙ ይነገራቸዋል።

ካፒቴን አሻሪ ኤምቲ ኦነር 25 መርከብ ግን አንዱንም አላዘጋጀችም ነበር። የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል ያወጣቸው ምሥሎች፤ መርከቡ ዝቅተኛ ወለል እንዳለው እና ምንም ዓይነት ተጨማሪ የጥንቃቄ መከላከያዎችን ያልያዘ እንደነበር ያሳያሉ።

የመርከቡ ባለቤት የሆነው ሶማሊያዊው ኡስማን ሺሬ ቁድ "ልንጠነቀቅለት የሚገባ ምንም ዓይነት ስጋት አለ ብለን አናምንም ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በአሁኑ ጊዜ ነዳጅ የጫነው መርከብ እና ሠራተኞቹ ሊለቀቁ የሚችሉበትን ድርድር ለማድረግ ሶማሊያ እንደሚገኙ ባለቤቱ ገልጸዋል።

ነዳጅ ጫኙን መርከብ የያዙት "የአካባቢው ወጣቶች" የማስለቀቂያ ገንዘብ አልጠየቁም በማለት የሚናገሩት ኡስማን፤ "ዓላማችን ያለ ምንም አመጽ ወይም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መርከቡን በሰላማዊ መንገድ ማስለቀቅ ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አራት ኢንዶኔዥያውያን፣ 10 ፓኪስታናውያን፣ አንድ ሕንዳዊ፣ አንድ ስሪላንካዊ እና አንድ የምያንማር ዜጋ እገታ ላይ ናቸው። ይህ ክስተት በርካታ አገራት ምላሽ ለመስጠት እንዲቀናጁ አድርጓል።

የግብፅ፣ የኢንዶኔዥያ እና የፓኪስታን መንግሥታት የመርከብ ሠራተኞቹን ለማስለቀቅ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል መርከቡ ላይ የሚያደርገውን ክትትል መቀጠሉን ገልጿል። የዩናይትድ ኪንግደሙ የባሕር ትራንስፖርት ተቋም በበኩሉ እስካሁን ድረስ በተከሱት እገታዎች ውስጥ አንድም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌላ አስታውቋል።

ስለ መርከብ "እንቅስቃሴ፣ መለቀቅ ወይም ስለ ሁኔታው መባባስ የሚያመለክት የተረጋገጠ መረጃ" ግን እንደሌለ ገልጿል።