ዜሌንስኪ ሞስኮ ዩክሬንን ለማጥቃት ከሰሜን ኮሪያ ያገኘችውን ሚሳዔል እየተጠቀመች ነው ሲሉ ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ አገራቸውን ለማትቃት ከሰሜን ኮሪያ ያገኘችውን ሚሳዔል እየተጠቀመች ነው ሲሉ ከሰሱ።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ክስ ያሰሙት አገራቱ ሌሊቱን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ከቆዩ በኋላ ነው።
ዩክሬን በደቡብ ዛፖሪዝሂያ ከተማ ላይ የተፈፀመው የባሌስቲክ ሚሳዔል ጥቃት ሰባት ሰዎችን መግደሉን እና ቢያንስ 24 ሰዎችን ማቁሰሉን አስታውቃለች።
በምዕራብ ሩሲያ ቮሮኔዝ ደግሞ ትልቁ የኦንላይን መሸጫ ዋይልድቤሪ መጋዘኖች በዩክሬን ተመትተዋል። የሩሲያ አማዞን በመባል የሚታወቀው ይህ ኩባንያ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በተደጋጋሚ ዒላማ ተደርጓል።
ጥቃቶቹ የተከሰቱት፣ ከዩክሬን ድንበር ከ1,100 ኪ.ሜ. በላይ ርቀት ላይ በምትገኘው የታታርስታን ሪፐብሊክ በዩክሬን ድሮን በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሕጻንን ጨምሮ ቢያንስ 13 ሰዎች ከተገደሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ዜሌንስኪ ሰኞ ምሽት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ "ለመጀመሪያ ጊዜ" ሩሲያ "ከሰሜን ኮሪያ ድጋፍ ውጭ ጦርነት ልታውጅ አትችልም" ብለዋል።
"የሰሜን ኮሪያ ጥቃቶች እዚህ በዩክሬን፣ በአውሮፓም በጨመሩ ቁጥር ሚሳዔሎቻቸውና ወታደሮቻቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ ድክመቶቻቸውንና ክፍተቶቻቸውን የበለጠ ይሸፍናሉ" ሲሉ ዜሌንስኪ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ለተቀረው ዓለም አደጋ እንደሚፈጥር አክለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ንግግራቸውን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላቀረቡም።
ዜሌንስኪ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የዩክሬንና የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ድጋፍ እያገኘች ነው ብለው ሲከሱ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም።
የዩክሬን ጦር እንዳስታወቀው፣ ሞስኮ እአአ በየካቲት 2022 ወረራ ከፈጸመች ወዲህ ሩሲያ በርካታ የሰሜን ኮሪያ ሚሳዔሎችን ተኩሳለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቅዳሜና እሁድ እስከ 50,000 የሚደርሱ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሩሲያ ጦር ጋር ለመዋጋት እየተላኩ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በነሐሴ 2024 የዩክሬን ወታደሮችን ከኩርስክ ግዛት ለማስወጣት ወደ 11,000 የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሰማራታቸው ተገልጿል።
በጥር 2025 የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፥ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ በተካሄደው ጦርነት ወደ 40 በመቶ የሚጠጋ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ዜሌንስኪ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር በምዕራብ ሳይቤሪያ በሚገኝ የሩሲያ ፔትሮኬሚካል ፋብሪካ ላይ የዩክሬን ጦር የፈፀመውን የተሳካ የአየር ድብደባ "እጅግ ጠቃሚ ስኬት" ሲሉ አድንቀዋል።
ዩክሬን ወደ ሩሲያ ዘልቃ በመግባት ተጨማሪ ጥቃቶችን እንደምትፈጽም የዛቱት ዜሌንስኪ "ይህም ለሩሲያ እና ለሩሲያውያን ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ማሳየት አለበት" ብለዋል።
የዛፖሪዝሂያ የክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢቫን ፌዶሮቭ ተሽከርካሪዎችና ሕንፃዎች በእሳት ሲቃጠሉ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በመለጠፍ ሞስኮ ከተማዋን በሚሳዔልና ዒላማቸውን ለይተው በሚመቱ ቦምቦች መደብደቧን ተናግረዋል።
ሰባቱ ሟቾች የዩክሬን የዛፖሪዝስታል የብረታ ብረት ፋብሪካ ሠራተኞች ሲሆኑ በኋላ ላይ ፋብሪካው ስራውን አቋርጧል።
በዋና ከተማዋ ኪየቭ ላይ በተፈፀመው ጥቃት አንድ ሰው ቆስሏል። ሌሊቱን በዋና ከተማዋ ዳርቻ በተፈጸሙ ድብደባዎች የተነሳ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን እሳትም ተቀስቅሷል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት በኋላ ላይ የሕፃናት ሆስፒታል ጉዳት እንደደረሰበት አስታውቀው ነገር ግን ሠራተኞችና ታካሚዎች ወደ መጠለያ መወሰዳቸውን እና ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ተናግረዋል።
በሰሜን ምሥራቅ የዩክሬን ከተማ ሱሚ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ፈጽሞ ሁለት ሴቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሰርሂ ክሪቮሼየንኮ ተናግረዋል።
በኋላ ላይ ሩሲያ ከሰዓት ከተማዋን በቦምብ ከደበደበች በኋላ አንድ ሰው መሞቱን አስታውቀዋል።















