የአውሮፓ እግር ኳስ ኅብረት የፊፋ ዕቅድ ከጸደቀ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላለመሳተፍ ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበራት ኅብረት (ዩኢኤፍኤ) 55 አባላት፤ የፊፋ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ድርሻ ለግል ባለሀብቶች የመሸጥ ሀሳብ ተግባራዊ መሆን የሚጀምር ከሆነ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላለመሳተፍ ወሰኑ።
አባል አገራቱ ውሳኔውን ያስተላለፉት የዓለም እግር ኳስን የሚመራው ፊፋ፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ይፋ ያደረገው አዲስ እቅድ ላይ ለመወያየት በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው።
የሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ እግር ኳስን የሚያስተዳድረው እንዲሁም የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ያስናገደው ኮንካካፍም በተመሳሳይ ሐሙስ ዕለት ስብሰባ አካሂዶ ነበር። በስብሰባውም የኮንፌዴሬሽኑ 41 አባላት በፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የቀረበውን እቅድ "ውድቅ" ማድረጋቸውን አስታውቋል።
ምንጮች እንደሚገልጹት የኮንካፍ አባል የሆኑ አገራት በፊፋ ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ ላይ እምነት እያጡ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ኢንፋንቲኖ ያቀረቡት ዕቅድ፣ ፊፋ የዓለም ዋንጫን ጨምሮ የሚያዘጋጃቸው ዋና ዋና ውድድሮችን የሚመራ የንግድ ድርጅት እንዲቋቋም የሚያደርግ ነው። የውጭ ባለሀብቶችም የዚህን ድርጅት ድርሻዎች መግዛት ይችላሉ።
በፕሬዝዳንቱ እቅድ መሠረት "ሦስተኛ ወገን" ባለሀብቶች 'ፊፋ ፎርዋርድ ኢንተርፕራይዝ' የሚል ስያሜ ይሰጠዋል የተባለው ድርጅት ውስጥ እንዲገዙ የሚጋበዙት "አነስተኛ እና ተቆጣጣሪነት እንዲኖራቸው የማያደርጉ" ድርሻዎችን ነው።
የአውሮፓ እግር ኳንስ የሚያስተዳድረው ዩኤፍኤ ከአስቸኳይ ስብሰባውም አስቀድሞ ሁለት ጠንካራ መግለጫዎችን በማውጣት ተቃውሞውን ግልጽ አድርጓል። በአስቸኳይ ስብሰባውም ይህንን አቋም አጽንቷል።
የአውሮፓው የእግር ኳስ ማህበራት ኅብረት ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ "ዓለም ዋንጫ እንደ የኢንቨስትመንት ምርት ሊያዝ አይችልም" ብሏል።
"ከእግር ኳስ ግዙፍ ስፖርታዊ አሻራዎች አንዱ ነው። በተጨዋቾች፣ በብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም በመላው አህጉሩ በሚገኙ ደጋፊዎች አማካኝነት ትውልዶችን በፈጀ ጊዜ የተገነባ ነው። የትኛውም አካሉ በግል ባለሀብቶች እጅ መሆ ንየለበትም። ዓለም ዋንጫ ለሽያጭ አይቀርብም" ሲልም አቋሙን አስረግጧል።
የዩኤፋ አድማውን የሚያደርገው የወንዶች እና የሴቶች የዓለም ዋንጫዎች እንዲሁም የክለቦች ዓለም ዋንጫን ጨምሮ በሀሉም የፊፋ ውድድሮች ላይ ነው። የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ያቀረቡት እቅድ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አባላት ድምጽ የሚሰጥ ከሆነ ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል።
የአውሮፓው እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ይህንን ውሳኔው ተፈጸሚ የመሆኑ ጉዳይ የሚታየው በመጪው ጥቅምት በሚካሄደው የሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ነው።
በፊፋ ፕሬዝዳንት ቀረበው እቅድ ተግባራዊ ለመሆን ለፊፋ 211 አባላት ቀርቦ መጽደቅ አለበት። ኢንፋንቲኖ ይህንን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸው 106 የድጋፍ ድምጽ ነው።
አሁን ተቃውሟቸውን ያሰሙት ዩኤፍኤ እና ኮንካፍ በድምሩ 96 አባላትን ይዘዋል፤ የሚሰጡትም የተቃውሞ ድምጽ እንደሆነ ይጠበቃል።
ኢንፋንቲኖ ለፊፋ አባላት በጻፉት ደብዳቤ ይህን አወዛጋቢ እቅድ የደገፉ አገራት 40 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።
እስከ መስከረም 8/2019 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እቅዱን የሚበቀሉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች መጀመሪያውን 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኙም አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ረቡዕ ዕለት እቅዳቸው ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ለመከላከል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ እቅዱ "ግዴታ አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።















