በባሕረ ሰላጤው አገራት የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ለእስር የሚዳርጉት እና ከአገር የሚያስባርሩት ለምንድን ነው?

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ከሁለት ወር በፊት እስራኤል እና አሜሪካ ቴህራን ላይ ጦርነት ሲከፍቱ የባሕረ ሰላጤው አገራት ለብሔራዊ ደኅንነታቸው አደጋ ናቸው የተባሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘቶችን የሚያጋሩ ሰዎችን እንደሚያስሩ፣ እንደሚከስሱ እና ከአገር እንደሚያባርሩ ይፋ አደረጉ።

አገራት አዳዲስ ሕጎችን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ይግባኝ የሚባልበት መንገድን ገደቡ፤ እንዲሁም ነባር ሕጎችን በመጠቀም ዜግነትን እስከ መንጠቅ የሚደርስ እርምጃዎችን ወሰዱ።

ባህሬን የ69 ሰዎችን ዜግነት ከነጠቀች በኋላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ "የኢራንን ጠብ አጫሪ ድርጊት አጉልተው ያሳዩ፣ ድጋፋቸውን የገለጹ እና ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት የፈጠሩ ግለሰቦች የባህሬን ዜግነት ተነጥቋል" ሲል አስታውቋል።

የጸጥታ ኃይሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን እና እንቅስቃሴያቸው ላይ የሚያደርጉትን ክትትል አጠናክረዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እርምጃዎቹ ሃሳብን በነጻነት መግለጽን የሚጋፉ ናቸው ሲሉ ኮንነዋቸዋል።

በባህሬን እና ኩዌት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ከተለያየ የሕይወት መስክ የተገኙ ናቸው።

ጋዜጠኞች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና መደበኛ ነዋሪዎች ይገኙበታል።

አገራቱ የቀረቡት ክሶች የሃይማኖት ግጭትን በማነሳሳት፣ የሐሰት ዜናዎችን በማሰራጨት፣ የሞባይል ስልኮችን አላግባብ መጠቀም እና ሌሎች የአገሪቱን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች ላይ በመሳተፍ መሆናቸውን ይዘረዝራሉ።

በርካታ የባህረ ሰላጤው አገራት በግጭቱ መጀመሪያ ኢራን የሰነዘረችባቸው ጥቃቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ወይም መረጃዎችን መቅረጽ እና ማተምን ከልክለዋል።

በባህሬን እና ኩዌት ቤተሰቦቻቸው የታሰሩባቸው ሰዎች ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት ይከለከላሉ፣ ወይም ዜግነታቸውን ይነጠቃሉ የሚል ፍራቻ አላቸው።

ይህ የሆነው በኩዌት አዲስ የዜግነት ሕግ ተግባራዊ ከተደረገ እና በቅርቡ በባህሬን የወጣውን ንጉሣዊ ድንጋጌን ተከትሎ ነው።

አንድ በስም እንዳይጠቀሱ የጠየቁ የኩዌት አክቲቪስት፣ ባለሥልጣናት በጦርነት ጊዜ የኦንላይን እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክቲቪስቱ ይህ በአንዳንድ መንገዶች ላይ በሚገኙ የደህንነት ፍተሻዎች መንገደኞችን በማስቆም የሞባይል ስልኮቻቸውን መፈተሽ፣ የተለዋወጧቸውን የጽሑፍ፣ የድምጽ መልዕክቶች፣ ያነሷቸውን ፎቶዎችን መመልከትን ያካትታል።

ኩዌት በነጻ ያሰናበተችው ጋዜጠኛ ሺሃብ ኢልዲን

ኩዌት 135 ሰዎችን የማኅበራዊ ሚዲያን አላግባብ መጠቀምን በሚል በቁጥጥር ስር አውላ ምርመራ ስታደርግ ከቆየች በኋላ እአአ ሚያዝያ 23 2026 የኩዌት የደኅንነት ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጥቷል።

ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች አስራ ሰባት ተከሳሾች የሦስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። በውጭ አገር የሚኖር አንድ ተከሳሽ በሌለበት በድምሩ የ10 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

ፍርድ ቤቱ 109 ተከሳሾች ላይ ቅጣት ባይጥልም የተወሰኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸውን እንዲሰርዙ አዟል። ሌሎች ዘጠኝ ደግሞ በነፃ ተሰናብተዋል።

ሁሉም በሃይማኖት መካከል ግጭትን ማነሳሳት እና የሐሰት ዜና በማሰራጨት ተከስሰው ነበር።

ፍርድ ቤቱ በነጻ ካሰናበታቸው ሰዎች መካከል በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ በኩዌት የሚገኙ ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ በሄደበት የታሰረው የኩዌት እና አሜሪካ ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ አህመድ ሺሃብ-ኤልዲን ይገኝበታል።

ጋዜጠኛው በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያሸነፈ እና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ድርጅቶች ዘገባዎችን የሠራ ነው። ሺሃብ ኤልዲን ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት፣ ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ በመጣል እና የሞባይል ስልክን አላግባብ በመጠቀም ክስ እንደተመሰረተበት ተናግሯል።

ከኩዌት ውጭ የሚኖሩት እህቶቹ ላራ እና ሉማ የሕግ አማካሪ የሆኑት ካውሊፍዮን ጋላገር "አህመድ ከ52 ቀናት እስር በኋላ ከተከሰሰባቸው ክሶች ሁሉ ነጻ በመውጣቱ ደስ ብሎናል" ብለዋል።

'ዜግነቴ ይነጠቃል' ብሎ መፍራት

በመጋቢት ወር ኩዌት ሠራዊቱን የሚያጣጥል ወይም "ሆን ተብሎ በጦሩ ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽር" ይዘት የሚያሰራጩ አካላት ከ16,250 እስከ 32,500 ዶላር የሚደርስ የገንዘብ እንዲሁም ከሦስት እስከ አስር ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የሚደነግግ ሕግ አውጥታለች።

መንግሥት ለብሔራዊ ደኅንነት እና ሽብርተኝነት ለመከላከል ልዩ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋሙንም አስታውቋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አባል የሆኑት ማህሙድ ሻላቢ እርምጃዎቹ ባለሙያዎች ራሳቸውን በስፋት ሳንሱር እንዲያደርጉ ማስገደዱን እንዲሁም ገለልተኛ የሆነ ጋዜጠኝነትን ፈታኝ ማድረጉን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ዘመዱ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ታስሮ የነበረው የኩዌት ዜጋ አነጋግሯል።

ግለሰቡ የታሰረው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራቸው፣ አስተየየቱን በሰጠባቸው ወይም በወደዳቸው (ላይክ ባደረጋቸው) ነገሮች ምክንያት እንደሆነ አብራርቷል። ከእነዚህም መካከል በኻሜኒ ግድያ የተሰማውን ሐዘን የሚገልጹ ጽሁፎች እንደሚገኙበት ጠቅሷል።

ማንነቱ እንዲገለጽ ፈቃደኛ ያልሆነው ይህ የኩዌት ዜጋ፣ አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ከሺዓ ማኅበረሰብ የመጡ መሆናቸውን ገልጿል። ይህም በእርሱ አመለካከት ብዙ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስተያየታቸውን ከመስጠታቸው በፊት ሁለቴ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

እንደዚህ ግለሰብ ገለጻ ከሆነ አንዳንድ እስረኞች፣ ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ፣ ወደ ኩዌት ማዕከላዊ እስር ቤት ተዛውረዋል።

ዜግነታቸው የሌላ አገር የሆነ እስረኞች ደግሞ ወዲያውኑ ከአገር ለማባረር በኢራን ጦርነት ምክንያት የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራቸውን በማቆማቸው ወደ ጊዜያዊ ማቆያ ስፍራዎች ተዛውረዋል ብሏል።

የኩዌት ዜጋ የሆነው እና ለቢቢሲ መረጃዎችን የሰጠው ይህ ግለሰብ የአንዳንድ ታሳሪዎች ጠበቆች ደንበኞቻቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጣቸው ዜግነታቸው ሊሰረዝ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግሯል።

በኩዌት አዲሱ የዜግነት ሕግ አንቀጽ 13 የመንግሥትን ደህንነት፣ ፈጣሪን ወይም አሚሩን መሳደብ እንዲሁም ለአገሪቱ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ ወይም የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ጎጂ የሆኑ ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ የተገኘ እና ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ ዜግነት ሊሰረዝ ይችላል።

አንቀጽ 14 ደግሞ አንድ ሰው ከኩዌት ጋር ጦርነት ውስጥ ላለ አገር ወይም የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶቿን ካቋረጠችባቸው አገራት ጋር የሚሰራ ወይንም የሚደግፍ ከሆነ ዜግነቱ እንዲሰረዝ ይደረጋል።

ቢቢሲ የኩዌት ባለሥልጣናትን ግለሰቦቹ ስለታሰሩበት ሁኔታ እና ለእስር ስላበቃቸው ምክንያቶች ለመጠየቅ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ምንም ምላሽ አላገኘም።

የ69 ሰዎችን ዜግነት የሰረዘችው ባህሬን

በባሕሬን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉባቸው ክሶች ኩዌት ግለሰቦችን ካሰረችባቸው ምክንያቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው በሁለቱም አገራት የሚገኙ በርካታ ታሳሪዎች የመናገር ነጻነታቸውን በመጠቀም ባጋሯቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ምክንያት "የሐሰት ዜናዎችን" በማሰራጨት ወይም ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ባለመጠቀም የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የድርጅቱ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ተመራማሪ ማህሙድ ሻላቢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፍትህ ሂደቱ ላይ "ከባድ ስጋት" አላቸው።

"በባህሬን አንዳንድ ታሳሪዎች ጠበቃ እንዳያገኙ ተከልክለዋል" ያሉት ተመራማሪው፣ በቅርቡ በኩዌት የተደረጉት የሕግ ለውጦች "በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ አንድ የይግባኝ ደረጃን ሙሉ በሙሉ አስወግዷል" ብለዋል።

የባሕሬን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እአአ ሚያዝያ 27 "የኢራንን ጠብ አጫሪ ድርጊት አጉልተው ያሳዩ፣ ድጋፋቸውን የገለጹ እና ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት የፈጠሩ" 69 ሰዎች ዜግነት መሰረዙን አስታውቋል።

ባለሥልጣናቱ ሁሉም የባሕሬን የዘር ግንድ የሌላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ዜግነቶቹ የተሻሩት በንጉሥ ሃማድ ቢን ኢሳ አል ካሊፋ በወጡ መመሪያዎች እና በባሕሬን የዜግነት ሕግ አንቀጽ 10 ላይ በመመስረት ነው ብሏል።

ሕጎቹ "የመንግሥቱን ጥቅም የሚጎዱ" ወይም ለመንግሥት ታማኝ የመሆን ግዴታን የሚቃረኑ ድርጊቶች ላይ መሳተፋቸው የሚጠረጠር ግለሰቦች ዜግነትን መንጠቅ ይፈቅዳል።

በባሕሬን የመብቶች እና የዲሞክራሲ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሰይድ አህመድ አልዋዳኢ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት እርምጃውን "ለትውልድ የሚዘልቅ አደገኛ የጭቆና ዘመን መጀመሪያ" ሲሉ ገልጸውታል።

ባሕሬን በወንጀል ድርጊቶች ላይ ተሳትፈዋል ያለቻቸው ተከሳሾች

ሂዩማን ራይትስ ዎች በባሕሬን የኢራን ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የሚሳተፉ፣ ጦርነቱ በመቃወም አስተያየቶችን የሚሰጡ ወይም በኦንላየን ተያያዥ መረጃዎችን የሚያጋሩ ግለሰቦች ላይ የሚደረጉ አፈናዎችን መጨመራቸውን ገልጿል።

አንድ የባሕሬን አክቲቪስት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሴቶችን፣ ታዳጊዎችን እና የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ወደ 304 የሚጠጉ ሰዎች ታስረዋል። አንዳንዶቹ ከአገር እንዲባረሩ ሲደረግ ሌሎቹ ደግሞ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል ብለዋል።

ቢቢሲ ባሕሬን ይህንን ቁጥር እንድታረጋግጥ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

እንደ አክቲቪስቱ ገለጻ ክሶቹ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ከውጭ አካላት ጋር መገናኘት፣ መረጃ መላክ ወይም መተባበር እና ሐሰተኛ ዜናዎችን ማሰራጨት የሚሉ ናቸው።

የባሕሬን ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስሮቹ የተፈጸሙት በወንጀል ድርጊቶች ላይ ተሳትፈው በተገኙ ላይ ብቻ ነው።

የባሕሬን የመንግሥት ቃል አቀባይ ደኅንነትንና መረጋጋትን ለመጠበቅ እና "ግልጽ የሆነ የኢራን ጥቃት" ለመጋፈጥ በሚደረገው ጥረት በርካታ ግለሰቦች በባሕሬን ሕግ መሠረት ወንጀል መፈጸማቸው በመጠርጠሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ቃል አቀባዩ "ሽብርተኛ" ሲሉ ከጠሩት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር በመገናኘታቸው፣ እንዲሁም "ለኢራን ጥቃት እና ለሽብር ህዋሶቿ ድጋፍ በመስጠት"፣ የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃዎችን በኦንላየን በማሰራጨት መሆኑ ተጠቅሷል።

በኢራን ጦርነት ወቅት የባሕረ ሰላጤው አገራት መንግሥታት ጥቃት ለመፈጸም እያቀዱ ነው ወይንም አለመረጋጋትን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል በሚል የተጠረጠሩ ቡድኖች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

አንዳንዶቹ እንደ ባለሥልጣናቱ ገለጻ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ሌሎቹ ደግሞ ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተገለጹ ናቸው።