ከ600 በላይ እስረኞች በይቅርታ ሲለቀቁ 28 ይቅርታ ባለመጠየቃቸው ሳይፈቱ ቀሩ

መፈታታቸው ከተነገሩት መካከል አቶ ክርስቲያን ታደረለ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ዶ/ር ጫኔ ከበደ
የምስሉ መግለጫ, መፈታታቸው ከተነገሩት መካከል አቶ ክርስቲያን ታደረለ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ዶ/ር ጫኔ ከበደ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች በከባድ ወንጀሎች ተከስሰው በፌደራል መንግሥቱ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ ከስድስት መቶ በላይ ሰዎች በይቅርታ መፈታታቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በተመሳሳይ ክስ ለዓመታት በእስር ላይ የቆዩ ነገር ግን ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ያልሆኑ 28 እስረኞች ደግሞ ሳይፈቱ ቀርተዋል።

በ2019 ዓ.ም. አዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜ 5/2018 ዓ.ም. ከእስር መፈታታቸው የተነገረው በመቶዎች የሚቆጠሩ ታሳሪዎች ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው በይቅርታ፣ ክሳቸው በሂደት ላይ የነበረው ደግሞ እንዲቋረጥ ተደርጎ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ለአዲሱ ዓመት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላይ ልዩ ልዩ ወገኖች "በአንድም ሆነ በሌላ ስህተት የታሠሩ ወገኖች በይቅርታ እና በሕግ አግባብ እንዲፈቱ" መጠየቃቸውን እና መንግሥትም ተቀብሎ "በሂደቱ የተስማሙትን ፈትቷል" ብለዋል።

ኢሰመኮ እንዳለው የተለቀቁት ሰዎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ በሽብር እና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ተከሰው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠባቸው እንዲሁም በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ነበሩ።

ታሳሪዎቹ "ጉዳያቸው በልዩ ሁኔታ እንዲታይ. . . በኮሚሽኑ በኩል ለመንግሥት እንዲቀርብላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ" በማድረግ ኢሰመኮ ታሳሪዎቹ በሕግ ሂደት ይቅርታ እንዲገያኙ ጉዳዩን ለመንግሥት አቅርቦ ምላሽ ማግኘቱን ገልጿል።

በዚህም በክስ ሂደት ላይ የነበሩት ታሳሪዎች "በራሳቸው ፍላጎት ያቀረቡትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ" ኮሚሽኑ ጥያቄ ለመንግሥት አቅርቦ አዎንታ ምላሽ በማግኘቱ ከወራት ሂደት በኋላ ከ600 በላይ እስረኞች ለመለቀቅ መብቃታቸውን አስታውቋል።

በፌዴራል ደረጃ ከተለቀቁት ውስጥ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ዶ/ር ጫኔ ከበደ እንደሚገኙበት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በመግለጫቸው ወቅት ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተገናኘ ተመሳሳይ የሽብር ክስ የቀረበባቸው እነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አምስቱን ጋዜጠኞች ጨምሮ በኢሰመኮ በኩል የቀረበውን የይቅርታ ሰነድ ያልፈረሙ ተከሳሾችን እንዲሁም የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ በተፈቱት ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ስለመኖር አለመኖራቸው ቢቢሲ ማጣራት እያደረገ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከእስር ስለመለቀቃቸው ዛሬ ይፋ ያደረጋቸው ግለሰቦች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለው እንደሆነ ለማወቅም እየሞከርን ነው።

በዓመቱ የመጨረሻ ዕለት ከእስር መለቀቃቸው የተነገረው ግለሰቦች በዚሁ በሕግ እና በይቅርታ አሠራር ሂደት በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸው በይቅርታ፤ ጉዳያቻው በክስ ሂደት ላይ የነበሩ ተከሳሾች በቅድመ ሁኔታ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲወጡ መደረጉ ተጠቅሷል።

በታሳሪዎቹ ጥያቄ መሠረት ከአዲሱ ዓመት ጋር በማያያዝ መንግሥት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ከ600 በላይ የተፈረደባቸው እና ጉዳየቻው በሂደት ላይ የነበረ ሰዎች ከእስር ተለቀዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የነበሩ እና የይቅርታ ጥያቄ ያላቀረቡ 28 ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል።

የሕዝብ ተወካዮችን እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በተለያዩ መዝገቦች የሽብር ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾች፣ ይቅርታ ጠይቀው ክሳቸው እንዲቋረጥ እና ከእስር እንዲለቀቁ በመንግሥት ለቀረበላቸው ጥያቄ የተለያየ ምላሽ መስጠታቸውን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

ከሦስት ዓመት በላይ በእስር ላይ የቆዩት የሽብር ወንጀል ተከሳሾች፣ ይቅርታ ጠይቀው ከእስር እንዲለቀቁ የሚጠይቀው ሰነድ የደረሳቸው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አማካኝነት ነበር።

ከተከሳሾች መካከል አብዛኞቹ የቀረበላቸውን የይቅርታ መጠየቂያ ሰነድ ሲፈርሙ ቅድመ ሁኔታውን አንቀበልም በማለት ካልፈረሙት መካከል ፖለቲከኛ እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ቢቢሲ ተረድቷል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበው ክስ፣ በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ በተፈፀሙ የሰዎች ግድያዎች፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት እንዲሁም በሌሎችም የሽብር ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚዘረዝር ነው።

የይቅርታ መጠየቂያ ሰነዱ፣ በየክስ መዝገባቸው በሽብር የቀረቡባቸውን ወንጀል አምነው ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚጠይቅ ይዘት ያለው ስለመሆኑ ቢቢሲ ከተከሳሾቹ ቤተሰቦች እና ጠበቆች በወቅቱ ተረድቷል።

በዚህም መሠረት ተከሳሾቹ የተጠቀሱትን ወንጀሎች ስለመፈፀማቸው አምነው፣ ዳግመኛ የእንደዚህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ ላለመሳተፍ ቃል እንዲገቡ እና ተሳትፈው የሚገኙ ከሆነ ደግሞ መንግሥት "አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድባቸው" እንዲስማሙም ሰነዱ ይጠይቃል።