ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከትራምፕ ዛቻ በኋላ የቡድን 7 አገራት ከክምችታቸው 100 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እና ናፍጣ ሊለቁ ነው
የቡድን ሰባት አገራት የዋጋ ንረት ያስከተለውን የአቅርቦት ችግርን ለማቃለል 100 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እና ናፍጣ እንደሚለቅቁ አስታወቁ።
የቡድን ሰባት መሪዎች በሰጡት መግለጫ፣ ይህ በ20 ቀናት ውስጥ የሚለቀቀውን ነጭ ናፍጣ የሚያካትት ሲሆን "አስፈላጊ ከሆነ ተጨማሪ ናፍጣ ለመልቀቅ ውይይት ይደረጋል" ብለዋል።
አሜሪካን ጨምሮ የላቀ ምጣኔ ሃብት ያላቸው የቡድኑ አባል አገራት፣ እርምጃው ወዲያውኑ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር እና ለአራት ወራት ያህል እንደሚቆይ ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ነዳጅ ወደ ውጪ እንዳይላክ እገዳ እንደሚጥሉ ካስፈራሩ በኋላ በተላለፈው ውሳኔ መሠረትም በቡድን ሰባት አባል አገራት መካከል ኢነርጂን እና የኢነርጂ ውጤቶችን ወደ ውጪ መላክ የሚከለክል ምንም ዓይነት ገደብ አይኖርም ተብሏል።
ቡድን ሰባት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ጣልያን እና ፈረንሳይን የሚይዝ ሲሆን አውሮፓ ኅብረትም በስብሰባዎቹ ተወክሏል።
ትራምፕ ቀደም ብሎ የአውሮፓ አገራት ከክምችታቸው ነዳጅ ወደ ገበያ ለመልቀቅ ካልተስማሙ ከአሜሪካ ናፍጣ ወደ ውጪ እንዳይላክ እንደሚያግዱ አስጠንቅቀው ነበር።
ይህንን ተከትሎ የቡድን ሰባት አገራት ከነዳጅ ክምችታቸው ወደ ገበያ ለመልቀቅ መስማማታቸው በመጪው ወር ከሚካሄደው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ አስቀድሞ ለአሜሪካ ሸማቾች የዋጋ ንረትን እንደሚያቃልል ተገልጿል።
ትራምፕ አርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ " አውሮፓውያን ከነጭ ናፍጣ ክምችታቸው በብዛት ለመልቀቅ ተስማምተዋል፤ ሒደቱም ወዲያውኑ ይጀምራል" ብለዋል።
የግምጃ ቤት ኃላፊው ስኮት ቢሴንትም ቀደም ብለው በዋጋ ንረቱ "የአሜሪካ አርሶ አደሮች ፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና የንግድ ተቋማት ጫናውን መሸከም የለባቸውም" ሲሉ አሳስበው ነበር።
ትራምፕ በኋላ ላይ በዋይት ሃውስ በተናገሩበት ወቅት ግን "ነጭ ናፍጣ ወደ ውጭ የመላክ እገዳ ጠረጴዛ ላይ አልነበረም" ብለዋል።
ቡድን ሰባት ከክምችቱ ነዳጅ ለመልቀቅ ያሳለፈውን ውሳኔ በመጥቀስም ፤ "አውሮፓ ያደረገው በጣም ትልቅ ነገር ነው" ሲሉ ውሳኔውን አድንቀዋል።
"አውሮፓ ብዙ ነጭ ናፍጣ አለው፤ ለዓለም ትልቁን አስተዋፅኦ ያደረጋል፤ እኛም እንደዚያው" ያሉት ትራምፕ ከአሜሪካ ነዳጅ እንዳይላክ እንደማያግዱ አስታውቀዋል። " ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን" ብለዋል።
ትራምፕ ነጭ ናፍጣ ወደ ውጭ እንዳይላክ እገዳ እንደሚጥሉ ያስታወቁት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሲሆን አስተዳደራቸው አውሮፓ ከክምችቱ እንዲለቅ ጫና ሲያደርግ ቆይቷል።
ውሳኔው የተላለፈበትን ስብሰባ የመሩት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፣ ኅብረቱ በዓለም አቀፍ የኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኢኤ) ትብብር ሥር "እስከ 100 ሚሊዮን በርሜል" የሚደርስ ክምችት በአራት ወራት ውስጥ ለመልቀቅ መስማማቱን" ተናግረዋል።
ሆኖም የትኞቹ አገራት እንደሚለቅቁ እንዲሁም በምን ያህል ፍጥነት እንደሚለቅቁ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ነጭ ናፍጣ በተለይ በትራንስፖርት ኢንደስትሪው እና በግብርናው ዘርፍ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን የዋጋው ንረት ምግብን ጨምሮ በተለያዩ ወሳኝ ፍጆታዎች ላይ የዋጋ ጭማሪን አስከትሏል።
ግማሽ የሚሆነው የዩኬ ናፍጣ ከውጭ የሚገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 31 በመቶ የሚሆነው ከአሜሪካ የሚላክ ነው።
በውሳኔው አሜሪካ ለመጣል ስታስፈራራ የነበረውን እገዳ ማስቀረት መቻሉም ዩኬን ጨምሮ ከውጪ በሚመጣ ነዳጅ ላይ ጥገኛ ለሆኑ አገራት እፎይታን የሚሰጥ ነው ተብሏል።
አሜሪካ በዓለማችን ከፍተኛው ነጭ ናፍጣ ከሚያቀርቡ አገራት መካከል አንዷ ናት። እንደ የአሜሪካ ኢነርጂ ኢንፎርሜሽን አስተዳደር መረጃ ከሆነ በአገር ውስጥ ያላት ማጣሪያ በየቀኑ ከአራት እስከ አምስት ሚሊዮን በርሜል ያመርታል።
ከዚህ ውስጥ 3.6 ሚሊዮኑን አሜሪካውያን የሚጠቀሙበት ሲሆን የነዳጅ አጣሪዎች በቀን ከ1.2 እስከ 1.5 ሚሊዮን በርሜል ናፍጣ ወደ ውጪ ይልካሉ። ይህም አሜሪካን በዓለም ገበያ ወሳኝ አቅራቢ አድርጓታል።
ዋነኛ የነዳጅ አምራች የሆነችው ሩሲያ በነዳጅ ማጣሪያዎቿ ላይ በዩክሬን የተፈፀመባትን ጥቃት ተከትሎ ነጭ ናፍጣን ወደ ውጭ እንዳይላክ አግዳለች። ይህም የአቅርቦት እጥረቱን አባብሶታል።
ነጭ ናፍጣ ከቤንዚን የበለጠ ለማጣራት አስቸጋሪ ቢሆንም ፣ በትራንስፖርት ኢንደስትሪው እና በግብርናው ዘርፍ ጥቅም ላይ ስለሚውል ፍላጎትን መቀነስ አስቸጋሪ ነው።