የማንችስተር ሲቲ የፕሪሚየር ሊግ ተቀናቃኞች ባለቤቶቹ ክለቡን ለመሸጥ እንዲገደዱ ጠየቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የማንችስተር ሲቲ ባለቤቶች የፋይናንስ ሕጎችን በመጣሳቸው እንደቅጣት ክለቡን ለመሸጥ ሊገደዱ ይገባል ሲሉ በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ስፖርት ተናገሩ።

በዚህ ሳምንት የገለልተኛው የእግር ኳስ ተቆጣጣሪ ተቋም ሊቀመንበር ዴቪድ ኮጋን፣ ማንችስተር ሲቲን በተመለከተ እርምጃ ለመውሰድ "የሚያስፈልገው ድፍረት እና ቁርጠኝነት አለኝ" ብለዋል። ክለቡ ግን የቀረበበትን ክስ አስተባብሎ ይግባኝ ጠይቋል።

ተቆጣጣሪው አካል የአንድ ክለብ ዳይሬክተሮች ለሥራው ተስማሚ አይደሉም ተብለው ከተገመገሙ ከኃላፊነታቸው የማንሳት እና ጉዳዩ እጅግ ከባድ ከሆነ ደግሞ ክለቡ እንዲሸጥ እስከማስገደድ የሚደርስ ሥልጣን አለው።

አሁን ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ ያሉ ሦስት ተፎካካሪ ክለቦች ከፍተኛ ኃላፊዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ይህ ቅጣት ለማንችስተር ሲቲ ተገቢ የሆነ እርምጃ ነው ብለው ያምናሉ።

ማንችስተር ሲቲ ከአውሮፓውያኑ 2009 እስከ 2018 ድረስ የፕሪሚየር ሊጉን የፋይናንስ ደንቦች ጥሷል በሚል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል፤ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ሲደረግ ከነበረው ምርመራ ጋር በቂ ትብብር እንዳላደረገ ተገልጿል።

ክለቡ "ሐሰተኛ" የንግድ ውሎችን በመጠቀም 900 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ እንዳለው በማስመሰል እና ኪሳራውን በመደበቅ ጥፋተኛ ተብሏል።

የማንችስተር ሲቲ ባለቤት አቡ ዳቢ ዩናይትድ ግሩፕ ሲሆን፣ ይህም የዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ማንሱር ንብረት የሆነ የግል ኢንቨስትመንት ኩባንያ ነው።

ገለልተኛው ኮሚሽን በማንችስተር ሲቲ ላይ ምን ዓይነት ቅጣት እንደሚጣል ገና አልወሰነም። ሊጣሉ ከሚችሉት ቅጣቶች መካከል የገንዘብ መቀጮ፣ ነጥብ መቀነስ፣ ቀደም ሲል ያሸነፋቸውን ዋንጫዎች መሰረዝ ወይም ከሊጉ ማባረር ጭምር ይገኙበታል።

ነገር ግን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የክለብ ኃላፊ እንደሚያምኑት የማንችስተር ሲቲ ባለቤቶች ክለቡን እንዲሸጡ ካልተገደዱ ማንኛውም ቅጣት ትርጉም አይኖረውም ብለዋል።

እንዲሁም ከዚያ ያነሰ እርምጃ ከተወሰደ፣ የእግር ኳስ ተቆጣጣሪው ተቋም ላይ ጥያቄ እንደሚያነሳም ገልጸዋል።

በሲቲ ተፎካካሪ ክለቦች ዘንድ ያለውን ቁጣ ከሚያሳዩ አስተያየቶች ውስጥ፣ የፋይናንስ ሕግ ጥሰቶቹ የፕሪሚየር ሊጉን ተዓማኒነት እንዳበላሹ አንድ ኃላፊ ገልጸዋል። ባለቤቶቹ በቦታቸው እንዲቆዩ ከተፈቀደላቸው ደግሞ ጉዳዩን ዘግተው ወደፊት መሄድ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ሌላ የፕሪሚየር ሊጉ ቡድን ኃላፊ እንዳሉት፣ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ስለ ቅጣቱ በይፋ አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠቡ እና ሂደቱ እንስኪጠናቀቅ እንዲጠብቁ ጠይቋል። ሆኖም አንዳንድ ክለቦች አስተያየታቸውን በግል ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣናት እንዳቀረቡ ይነገራል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች ክለቦች አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ነገር ግን አንዳንድ ክለቦች ክለቡ በግድ እንዲሸጥ የሚያስገድድ ከዚህ ቀደም ተፈጽሞ የማያውቅ ቅጣት መጠየቃቸው፣ ተቆጣጣሪው ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በላይ ሳይሆነው ከፍተኛውን ቅጣት እንዲጥል ጫና ሊፈጠርበት ይችላል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በብሪታንያ ውስጥ ያሉ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በእንዲህ ዓይነት እርምጃ ሊጎዱ ይችላሉ የሚለው ስጋት እየጠነከረ ነው።

ባለፈው መስከረም ወር ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም፣ ይህ ጉዳይ የሲቲ ባለቤቶች ክለቡን እንዲሸጡ የሚያደርግ ከሆነ "በጣም እንደሚያሳስባቸው" በመናገራቸው ተተችተው ነበር።

ተቆጣጣሪው አካል በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ሆኖም ኮጋን ተቋሙ በምንም ዓይነት የፖለቲካ ጫና እንደማዳከም በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ሊቀ መንበሩ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለፓርላማ ኮሚቴ ሲናገሩ፣ የይግባኙ ሂደት ውጤት ምን እንደሚሆን በመመልከት ተቆጣጣሪው አካል የሲቲን አመራር ለመመርመር ወይም እርምጃ ለመውሰድ እንደማይፈራ ገልጸዋል።

"የክለቡን ስም እርሱ፣ የክለቡን መጠን እርሱ፣ የጉዳዩን ስፋት እርሱ። አንድ ክለብ ትልቅ ነው ብለን ብቻ በሕግ የተጣለብንን ግዴታ ችላ ልንለው አንችልም" ብለዋል።

"ለእኛ በሚቀርቡት ሁኔታዎች፣ ማለትም በፕሪሚየር ሊጉ ገለልተኛ ኮሚሽን በተሰበሰቡ ማስረጃዎች እና በይግባኙ ሂደት በሚሰጠው ፍርድ መሠረት፣ ሕጉ የሚያዘውን ተገቢ እርምጃ በእርግጠኝነት እንወስዳለን።"

"ነገር ግን በአንድ አቅጣጫ ሲታይ፣ እነዚህ ጉዳዮች ጥፋተኛ ተብለው ስለተወሰኑ ማስረጃዎቹ አስቀድመው ተመዝነዋል። ስለዚህ ይህን ለማድረግ በእርግጥ ድፍረቱ አለን።...እነዚያ ሁኔታዎች ከተሟሉ እኛ እርምጃ ካልወሰድን የእግር ኳስ ተቆጣጣሪ መኖሩ ምን ፋይዳ አለው?" ብለዋል።

የገለልተኛው የእግር ኳስ ተቆጣጣሪ አካል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሪቻርድ ሞንክስ፣ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ሊኖሩ የሚችሉ የሕግ ጉዳዮች ወጪ እንዴት እንደሚሸፈን በፓርላማ አባላት በተጠየቁ ጊዜ፣ በክለቦች ላይ በሚጣለው ክፍያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 2 ሚሊዮን ፓውንድ የሕግ ክርክር መጠባበቂያ ገንዘብ እንደሚሰበሰብ ተናግረው፤ ጉዳዩ ከተጠናቀቀ በኋላ ገንዘቡ በወጪ መልክ እንደሚመለስም አስረድተዋል።

"በግልጽ ሁኔታ፣ አንድን የተወሰነ ጉዳይ ሳልጠቅስ፣ ለማንኛውም ክለብ የተያዘ ትልቅ የሕግ ክርክር ሊኖር ይችላል፤ ይህም ከ2 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሕግ ወጪ እና በተለይም የጠበቆች ወጪ እንድናወጣ ሊያስገድደን ይችላል" ብለዋል ሞንክስ።

"ይህ ከተፈጠረ ከመንግሥት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ መንግሥት በጥሬ ገንዘብ ረገድ ብድር ይሰጠናል።

"ያንን የሕግ ክርክር እንደምናሸንፍ እና ወጪዎቻችንን እንደምናስመልስ እንጠብቃለን፤ ከዚያም የመንግሥትን ገንዘብ እንመልሳለን። ነገር ግን ያን ትልቅ ክርክር ብንሸነፍ፣ ወጪው በመጨረሻ በክለቦች ላይ በሚጣለው ክፍያ ላይ ይጨመራል፤ መንግሥትንም በዚያ መንገድ እንከፍላለን" ሲሉ አክለዋል።

ባለፈው ወር፣ ተቆጣጠሪው አካል በእንግሊዝ የወንዶች እግር ኳስ ከፍተኛዎቹ አምስት ዲቪዥኖች ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን በየዓመቱ ከ20 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ እንደሚያስወጣ ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች፣ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በተያያዘ ከየትኛውም የሲቲ ስፖንሰር አድርጊ ክስ ቢቀርብባቸው ለአምስቱ የቦርድ ዳይሬክተሮች የሕግ ወጪያቸውን ለመሸፈን ተስማምተው ድምፅ ሰጥተዋል።

የሲቲ ሁለት የንግድ አጋሮች የሆኑት ኢቲሃድ እና ኢቲሳላት በበኩላቸው በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሕግ እርምጃ ለመውሰድ እያሰቡ እንደሆነ ገልጸዋል።

ተቆጣጣሪው አካል በተሰጠው የሕግ ሥልጣን መሠረት አንድ ክለብ እንዲሸጥ ለማስገደድ ሥልጣን አለው። ይህም አንድ የክለብ ባለቤት ከታማኝነት፣ ከሥነ ምግባር እና ከፋይናንስ ጥንካሬ አንፃር የሚጠበቁትን መስፈርቶች ያሟላ እንደሆነ እንዲመረመር ያስችለዋል።

አንድ ባለቤት ይህን ግምገማ ካላለፈ፣ ተቆጣጣሪው በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ባለቤትነቱን ለመልቀቅ ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ ሊያዝ ይችላል፤ ከዚያም ከባለቤትነት የማስለቀቂያ ትዕዛዝ ሊያወጣ ይችላል።

ማንችስተር ሲቲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።

ከዚህ በፊት ግን ክለቡ የኮሚሽኑ ውሳኔ "ግልጽ የሆኑ የሕግ፣ የመርኅ እና የእውነታ ስህተቶችን የያዘ እና አስተማማኝ ያልሆነ" ነው ብሏል።

በተጨማሪም ክለቡ፣ "ለሁሉም አቋሞቻችን ድጋፍ የሚሰጥ እርግጠኛ እና የማይካድ ማስረጃ በሰፊው አቅርበናል" ሲል ገልጿል።