ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለባድመ ቅርብ በሆኑ የድንበር አካባቢዎች ከረቡዕ ጀምሮ ውጊያ መካሄዱን ነዋሪዎች ተናገሩ
ከኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙት ገምሃሎ እና ናፍራ በተባሉ አካባቢዎች ከረቡዕ እና ሐሙስ ዕለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል ውጊያ መካሄዱን ነዋሪዎች ተናገሩ።
የትጥቅ ግጭቶችን ቦታ እና ኹነት የሚከታተለው "አክሌድ"፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትናንት ሐሙስ ጓል ገምሃሎን እንደተቆጣጠረ እንዲሁም ይበልጥ ወደ ድንበር እየተጠጋ መሆኑን ገልጿል።
ገምሃሎ ከሽራሮ አልፎ እና ከባድመ በፊት የሚገኝ ለኤርትራ ድንበር የቀረበ አካባቢ ነው። መስከረም ላይ ተጀምሮ በፍጥነት ከዋና ዋና ከተማዎች የራቀው የትግራይ ክልል ግጭት፣ በድንበር አካባቢዎች በሚካሄዱ ውጊያዎች ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት የወጡ ሪፖርቶች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኤርትራ ጦር ወታደሮቻቸውን በድንበር አካባቢዎች እያሰፈሩ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
የኤርትራ ሠራዊት "በርካታ ወታደሮችን እና ከባድ መሣሪያዎችን" ካሰማራባቸው ስፍራዎች አንዱ ጓል ገምሃሎ እንደሆነ አክሌድ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መረጃ አመልክቶ ነበር።
ረቡዕ ኅዳር 16 እና ሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. በገምሃሎ ውጊያ የተካሄደው በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሚመሩት የትግራይ ኃይሎች መካከል እንደሆነ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ኤርትራ ወታደሮች የመከላከያ ግንባር ፈጥረውበት ነበር ከተባለው ከዚህ ስፍራ ስለመውጣታቸው ግልፅ አልሆነም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት፣ መከላከያ ሠራዊት ማክሰኞ ሌሊት በባድመ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኘው ይህ አካባቢ ገብቷል። ይህንን ተከትሎም ከማግሥቱ ረቡዕ ኅዳር 16 ጠዋት አንስቶ ውጊያ መካሄዱን ገልጸዋል።
የትግራይ ኃይሎች "ላለፉት ሁለት ሳምንት ገደማ" ገመሃሎ ውስጥ እንደነበሩ የሚናገሩ አንድ ነዋሪ፣ "[ረቡዕ] ከሦስት ሰዓት በኋላ እስከ 12 ሰዓት ነው ውጊያ የተፈጠረው። ከባድ መሳሪያ ወደ እኛ አሁን እየተወነጨፈ እየመጣ ነው" ብለዋል።
አራት ልጆች አባት የሆኑት ነዋሪ፣ በውጊያው ምክንያት ሙሉ ቤተሰባቸው ከስፍራው መሸሹን ተናግረዋል።
የስምንት ወር ልጇን ይዛ ወደ ጫካ መሸሿን የምትናገር ሌላ የገምሃሎ ነዋሪ ደግሞ፣ "[ረቡዕ] ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ተጀመረ። የአየር ድብደባ ከባድ እና ቀላል መሳሪያ ሲተኮስ ነበር። ከዚያ ወደ በረሃ ወጣን። ሲተኮስ እንጂ ሠራዊት በዐይናችን አላየንም። ተኩሱ እስከ ዛሬ ጠዋት አለ" ስትል ትናንት ሐሙስ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ አረስድታለች።
ውጊያው ከመቀስቀሱ አስቀድሞ በስፍራው የትግራይ ኃይሎችን ስትመለከት እንደነበር የምትናገረው ነዋሪ፣ "ውጊያው እየተካሄደ መመለስ ፈራን። ጥቂት ቀናት አይተነው ተረጋግቶ ከሰነበተ ወደ ሽራሮ ለመሄድ እያሰብን ነው" ብላለች።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአቅራቢያው የሚገኘው ሌላኛው የድንበር አካባቢ 'ቢያራ' ነዋሪ በበኩላቸው፣ ከረቡዕ ንጋት ጀምሮ በናፍራ አቅጣጫ የከባድ መሣሪያ ድምፅ እንደሚሰማ ገልጸዋል።
ግጭቶችን የሚከታተለከው አክሌድ ባወጣው መረጃ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና አጋሩ የሆነው የትግራይ ሰላም ኃይል ለባድመ ቅርብ የሆነውን ጓል ገምሃሎን "ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን" አስታውቋል።
እንደአክሌድ ገለጻ፣ ፌደራል መንግሥት የድንበር መንደሩን የተቆጣጠረው ከረቡዕ ምሽት አንስቶ በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በከባድ መሣሪያ የታገዘ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጓል ገምሃሎን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ይበልጥ ወደ ድንበር ወደሚጠጉት "ገዛ ተጋሩ እና ሰምበል አቅጣጫ መንቀሳቀስ መቀጠሉን" የሚያመለክት መረጃ መኖሩን አክሌድ በድረ ገጹ አስፍሯል።
እስካሁን ድረስ በድንበር አካባቢዎች በሚደረጉት ውጊያዎች የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን የሚያመለክት ግልፅ መረጃ አልተገኘም። ይሁን እንጂ በአካባቢው የሚታየው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት ሊገቡ ይችላሉ የሚለውን ስጋት አባብሶታል።
ትናንት ሐሙስ ኅዳር 17/2019 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የኤርትራ መንግሥት አማጺያን ያስታጥቃል የሚል ክስ አቅርበው፣ "ሻዕቢያ በማይታረም ስህተት ውስጥ የሚዳክር ኃይል ከሆነ ጥፋቱ ለኤርትራ ነው የሚሆነው" የሚል ማስጠንቀቂያም ሰጥተዋል።
"የኢትዮጵያ ጠላት ማስታጠቅ፣ ማስታጠቂያ መስመር መሆን፣ የኢትዮጵያ ጠላቶችን መተባበር አቁሙ" በማለት የኤርትራ መንግሥትን አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በቀይ ባሕር ላይ ማግኘት የሚፈልገውን የባሕር በር ለማሳካት "ውጊያ አያስፈልግም" ያሉት ዐቢይ፣ "ውጊያ ካለስ? ምንም ጥርጥር የለውም ኢትዮጵያ አሸናፊ ናት። አንድ አይደለም 'እደመራለሁ' የሚል ኃይል ካለም እኛ አሸናፊዎች ነን፤ ለዚያ ነው የምንዘጋጀው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ለኢትዮጵያ ታጣቂዎች ድጋፍ ያደርጋል በሚል የሚቀርብበትን ክስ የማይቀበለው ኤርትራ መንግሥትም በበኩሉ፣ ኢትዮጵያ "ሉዓላዊ የባሕር በር" በማግኘት ስም ወረራ የመፈጸም ዕቅድ አላት በማለት ይከሳል።
በቅርቡ በኤርትራ ከሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች እና የቀጣና ዳይሬክተሮች ጋር የተወያዩት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል ይህንን ክስ በድጋሚ አቅርበዋል።
"ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ሰፊ የወረራ ጦርነት ለመክፈት መዘጋጀቷ ለክርክር ወይም ለመላምት የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም" ሲሉ በኤርትራ ቤተ መንግሥት ለተሰበሰቡት የተመድ ተወካዮች ተናግረዋል።
የባሕር በር "በጦርነት ለማግኘት ወሰነችው" ኢትዮጵያ፣ "እስከ ዳህላክ ደሴቶች ድረስ ያለውን መላውን የኤርትራ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ የመጠቅለል" ፍላጎት አላት በማለት ከስሰዋል።
"ኢትዮጵያ ያወጀችውን የወረራ ጦርነት አቃለን ልንወስደው አንችልም። ችግሩ በራሱ ጊዜ እንዲጠፋ ተስፋ በማድረግ እንደ ሰጎን አንገታችንን አሸዋ ውስጥ ልንቀብርም አንችልም" ማለታቸውን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ላለፉት ዓመታት በክስ እና በወታደራዊ ዝግጅት ላይ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዳግም ወደ ግጭት ይገባሉ የሚል ስጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ሠራዊቷ በኤርትራ ይደገፋሉ ከምትላቸው ከህወሓት ኃይሎች ጋር በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ወደ ግጭት ከገባ በኋላ አብዛኛውን የትግራይ አካባቢዎች በመቆጣጠር ግጭቱ ከኤርትራ ጋር ወደሚዋሰኑ አካባቢዎች ደርሷል።
ይህም የሁለቱ አገራት ወታደሮች ወደ ግልጽ ጦርነት እንዲገቡ በር ሊከፍት ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።