ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ሻዕቢያ በማይታረም ስህተት ውስጥ የሚዳክር ከሆነ ጥፋቱ ለኤርትራ ነው የሚሆነው" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ "ሻቢያ በማይታረም ስህተት ውስጥ የሚዳክር ኃይል ከሆነ ጥፋቱ ለኤርትራ ነው የሚሆነው" ሲሉ ዛሬ ሐሙስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር አስጠነቀቁ።
ኤርትራ መንግሥት፣ "የኢትዮጵያ ጠላትን ማስታጠቅ" እንዲሁም "ለኢትዮጵያ ጠላቶች መተባበር" እንዲያቆምም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ለማግኘት በኤርትራ ላይ "ወረራ እንደማትፈጽም" የገለጹት ዐቢይ፣ ውጊያ የሚጀመር ከሆነ ግን "አንድ አይደለም እደመራለሁ የሚል ኃይል ካለም እኛ አሸናፊዎች ነን" ብለዋል።
ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 17/2019 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝነተው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡቸላው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከምትገኘው ጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንዱ ኤርትራን የተመለከተ ነበር። ጋሻው ዳኘው የተባሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ ኤርትራ መንግሥት "ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ" በኢትዮጵያ ላይ "አፍራሽ እና አሉታዊ" አቋም ሲከተል መቆየቱን ገልጸዋል።
"የኢትዮጵያን ሰላም እና መረጋጋት ለማወክ" እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተውም፣ "የኢትዮጵያ ሰላም እና ደኅንነት የሚፈታተኑ ድርጊቶችንስ እስከ መቼ እንታገሳለን?" የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
በፓርላማው ውሎ የመጀመሪያው አጋማሽ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ከሰላም፣ ከደኅንነት እና ከዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን ባነሱበት ከእረፍት በኋላ የተደረገ የስብሰባው ክፍል ነው።
ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ስምምነት የተፈጠረበትን ጊዜ አንስተው፣ "የኤርትራ መንግሥት ከተደበቀበት ወጥቶ ከማያውቅበት በራሳችን አውሮፕላን ሳውዝ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኬንያ እየወሰድን ጎረቤት ጋር አገናኝተናል" ብለዋል።
ከኤርትራ ጋር "አብረን ለመልማት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል" ሲሉ የተደመጡት ዐቢይ፣ አገሪቱ መንግሥት ፈቃደኛ እንዳልነበረ በማንሳት ወቅሰዋል። "የኤርትራ መንግሥት ለጊዜው መንግሥት ነው። ግን የልማት፣ የእድገት የሚባል...ቋንቋው ውስጥ የለም። አይገባቸውም ልማት፣ መንገድ እንሥራ፣ ድልድይ እንሥራ አይገባቸውም" ብለዋል።
ከኤርትራ መንግሥት ጋር መቃቃሩ የተባባሰው በፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ምክንያት መሆኑን በድጋሚ አንስተዋል። አሁን ደግሞ ከመስከረም ጀምሮ ከፌደራል መንግሥት ጋር ዳግም ግጭት ውስጥ የገቡት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች "ኤርትራ ገብተዋል" የሚል ክስ አቅርበዋል።
"ያቆረቆዘው ኃይል የትግራይን ትንሿን ሀብት በመኪና ጭኖ ደግሞ ኤርትራ ገባ" ሲሉ ከ800 በላይ ተሽከርካሪዎች ወደ ኤርትራ ተወስደዋል በሚል በክልሉ ባለአደራ አስተዳደር የቀረበውን ክስ አጠናክረዋል።
የኤራትራ መንግሥት እና የህወሓት አመራሮች ከዚህ ቀደም ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ በሰጡት ምላሽ፣ የትግራይ ኃይሎች ወደ ሰሜናዊቷ ጎረቤት አገር ተሻግረዋል የሚለው ክስ ውድቅ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ መንግሥታቸው ከኤርትራ አቻው ሁለት ጉዳዮችን ማግኘት እንደሚፈልግ በዛሬው ንግግራቸው ጠቅሰዋል። "አንድ፣ የኢትዮጵያ ጠላት ማስታጠቅ፣ ማስታጠቂያ መስመር መሆን፣ ለኢትዮጵያ ጠላቶች መተባበር አቁሙ" ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፅ መንግሥት በኤርትራ በኩል የትግራይ ኃይሎችን እያስታጠቀ መሆኑን የሚገልፅ ክስ አቅርቦ ነበር። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጥቅምት ላይ ባደረጉት ንግግር የትግራይ ኃይሎች "በምፅዋ ወደብ የተላለፈላቸውን የአንድ መጠነኛ አገር የመከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል የጦር መሣሪያ" መማረኩን ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጠቀሱት ሁለተኛው ጉዳይ "በሁሉም መስክ ለጋራ ልማት አብረን እንሥራ" የሚል ነው። "አብረን ስንሠራ ሃሳቡን፣ ገንዘቡን፣ ጉልበቱን እኛ እናዋጣለን። ተባባሪ ብቻ ሁኑ እናንተ። ከእናንተ ገንዘብ አንጠብቅም፤ ሃሳብ አንጠብቅም። ይሄን ማድረግ ከቻላችሁ በሰላም አብሮ መኖር ይቻላል" ብለዋል።
እነዚህ ሁለት የኢትዮጵ ያ ፍላጎቶችን ማሳካት የማይቻል ከሆነ ግን "ጥፋት" እንደሚከተል አስጠንቀቅዋል። "ነገር ግን ሻዕቢያ በማይታረም ስህተት ውስጥ የሚዳክር ኃይል ከሆነ ጥፋቱ ለኤርትራ ነው የሚሆነው" ብለዋል።
ዐቢይ ቀጥለው፣ ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዓመታት በይፋ ስትገልፅ ከቆየችው በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ጋር በተያያዘ "ኤርትራን ልትወር ነው" የሚል ስጋት እንደሚነሳ ጠቅሰዋል።
" 'ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ብላ ወረራ ታካሂዳለች' [ይባላል]፤ አናካሂድም ወረራ። ወረራ አያስፈልግም፤ በሰላም በንግግር ነው የምንፈልገው" ብለዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ማገድ እንደማይቻል የሚጠቁም ገለጻ ሰጥተዋል።
"ኢትዮጵያ ካላደገች፣ ኢትዮጵያ ሰላም ካልሆነች ሰላም መሆን የሚችል ቀጣና እና አፍሪካ አይኖርም። ትልቅ ሕዝብ ነን፤ የእኛ መታወክ ብዙ ያውካል። ትልቅ ዛፍ ስለሆን ከጸናን ጥላችን ሰፈሩን ያዳርሳል፤ ግንዳችን ከተጎዳ ግን ሁሉም ይጎዳል ማለት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር አግኝተዋል ያሏቸውን እንደ ዮርዳኖስ፣ ኢራቅ፣ ፖላንድ በምሳሌነት የጠቀሱት ዐቢይ፣ "ይሄ ነው ተግባራዊ ማድረግ እንጂ ጦርነት አያስፈልግም" በማለት አክለዋል።
"መዝረፍ አንፈልግም፣ መቀማት አንፈልግም፣ ሰጥቶ መቀበል መርህ እንድናድግ እና ከእኛ ጋር እደጉ ነው፤ እኛ አድገን እናንተ ተራቡ አይደለም ጉዳዩ። ይሄንን ጉዳይ ለማወሳሰብ ብዙ አይነት ቁማሮች ይነገራሉ" ብለዋል።
እንደ ዐቢይ ገለጻ፣ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ በአየር ክልል በኩል የሚደረግ ጉዞ ጋር የተያያዘ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በስም ያልጠቀሷቸው አገራት "በምድርም በሰማይም" ኢትዮጵያን "መዝጋት እንደሚያስቡ" ጠቅሰዋል።
"በምድርም በሰማይም ተዘግተን ሰላም የሚሆን አፍሪካ፣ ሰላም የሚሆን ቀጠና ግን ህልም ነው እሱ" ብለዋል። ቀይ ባሕር እጥረት የሌለበት ሀብት መሆኑን አንስተውም፣ "ተስማምተን በሕግ አግባብ መሥራት እንችላለን" የሚል አቋማቸውን ገልጸዋል።
"እኛ የቀይ ባሕር አክሰስ ስናገኝ ኤርትራን የምንጎዳ ከሆነ ትክክል አይደለም። ኤርትራ ግን 30 ዓመት ዞር ብላ ያላየችውን፣ አንድ ኪሎ ሜትር አስፋልት ያልሠራችበትን ሰፈር አሁን 'አትጠቀሙበት' ብትል ብዙ ጥቅም የለውም። እነሱም ይጠቀሙ እኛም እንጠቀም በጋራ እንደግ" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "አይ፣ ኢትዮጵያ አያስፈልጋትም፣ እንትን እኮ ነው፣ ምናምን እኮ ነው የሚባል ንግግር ግን፣ በምድርም በሰማይም ተዘግተን ከምናልቅ" ብለው ንግግራቸውን ሲገቱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጭብጨባ ተችሯቸዋል።
ጦርነት የሚጀመር ከሆነ፣ "የሚያግዝህ የለም፤ ራስህ ነህ የምትሸከመው" ሲሉ የተደመጡት ዐቢይ፣ "ወደ ጥፋት መሄድ ስለማንፈልግ በጥሞና ማሰብ ያስፈልጋል፣ በጋራ ማደግ ያስፈልጋል፣ ውጊያ አያስፈልግም" በማለት ተናግረዋል።
"ውጊያ ካለስ? ምንም ጥርጥር የለውም ኢትዮጵያ አሸናፊ ናት። አንድ አይደለም 'እደመራለሁ' የሚል ኃይል ካለም እኛ አሸናፊዎች ነን፤ ለዚያ ነው የምንዘጋጀው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ "ሉዓላዊ የባሕር በር" በማግኘት ስም ወረራ ልትፈጽም እንደምታስብ በመግለጽ በተደጋጋሚ ከስሳለች።
ዐቢይ ይህንን ንግግር ያሰሙት መስከረም ላይ ያገረሸው የትግራይ ክልል ግጭት ተስፋፍቶ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ይገባል የሚል ስጋት በተፈጠረበት ወቅት ነው። ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል።
ከህወሓት ኃይሎች ጋር ግጭት በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልል ዋና ዋና ከተሞችን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ውጊያው ወደ ኤርትራ የድንበር አካባቢዎች አተኩሯል።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ አዋሳኝ በሆኑ የድንበር አካባቢዎች ሁለቱም አገራት ወታደሮቻቸውን ማስፈራቸውን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ እና ግጭቶችን የሚከታተለው 'አክሌድ' ባለፈው ሳምንት አሳውቀዋል። ይህ ሁኔታ ሁለቱ አገራትን ወደ መጠነ ሠፊ ጦርነት ሊያስገባቸው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች ወረራ ፈጽመዋል የሚል ክስ ተባበሩት መንግሥታት አቅርቦ ነበር። ነዋሪዎችም በወቅቱ የኤርትራ ወታደሮች ወደ አዲግራት አቅጣጫ በሚገኙ ትግራይ ክልል ገብተው እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል።
ኤርትራ ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች። በምላሹም ኢትዮጵያ ወረራ ልትፈጽምባት እንደሆነ በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት በጻፈችው ደብዳቤ ከስሳለች።