"ቢፈለግም ባይፈለግም በቀጣናው ታላቅ ወንድም ነን" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "ቢፈለግም ባይፈለግም" ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ "ታላቅ ወንድም" መሆኗን እንዲሁም መከላከያ ሠራዊቷን እያስታጠቀች ያለችው ቀጣናውን "አሁን ከሚታየው የተዘራረቀ ሁኔታ ለመከላከል" ጭምር መሆኑን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "በቅርቡ ያጋጠሙ አንዳንድ ውጊያዎችን" የመራበት መንገድ "በየትኛውም መስፈርት" ዘመናዊ ሊባል የሚችል እንደሆነ በመግለጽ አሞካሽተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬ ሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሏቸው፣ ባለፉት ዓመታት የመከላከያ ሠራዊቱ አቅም በከፍተኛ መጠን እየተገነባ መሆኑን ማሳያዎች በመጥቀስ አብራርተዋል።

ሠራዊቱ እየተገነባ ያለው፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመከላከል እንደሆነም አስረድተዋል።

"ተቋሙ የሚገነባው ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ ቀጠናችን ዳካማ (ፍራጃይል) ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ለቀጠናችን ታላቅ ወንድም ነን፤ ቢፈለግም ባይፈለግም ታላቅ ወንድም ነን በኢኮኖሚም፣ በአገር ስፋትም፣ በሰው ብዛትም" ሲሉ ተናግረዋል።

ዐቢይ፣ ደኅነንት ተግዳሮቶች ተጋላጭ እንደሆነ የገለጹት የአፍሪካ ቀንድ፣ "ችግር ሲገጥመው፣ ወንድሞቻችንን ለማገዝ በሚያስችል ደረጃ" መከላከያ ሠራዊት "ዝግጅት እያደረገ" መሆኑን አንስተዋል።

"ችግሩ ያለው "ወንድሞቻችን 'አጋዥ፣ ተከላካይ ተቋም ነው' ከሚል ይልቅ 'ሊያጠቃን ይችላል' የሚለው ስጋት አልፎ አልፎ ሲበረታ ይታያል" ሲሉም ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሩሲያ የተረከበቻቸውን ሱ 35 ተዋጊ ጄቶች ጉዳይ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቅምት ለሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ወደ ሞስኮ በተጓዙበት ወቅት ዘመናዊ የሚባሉትን 12 ሱ-35 የጦር ጄቶች መረከባቸውን ገልጸው ነበር።

ዐቢይ ዛሬ በፓርላማ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በአራተኛ እና በአምስተኛ ትውልድ ተዋጊ ጄቶች መካከል የሚገኙን ዘመናዊዎቹ ሱ 35 ጄቶች መታጠቋን የተቃወሙ አካላት "የአሜሪካ ኮንግረስ ማዕቀብ እንዲጥል" ጥያቄ አቅርበዋል። የትኛዎቹ አካላት ይህንን ጥረት እንዳደረጉ ግን አላብራሩም።

"እኛ የታጠቅነው ኢትዮጵያን እና ቀጣናውን አሁን ከሚታየው የተዘራረቀ ሁኔታ ለመከላከል ነው። ማንንም የማጥቃት ፍላጎት የለንም" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።

ዐቢይ እንደሚናገሩት፣ መከላከያ ሠራዊት እነዚህን "ተዋጊ አውሮፕላኖች እና የአየር መከላከያ ስርዓቶች" እየታጠቀ ያለው ከሌሎች አገራት መንግሥታት ብቻ ሳይሆን "ከአሸባሪዎች" ጭምር የሚመጣ ስጋትን ለመመከት ነው።

"በርቀት ማጥቃት ለመንግሥታት ብቻ ሳይሆን ለአሸባሪዎችም ቀላል ተግባር እየሆነ ስለመጣ፣ አንድ ሰው፣ አንድ ቡድን ተነስቶ ሊያጠቃን ቢፈልግ ራሳችንን ለመከላከል ወይም አንድ ጎረቤት አገር ቢጠቃ ድጋፍ ለመስጠት እንደዚህ ያለው አቅም ያስፈልጋል" ብለዋል።

እንደ ዐቢይ ገለጻ፣ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት "ትልቅ ኢኮኖሚ" የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በቀጣናውም ትልቁ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ነው።

አክለውም፣ "በምዕራቡም፣ በምስራቁም ያሉ ኃያላን አገራት እንዲገነዘቡ የሚያስፈልገው፣ ኢትዮጵያ ራሷን የምትቆጥረው እንደ ታላቅ ወንድም ነው ለአካባቢ ሰላም" ብለዋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እና በኮሪያ የሠላም ማስከበር ሠራዊት ማሰማራቷን በአስረጅነት ጠቅሰዋል።

"የምንዘጋጀው ለመከከላል (ዲተር)፣ የመከላከል ብቃት እንዲኖር ከመፈለግ ብቻ ነው፤ ከዛ ያለፈ መሻት የለም" ያሉት ዐቢይ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት መጠንከሩ ለሌሎች አገራት ስጋት እንዳልሆነ ገልጸዋል።

"መከላከያ መጠንከሩ 'ለወንድሞቻችን ስጋት ነው ወይ?' ካላችሁ በፍጹም አይደለም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም አገር ወርራ አታውቅም፤ ዛሬም አይደለም፤ በታሪኳ፣ ወደፊትም ያ ፍላጎት የላትም" ብለዋል።

ቀጥለውም ግን በኢትዮጵያ ላይ ይህን አይነቱን ድርጊት መፈጸም የሚፈልግ አካል እንዳይኖር አስጠንቅቀዋል።

"ሌሎች ማወቅ ያለባቸው ግን ትንሽም ይሁን ትልቅ ማንም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መጥቶ ኢትዮጵያን ወርሮ በክብር መመለስ አይችልም" በማለት ሲናገሩ ከፓርላማ አባላት የድጋፍ ጭብጨባ ተችሯቸዋል።

"ይሄ በጂኦግራፊ የታጠረ ጉዳይ አይደለም፤ ማንም ነው ያልኩት ማንም። አድዋ ይደገማል አትሞክሩን አንፈልጋችሁም። ከተመጣ ግን ወደዚህ የሚመጣ ካለ ግን ያው የተለመደው የአባቶቻችን ተግባር ይደገማል ማለት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዐቢይ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በቅርቡ የተደረጉ ውጊያዎች ላይ አሳይቶታል ያሉትን ብቃት አድንቀዋል።

"መከላከያ፣ በቅርቡ ያጋጠሙንን አንዳንድ ውጊያዎች የመራበት መንገድ በየትኛውም መስፈርት እጅግ ዘመናዊ የሚባል የውጊያ የአምስተኛ ትውልድ የውጊያ (ፊፍዝ ጀነሬሽን ዎርፌር) ባህሪ የተላበሰ ነው" ብለዋል።

"ቀድሞ የጠላት ዒላማ ማወቅ፣ የጠላት ዒላማ ማየት፣ ጠላት የማድረግ አቅሙ እንዲኮታኮት ከማድረግ አንጻር የነበረው ብቃት በጣም በጣም የሚመሰገን ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።