በትግራይ ከእስር አምልጦ በአንድ ወር ውስጥ አምስት ሴቶችን የገደለው ተጠርጣሪ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ሸረ ከተማ ከዓመታት በፊት በአንዲት ሴት ግድያ ተከሶ የ22 ዓመት እስራት የተፈረደበት ግለሰብ፣ ከእስር ከወጣ በኋላ አምስት ሴቶችን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመግደል መጠርጠሩን የሰሜን ምዕራብ ዞን ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ገብረሥላሴ አማረ ተናገሩ።

የ54 ዓመቱ ተጠርጣሪ ተስፋይ ገብረዮሐንስ አምስቱንም ሴቶች ከገደለ በኋላ በሟቾቹ ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደፈጸመ ኮማንደሩ ተናግረዋል። ተጠርጣሪው ከአምስቱ መካከል የአንዲትን ሟች የአምስት ዓመት ልጅንም ማገቱን ፖሊስ አስረድቷል።

ተጠርጣሪው በ2015 ዓ.ም. አንዲትን ሴት ቡና በርካሽ ዋጋ እንደሚሸጥላት በማታለል ወስዶ በመግደሉ የ22 ዓመት እስራት ተፈርዶበት እንደነበር ኮማንደር ገብረሥላሴ አስታውሰዋል።

በመስከረም ወር አጋማሽ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የትግራይ ኃይል እስረኞችን ለቋል ያሉት ኮማንደሩ ተጠርጣሪው በዚህ አጋጣሚ ከእስር መውጣቱን አስረድተዋል።

እንደ ኮማንደሩ ገለጻ፣ ተጠርጣሪው መስከረም 25/2019 ዓ.ም. ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ነው አምስቱ ሴቶች ላይ ወንጀሉን የፈጸመው።

ተጠርጣሪው ወንጀሉን የፈጸመው ከጥቅምት 19 እስከ ኅዳር 8/2019 ዓ.ም ባሉት 20 ቀናት ውስጥ መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።

መጀመሪያ የተገደለችው ዮርዳኖስ ሓጎስ ስትባል በጥቅምት 19 ተገድላለች፤ የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ሟች የሻለም ዘነበ ደግሞ በጥቅምት 25፣ ሦስተኛዋ ሟች ገነት ደጀን በጥቅምት 30፣ አራተኛ ሟች ሚሊዮን ገብረእግዚአብሔር ኅዳር 7 እንዲሁም የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወሰንየለሽ መኮንን ደግሞ ኅዳር 8 ቀን ግድያ እና ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪው በሴቶቹ ላይ ግድያውን ለመፈጸም ቢላዋ፣ መጥረቢያ እና ድንጋይ እንደተጠቀመ ኮማንደር ገብረሥላሴ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ወንጀሉን እንደፈጸመ ያመነ ሲሆን፣ ወንጀሉን የፈጸመበትን ምክንያት ሲያስረዳ "በተፈጥሮዬ ችግር ስላለብኝ ነው" የሚል ምላሽ እንደሰጠ ፖሊስ አመልክቷል።

ኮማንደር ገብረሥላሴ እንዳብራሩት፣ ግድያ መፈጸሙ ለተጠርጣሪው የኩራት እና የእርካታ ስሜት የሚሰጠው እንደሚመስል በምርመራው ተረድተዋል።

በተጠርጣሪው ተገድለዋል ከተባሉት መካከል አንዷ የሆነችው የየሻለም ዘነበ የአምስት ዓመት ልጅም የት እንዳለች እስካሁን አልታወቀም።

ምርመራው እንደሚያሳየው፤ ተጠርጣሪው ልጅቷን ካገተ በኋላ እናቷን 40 ሺህ ብር እንድትሰጠው በመጠየቅ፣ ልጇን እንደሚመልስላት ነግሯት ነበር።

የሻለምም ራቅ ወዳለ ወዳለ ቦታ በመምጣት ልጇን እንደምትረከብ ነግሯት ከደረሰች በኋላ ጥቃት ማድረሱን ፖሊስ ገልጿል። ነገር ግን ልጅቷ ያለችበት ቦታ እስካሁን አልታወቀም፤ ጉዳዩም በምርመራ ላይ ይገኛል።

ከሟቾቹ መካከል የሆነችው ገነት እሷን ጨምሮ ሁሉም ሟቾች በሻይ ቡና እና በአልኮል መጠጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው ነበር ብሏል ፖሊስ።

የምርመራው መነሻ የሆነው በኅዳር 7/2019 ዓ.ም የተገደለችው በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች የሚሊዮን ገብረእግዚአብሔር ግድያ ነው።

ከሟቿ ጋር ትሠራ የነበረች ሴት፣ ሚሊየን በጠዋት ስልክ ደውላላት፣ ተስፋይ የሚባል ሰው ቡና በርካሽ ዋጋ እንደሚያቀርብላት ነግሯት ወደ ሥራ ቦታዋ እንድትመጣ እንደጠራት አሳውቃት ነበር።

አብራት የምትሠራዋ ወደ ሥራ ቦታው ባቀናችበት ወቅት ግን ሚሊየን ሻይ ቡና የምትሠራበት ቦታ በሩ ተዘግቶ ነበር የጠበቃት።

በዚህም ምክንያት ጓደኛዋን ፈልጋ ስላጣቻት ቁልፍ አፈላልጋ በሩን ከፍታ ስትገባ አስክሬኗን እንዳገኘች የፖሊስ ምርመራ አመልክቷል።

ፖሊስ ከጓደኛዋ በተገኘው መረጃ መሠረት ምርመራ ሲያካሂድ፣ ተስፋይ የሚባል ግለሰብ ከሟቿ ጋር በስልክ ተደዋውሎ እንደነበር ማወቁን ኮማንደር ገብረሥላሴ ገልጸዋል።

ከዚያም የተጠርጣሪውን ማንነት፣ አካላዊ ገጽታ እና ልዩ መለያ በማጣራት ወደ ተጠርጣሪው መድረሳቸውን ተናግረዋል።

ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በሠራው ወንጀል ከተፈረደበት እስር ማምለጡም ፖሊስ ምርመራውን ተስፋይ ላይ እንዲደረግ አስችሏል ሲሉ ኮማንደሩ ይገልጻሉ።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላም የወንጀሉን እውነተኛ ሁኔታ ለማረጋገጥ ግድያዎቹ ወደ ተፈጸሙባቸው ቦታዎች እንዲመራቸው እንደጠየቁት፣ እሱም እየመራ አምስት የወንጀል ቦታዎችን እንዳሳየ ኮማንደሩ አስረድተዋል።

ከሟቾቹ መካከል የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረችው ገነት ደጀን ከተገደለች በኋላ የት እንዳለች ሳይታወቅ እንደቆየች እና ቤተሰቦቿም በዚያን ጊዜ ስለመገደሏ እንዳላወቁ ተገልጿል።

ተጠርጣሪው ከከተማ ራቅ ወዳለ ቦታ ወስዶ አስክሬኗ የሚገኝበትን ቦታ የጠቆመ ሲሆን፣ የሟቿ መሆናቸውን የሚያመለክቱ የግል ንብረቶች እና የአካል ቅሪቶች እንዳገኙ ኮማንደሩ ገልጸዋል።

የሌሎቹ አስክሬን ቀደም ብሎ የተገኘ ቢሆንም በማን እና በምን ምክንያት እንደተገደሉ ለመመርመር በወቅቱ የነበረው የፀጥታ ሁኔታ እንዳላስቻለ ኮማንደሩ ተናግረዋል።

ከሟቾቹ መካከል የሻለም ዘነበ እና ገነት ደጀን ከቤት ውጪ ሲገደሉ ቀሪዎቹ በቤታቸው መገደላቸውን ፖሊስ አመልክቷል።

ይሁንና ምርመራው ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም። በተለይም የአምስት ዓመቷ ሕፃን ያለችበትን ቦታ ለማወቅ እና ሌሎች ተጨማሪ የወንጀል ጥቆማዎች ካሉ ለማጣራት ምርመራው እየቀጠለ እንደሆነ ተገልጿል።

በተጎጂዎቹ ቤተሰቦች በኩልም ተጠርጣሪው በሕግ እንዲጠየቅ እና ዳግም ከእስር እንዳይወጣ የሚፈልጉ መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።

በትግራይ ባላደራ አስተዳደር የሴቶች ጉዳይ ቢሮ የተፈጸመውን ግድያ እና ከግድያው በኋላ የተፈጸመውን ፆታዊ ጥቃት በጥብቅ አውግዟል።

ተጠርጣሪው እና በሴቶች ላይ ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት ሁሉ በሕግ ፊት ቀርበው የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቋል።

በሴቶቹ ሕይወት እና ክብር ላይ የተፈጸመው ድርጊት መላውን የትግራይ ሕዝብ በከባድ ድንጋጤ እና ሐዘን ውስጥ እንደጣለም አመልክቷል።

ቢሮው በመግለጫው፣ የትግራይ ሕዝብ እና ሴቶች ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በተካሄደው አውዳሚ ጦርነት፣ በረሃብ እና በውድመት ከደረሰባቸው ከባድ ስቃይ ሳያገግሙ ተደጋጋሚ ግድያዎች እና ጥቃቶች ሰለባ ሆነው መቆየታቸውን ገልጿል።

ከጦርነቱ በኋላ በሕዝቡ ላይ የተፈጠረው ጠባሳ ሳይሽር በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ግድያዎች መቀጠላቸው "ከባድ ማኅበራዊ እና ሰብዓዊ ቁስል ነው" ብሏል ቢሮው።