ሩሲያ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በኪየቭ ላይ በፈፀችው ጥቃት ቢያንስ 11 ሰዎች ተገደሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሩሲያ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በዩክሬን መዲና ኪየቭ ላይ በፈፀመችው ጥቃት ቢያንስ 11 ሰዎች መገደላቸውን የከተማዋ ከፍተኛ ወታደራዊ አስተዳዳሪ ተናገሩ።

ቲሙር ቲካንቸንኮ እንዳሉት ከሟቾቹ በተጨማሪ አምስት ሕፃናትን ጨምሮ 46 የሚሆኑ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በኪየቭ ግዛት ውስጥም ሌሎች ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የድንገተኛ አደጋ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ቲካቸንኮ በቴሌግራም ገፃቸው ባጋሩት ጽሑፍ በከተማዋ በሚገኙ ከ20 በላይ አካባቢዎች የነፍስ አድን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በሁለት አካባቢዎች ሁለት ትላልቅ የመኖሪያ ሕንፃዎች በጥቃቱ መመታታቸውን አክለዋል።

የአሁኑ ጥቃት የተፈፀመው ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ በሚጠበቅበት እና በቱርክ ከሚካሄደው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብሰባ ዋዜማ ላይ ነው።

ጥቃቱ ከመፈፀሙ ከሰዓታት በፊትም ዜሌንስኪ ባለፈው ሐሙስ 30 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ተከትሎ ሞስኮ በኪየቭ ላይ ሁለተኛ ዙር "መጠነ ሰፊ ጥቃት" ለመፈፀም እየተዘጋጀች እንደሆነ ገልጸው ነበር።

የየእሁድ ምሽቱ ጥቃት ለመዲናዋ ነዋሪዎች አስጨናቂ የነበሩ ከፍተኛ ፍንዳታዎች የተሰሙበት እንዲሁም ዩክሬን በአየር መከላከያ ደወል ድምጽ የተናወጠችበት ነበር። በርካታ ነዋሪዎችም ከምድር በታች ባሉ መጠለያዎች ለመግባት ተገደዋል።

የሩሲያ ባሊስቲክ ሚሳዔሎች በከተማዋ በርካታ ሕንፃዎችን መምታታቸውንም የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ክሊሽኮ ተናግረዋል።

በአንዳንድ የመኖሪያ ሕንፃዎች እሳት መነሳቱንም ከንቲባው አክለዋል።

እንደ ከንቲባው ከሆነ መጋዘን እና የመኪና ጋራዥም በጥቃቱ ወድሟል።

ሰኞ ዕለት ጠዋትም በከተማዋ መጠነ ሰፊ ውድመት ታይቷል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች ከፍርስራሽ ውስጥ ሕይወት ለመታደግ ጥረት እያደረጉ ነው።

ሄሊኮፕተሮች እሳት ለማጥፋት ውሃ ይዘው በኪየቭ ሰማይ ላይ ሲመላለሱ ታይተዋል።

ሩሲያ ባለፈው ሐሙስ በርካታ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን የፈፀመች ሲሆን፣ አርብ ዕለት የማስጠንቀቂያ ድምጽ ከተሰማ በኋላ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከአካባቢው አንዲወጡ ተደርገዋል።

ዩክሬን ቢያንስ 30 ሰዎች በተገደሉበት የሐሙሱ ጥቃት የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያን ሆነ ብላ ዒላማ በማድረግ ሞስኮን ከስሳለች።

ሩሲያ ግን ዩክሬን በቅርቡ በግዛቷ በሚገኙ የኃይል ጣቢያ እና የኢነርጅ መሠረተ ልማት ላይ የፈፀመችባትን ጥቃት ለመበቀል ወታደራዊ እና የኢነርጅ ሰፈርን ዒላማ ማድረጓን ገልጻለች።

የዩክሬን ጥቃቶች ምሽቱንም የቀጠሉ ሲሆን፣ ሩሲያ በምትቆጣጠረው ክሬሚያ ግዛት ሴቫስቶፖል ከተማ ጊዜያዊ የኃይል መቋረጥን አስከትለዋል።

ዩክሬን ክሬሚሊን ወደ ሰላም ንግግር እንድትመጣ ለማድረግ የተለያዩ ዒላማዎች ላይ የምትፈፅማቸውን ጥቃቶች ጨምራለች።

ሆኖም ጥቃቶቿ በኪየቭ ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት እንዲባባስ አድርጎታል።

ዜሌንስኪ ከኔቶ ስብሰባ አስቀድሞ አጋር አገራት የሩሲያን የባሊስቲክ ሚሳዔሎች ጥቃት ለመመከት የአየር መከላከያ ሚሳኤሎችን ለመላክ መዘግየት እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

ዜሌንስኪ ጨምረውም ዩክሬን ተንቀሳቃሽ የሆነውን ፓትሪዮት የአየር ጥቃት መከላከያ ሚሳዔሎችን እንድታመርት ፈቃድ ስለሰጠቻቸው አሜሪካን አመስግነዋል።