ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትኞቹ የዩኒቨርስቲ ዲግሪዎች ከፍተኛ ገቢን ያስገኛሉ?
ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ መያዛቸው በሕይወት ዘመናቸው የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝ በሰፊው ቢታመንም፣ አዳዲስ ጥናቶች ግን የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በሚያስገኙት ገቢ መካከል ያለው ልዩነት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
ይህ መረጃ የዩናይትድ ኪንግደምን (ዩኬ) ትምህርት እና የገቢ መጠንን መሠረት ደያረገ ሲሆን፣ ነገር ግን በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ውስጥም ያለው ሁኔታ ከዚህ ብዙም የተለየ እንዳልሆነ ይታመናል።
በትምህርት ዘርፎች እና በሚያስገኙት ገቢ ላይ የተደረገው የፊስካል ጥናት ተቋም (IFS) ጥናት እንደሚያሳየው፣ በሕክምናው ዘርፍ የሚመረቁ ተማሪዎች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ካልተመረቁት ጋር ሲነጻጸሩ እስከ ከ400 ሺህ ዶላር በላይ ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ።
ኢኮኖሚክስ ተመራቂዎች ከፍተኛ ገቢ ሊያገኙ ቢችሉም የፈጠራ ጥበብ፣ የፍልስፍና እና የቋንቋን ተመራቂዎችን ጨምሮ በሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ዲግሪ ያላቸው ዲግሪ ከሌላቸው ተመሳሳይ ሰዎች ገቢ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ሲል ጥናቱ አመልክቷል።
የዩኬ የትምህርት ባለሥልጣናን ዝቅተኛ ገቢ በሚያስገኙ የትምህርት ዘርፎች ላይ የቁጥር ገደብ እንደሚያስቀምጥ እና ዝቅተኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መስፈርቶችን ማስቀመጥን እንደሚመክር አስታውቋል።
መረጃው እንደሚያሳየው አማካይ ተመራቂዎች ከግብር እና ከትምህርት ብድር ክፍያ በኋላም ቢሆን በሕይወት ዘመናቸው ከዩኒቨርስቲ ካልተመረቁት አቻዎቻቸው ወደ 100 ሺህ ዶላር በላይ ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ።
በአማካይ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች ከፍተኛ የገንዘብ ጥቅሞች ቢያገኙም፣ መረጃው እንደሚያሳየው አንድ አራተኛ የሚሆኑት ተመራቂዎች ዩኒቨርሲቲ በመማራቸው ምክንያት በሕይወታቸው ውስጥ በገንዘብ ረገድ የከፋ ፈተና እንደገጠማቸው ያምናሉ።
ከአስር ወንድ ተመራቂዎች አንዱ ቀደም ሲል ከነበረበት ሁኔታ በላይ ከ90 ሺህ ዶላር በላይ የከፋ ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል።
ከ16 ዓመት በኋላ ትምህርታቸውን የቀጠሉ ነገር ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች፣ ተመሳሳይ ውጤት ካላቸው እና ዩኒቨርሲቲ ያልገቡ ተመሳሳይ ውጤት ካላቸው አቻዎቻቸው ጋር ሲነጻጸር የዕድሜ ልክ ክፍያቸው በአማካይ ከ53 ሺህ ዶላር በላይ ከፍ ያለ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ዝቅተኛ የትምህርት ውጤት ካላቸው ተመራቂዎች መካከል፣ ከአስር ተማሪዎች ውስጥ አራቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ባይገቡ ኖሮ በሕይወት ዘመናቸው በገንዘብ ረገድ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥማቸው ይችል እንደነበር ሊያስቡ ይችላሉ።
ጥናቱ ዕድሜያቸው 21 ዓመት ከመሆኑ በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ጊዜ የመጀመሪያ ዲግሪ ለመጀመር በዕድሜ ልክ የሚያገኙትን የገንዘብ መጠን ይመለከታሉ። መረጃው የተገኘው በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ የተወለዱ እና በ2002 የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናቸውን የወሰዱ በእንግሊዝ የሚኖሩ ተማሪዎችን ትንተና በመጠቀም ነው።
የትምህርት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት መንግሥት በአንዳንድ ተቋማት ላይ አንዳንድ ኮርሶችን ለመገደብ በተከታታይ "ለተማሪዎች ዝቅተኛ ገቢን" በሚያስገኙት ላይ አማራጮችን ለማዘጋጀት ዕቅድ አውጥቷል።
መንግሥት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የብድር ገንዘብን ለማግኘት የሚችሉበትን እና ዝቅተኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መስፈርቶችን ለማጤን አዲስ ውይይት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
'ሁሉም ዲግሪዎች እኩል አይደሉም'
የዩኬ ክህሎት ሚኒስትር ጃኩዊ ስሚዝ እንዳሉት የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ የሚያጠኑትን ትምህርት "በጥንቃቄ መምረጥ" አስፈላጊ ነው።
ጨምረውም "እንዲሁ በጭፍን የምትማሩትን የዲግሪ ፕሮግራም አትወስኑ" ብለዋል።
"ዩኒቨርሲቲ በመግባት ዲግሪ ማግኘት አንድ ወጣት ሊያደርጋቸው ከሚችላቸው እጅግ ለውጥን ከሚመያጡ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ነገር ግን ሁሉም ዲግሪዎች ዕኩል ስላልሆኑ፤ ለስኬት ሙሉ ለሙሉ ዋስትና አይሆኑም።
"በትምህርት ዓይነቶች ላይ ካለው ልዩነት በተጨማሪ፣ በጣም ብዙ ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው ኮርሶች ለወጣቶች በዝቅተኛ ዋጋ ጥሩ ትምህርት አያቀርቡም፣ በዚህም ተስፋን በመሸጥ ተማሪዎችን ችግር ላይ ይጥሏቸዋል።"
ሪፖርቱን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የሱተን ትረስት፣ የማኅበራዊ ዕድገት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኒክ ሃሪሰን፣ ዩኒቨርሲቲዎች "የገንዘብ ገቢ ስኬት ዋስትና ባይሆንም፤ ወደ ላይ ለማደግ ጉዞ በጣም አስተማማኝ መንገድ" ሆነው ቀጥለዋል ብለዋል።
አክለውም "አብዛኞቹ ተመራቂዎች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ ትልቅ የገንዘብ ጥቅሞችን እያገኙ ነው፣ ይህም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ወጣቶች ጋር ሲነጻጸር በአብዛኛው ከፍተኛ ነው።"
ይሁን እንጂ፣ ሪፖርቱ ወጣቶች ስላሏቸው የሙያ አማራጮች "ምቾት የማይሰጥ ጥያቄ" እንዳስነሳ ተናግረዋል።
"ወጣቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዳይገቡ የምንነግራቸው ከሆነ፣ በምትኩ ምን እንዲያደርጉ ነው የምንመክራቸው? ዝቅተኛ ዋጋ ባላቸው ዲግሪዎች ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች ብዙ ናቸው፣ ነገር ግን ሌላ የተሻሉ አማራጮች ግን የሉንም።
"የልምምድ እና የቴክኒክ ሙያ መንገዶች ለዕድገት እና ለስኬት ትልቅ ተስፋ ሊሰጡ ይችላሉ፣ ነገር ግን ለብዙ ወጣቶች በቂ እና ዘላቂ አማራጭ ለመሆን የሚያስችሉ አይደሉም።"
የዩናይትድ ኪንግደም ዩኒቨርሲቲዎች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቪቪየን ስተርን እንደሚሉት ኪነጥበብን የመሳሰሉ አንዳንድ የዲግሪ ምርጫዎች "ገንዘብ ለማግኘት ሲባል የታለሙ እንዳልሆኑ" ማጉላት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
"እነዚህ የትምህርት ዘርፎች ለዩናይትድ ኪንግደም ትልቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሆኑትን የፈጠራ ኢንዱስትሪዎችን እንደሚያንቀሳቅሱ መገንዘብ አለብን።
"ባለንበት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን፣ የሰው ልጅ እንዴት እንደሚያስብና እንደሚሠራ ያለውን ግንዛቤ የበለጠ ዋጋ እንሰጣለን፣ ወደፊትም ያነሰ አይሆንም" ብለዋል።