ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ሰላም ፈልጌ አሜሪካ ብመጣም አላገኘሁትም" - ልጃቸውን በሱስ የተነጠቁ እናት
ሜሪያም በአሜሪካ ሚኒያፖሊስ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ተቀምጠው የልጇን ስም የያዙ ሰነዶችን ያገላብጣሉ።
የ57 ዓመቷ እናት በፌንታኒል ሱስ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳልነበረ ከሆኑ አንዷ ናቸው።
ሰነዶቹን እየተመለከቱ ሊጥሏቸው እንደሚችል ይናገራሉ። ከሰነዶቹ መካከል የልጃቸው የአስከሬን ምርመራ ውጤት ይገኝበታል።
የልጃቸውን የግብር ሰነድ ጨምሮ ሌሎችም የአሜሪካ ሕይወቱን የሚያሳዩ ወረቀቶች ይዘዋል።
ልጃቸው ከሞተ ስምንት ዓመት ቢሆነውም አሁንም ሐዘን ላይ ናቸው።
ከሦስት አሥርታት በፊት የሶማሊያን የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽተው ነበር ወደ አሜሪካ የተሰደዱት።
በአሜሪካ ደግሞ ሌላ ሰቆቃ ጠበቃቸው።
"አሜሪካ የመጣሁት ሰላም ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን አላገኘሁትም" ይላሉ።
የሜኔሶታ የጤና ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት በአውሮፓውያኑ 2024 ከልክ ባለፈ መጠን ኦፒዮይድ የተባለውን ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገር ከመውሰድ ጋር በተያያዘ የ678 ሰዎች ሕይወት አልፏል።
በ2022 የሞቱት ሰዎች ከ1,000 በላይ ነበሩ። የ2024ቱ አሐዝ ከዚህ ያነሰ ቢሆንም ሱስ የፈጠረው ቀውስ በመላው አገሪቱ የቤተሰቦችን ኑሮ እንዳመሰቃቀለ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለሜሪያም ይሄ መረጃ አሐዝ ብቻ አይደለም። ከቁጥሩ አንዱ ልጃቸው ነው።
የልጃቸው የአስከሬን ምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው ለሞቱ ምክንያት ፌንታኒል ነው። ፌንታኒል ሰው ሠራሽ ኦፒዮይድ ሲሆን፤ በመላው አሜሪካ ከልክ ባለፈ መጠን በመውሰድ (overdose) ምክንያት የሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ቀጥሏል።
"ሲሞት አስከሬኑን ለማስመርመር ወሰንኩ። ማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ያንን እንዳላደርግ ቢነግሩኝም የተፈጠረውን ማወቅ ነበረብኝ" ይላሉ ሜሪያም።
ልጃቸውን ማጣታቸው ለዓመታት ሲሸሹ የኖሩትን ጠባሳ ጥሎባቸው ያለፈ ትውስታ አስታውሷታል።
"በአገሬ ጦርነት ሲጀመር ልጅ ነበርኩ። የምወዳቸው ሰዎች ፊት ለፊቴ ተገድለዋል።"
የአሜሪካ ኑሮ ሰላም እና መረጋጋት እንደሚሰጣቸው ተስፋ አድርገው ነበር። ነገር ግን ሌላ ዓይነት ከባድ ስብራት ጠበቃቸው።
"ሞት እጅግ ያሳምማል፤ እስከ ዛሬ አብሬው እየኖርኩ ነው። የምኖረው ከብዙ ቁስል ጋር ነው።"
የፌንታኒል ሱስ ሜኔሶታ በሚኖሩ ስደተኞች ዘንድ እየተስፋፋ የመጣ ችግር እንደሆነ የሶማሊያ የማኅበረሰብ መሪዎች ይናገራሉ።
ባለሙያዎች እንደሚሉት የስደተኛ ቤተሰቦች ከሱስ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል።
ኦፒዮይድን ለመከላከል የሚደረገው ንቅናቄ ዋና የስትራቱጂ ኃላፊ ጁሊ ቡች እንደሚሉት፤ በሄንፒን ግዛት የስደተኛ ልጆች ባህላቸውን እና የሚጠበቅባቸውን ለማመጣጠን ተቸግረው ያድጋሉ።
"አሜሪካ የተወለዱት ልጆች በአፍሪካ ያለው ዓይነት ልምድ የላቸውም። በጣም ጥብቅ የሆኑ ሶማሊያዊ ቤተሰቦች ናቸው የሚያሳድጓቸው። የሚያድጉት ግን በአሜሪካ ባህል ነው" ሲሉ ያብራራሉ።
በአሜሪካ ከሶማሊያ ስደተኛ ቤተሰቦች የሚወለዱ ልጆች "ቤተሰቦቻቸው ለማያውቁት አደንዛዥ ዕፅ፣ መጠጥ፣ ሙዚቃ እና አለባበስ" እንደሚጋለጡም ይናገራሉ።
እንደዚህ ያሉ የባህል እና የአኗኗር ልዩነቶች ወላጆች እና ልጆች "በግልጽ ስለ አደንዛዥ ዕፅ እና ጉዳቱ" ተነጋግረው መግባባት እንዳይችሉ እንደሚያደርጉ ባለሙያዋ ይገልጻሉ።
ሚኒያፖሊስ የምትኖረው ዴካም የዚህ ቀውስ ሰለባ ናት። ለዓመታት ልጇን በሱስ ምክንያት እንደምታጣ ስትፈራ ኖራለች።
ልጇ ታዳጊ ሳለ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም እና የጎዳና ነውጥ ውስጥ መሳተፍ እንደጀመረ ትናገራለች።
"አንዳንዴ ሰዎች በሽጉጥ እያባረሩት እየሮጠ ቤት ይመጣ ነበር" ትላለች።
"ሁሉንም መጋረጃ እንድዘጋው፣ መብራቱን እንዳጠፋው እና ሁሉም ልጆች መሬት ላይ እንዲተኙ ይጠይቀኝ ነበር። ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ወይም ማን ጥቃት እያደረሰብን እንደሆነ አናውቅም ነበር።"
የተፈጠረው ቀውስ መቼ የከፋ አደጋን እንደሚስከትልባቸው ባለማወቅ ሁሌም በጭንቀት ትኖር እንደነበር ታስታውሳለች።
"እሱ ላይ እየተተኮሰበት ሳለ አንድ እንግዳ እጁ ላይ የተመታበት ጊዜም ነበር።"
ከሜሪያም ልጅ በተለየ ሁኔታ የዴካ ልጅ በሕይወት ተርፏል።
የሜሪያም ልጅ የዴካ ልጅ የቅርብ ጓደኛ ነበር። የሜሪያም ልጅ ሲሞት በመደንገጥ የዴካ ልጅ ሕይወቱን ለውጧል።
ጓደኛውን ማጣቱ ሱስ እያስከተለ ካለው ቀውስ እና ከሕይወቱ መስመር መዛባት ጋር እንዲጋፈጥ አስገድዶታል።
አሁን ላይ ተመሳሳይ ፈተና የገጠማቸውን ወጣቶች ይረዳል። ሕይወቱን ሊያሳጣው ከነበረው ከእርሱ ስህተት እንዲማሩ ያግዛል።
የዴካ ልጅ ሕይወት ሲለወጥ ብዙ ነገሮች መቀየራቸውን ትናገራለች።
"እኔም ብዙ ነገሮች ለመለወጥ ወሰንኩ። ዛሬ ዛሬ ልጆች ይለውጡናል። እርስ በርስ ሳንግባባ እንቀራለን" ትላለች።
እሷ ሶማሊያ ሳለች ያደገችበትን መንገድ ለመተግበር ከመሞከር ይልቅ በተለየ ሁኔታ ከልጇ ጋር መነጋገር ጀምራለች።
ሜሪያም ደግሞ በጥንቃቄ የልጇን ሰነዶች ትሰበስባለች። የልጇን የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከላይ ታስቀምጣለች። የሕይወቷ ቁስል ማሳያ ነው።
የዴካ ልጅ ከሞት መትረፍ ለሜሪያም አዲስ የሕይወት አቅጣጫ ሰጥቷታል።
ከሶማሊያ ጦርነት የሸሸችው እናት በአሜሪካ የገጠማት ትግል የጦር መሣሪያ አይደለም።
በሚኒያፖሊስ ሱስ ቤተሰቦችን ሲበትን እና የማይሻር ጠባሳ ሲጥል አይታለች።
አሜሪካ አገኘዋለሁ ብላ ያሰበችው ሰላም ምኞት ሆኖ ቀርቷል።