ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ ቤት ስንገባ ጫማን ማውለቅ ምን ያህል የጤና ጠንቆችን ሊያስወግድ ይችላል?
ወደ ቤትዎ ሲገቡ ቀን ሙሉ የተለያዩ ቦታዎችን የረገጡበትን ጫማዎትን አደርገው ነው ወይስ በር ላይ አውልቀው ነው የሚገቡት?
በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሰዎች እራሳቸውም ሆኑ እንግዶች ወደ ቤታቸው ሲመጡ ጫማቸውን አውልቀው እንዲገቡ ይፈልጋሉ።
ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፤ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ለጨቅላ ሕጻናት ጤና፣ ለንጽህና እና ሌሎችም ምክንያቶች ይቀርባሉ።
እርስዎስ በቤትዎም ሆነ ወደ ሌሎች ቤት ሲገቡ ጫማን የማውለቅ ልማድን ይደግፋሉ? ቤት ውስጥ ጫማን ማውለቅ ለጤና ምን ጥቅም አለው? ጫማችን ምን ዓይነት የጤና ስጋትን ያስከትላል?
ዓለም አቀፋዊ ክፍፍል
ወደ ቤት ውስጥ ሲገባ ጫማ ማድረግዎ ወይንም ማውለቅ የሚወሰነው እንደኖርንበት ማኅበረሰብ ነው።
በበርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ እስያ እና የባልካን አገራት ጫማን ቤት ውስጥ ማድረግ እንደ ነውር ይቆጠራል።
ነገር ግን በአውሮፓ እና በአሜሪካ እንግዳን ጫማውን አንዲያወልቅ መጠየቅ ትህትና ማጣት ተደርጎ ይወሰዳል።
ጃፓን በዓለም ላይ ካሉ አገራት በሙሉ በጫማ ረገድ ጥብቅ ሥርዓት አላት። በበርካታ ቤቶች ወደ ሳሎን ከመግባቱ በፊት ኮሪደር ያላቸው ሲሆን፣ ጫማም የመጨረሻው መዳረሻ ያ ስፍራ ይሆናል።
እንግዳ ጫማውን ማውለቅ ከዘነጋ "ወዲያውኑ ስሜት የተቀላቀለበት ምላሽ ይሰጣሉ" ሲሉ ዶ/ር ፋቢዮ ግይጊ ተናግራል።
በለንደን ዩኒቨርስቲ የአንትሮፖሎጂ መምህር የሆኑት ዶ/ር ፋቢዮ "ወዲያውኑ ሰዎች ሊቆጧችሁ ይችላሉ፤ አይሆንም፤ ቁም፤ ጫማህን አውልቅ ይላሉ" ሲሉ ያስረዳሉ።
ይህ ከንጽህና እና ከፍልስፍና ጋር የተያያዘ ነው።
"ከትዕምርት አንጻር ካየነው ደጅ ማለት ንክኪ ያለው፣ አደጋ የሞላበት፣ ቆሻሻ እና የተበከለ" መሆኑን ያስረዳል።
"ቤት ውስጥ ደግሞ ንጹህ መሆን የምንፈልግበት፣ ጽድት ያለ ሁኔታ እንዲኖር የምናደርግበት በመሆኑ በርካታ ሃይማኖታዊ ክንውኖች በዚህ ዙሪያ የተደራጁ ናቸው" ይላሉ።
በጫማችን ላይ ያሉት ባክቴሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
ሁለት ጎዳናዎች ላይ የተደረጉ ስኒከር ጫማዎችን ወደ ማይክሮ ባዮሎጂ ቤተ ሙከራ ተወስደው ምርመራ ተደርጎባቸዋል።
በብራይተን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቤተሙከራ ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሳራ ፒት ጫማዎቹን በናሙና መሰብሰቢያ ጠራርገው ለአንድ ለሊት አስቀመጡት።
በሚቀጥለው ቀን በማይክሮስኮፕ ናሙናው ሲታይ ባክቴሪያዎች ተራብተው ተገኝተዋል።
ከተገኙት ባክቴሪያዎች መካከል ለኢንፌክሽን ምክንያት የሆኑት ስቴፊሎኮከስ ኦውሬስ (staphylococcus aureus ) ባክቴሪያዎች ተገኝተውበታል።
እነዚህ ባክቴሪያዎች በተለይ ጤናማ በሆኑ ሰዎች ላይ "መጥፎ" ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ፒት ያስረዳሉ።
"ራስህን ከቧጨርክ እና ስቴፊሎኮከስ ኦውሬስ ወደ ሰውነትህ ከገባ የተበከለ መግል ይፈጠራል ብለዋል።
በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ በሆኑ ሰዎች ላይ ኒሞኒያ፣ የደም ቧንቧ ኢንፌክሽን ያስከትላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
ጫማዎቹ በተፈጥሮ በሰው ቆዳ ላይ የሚኖረውን ስቴፊሎኮከስ ኤፒደርሚዲስ (staphylococcus epidermidis) የተባለውን የባክቴሪያውን የቅርብ ዝርያዎችንም ይዘው ተገኝተዋል።
ይህ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን በሽታ የመከላከል አቅማቸው ለተዳከመ ሰዎች ከባድ ሕመም ሊያስከትል የሚችል ሲሆን፣ በሆስፒታል ቆይታ ወቅት ታካሚዎች ብዙውን ጊዜ ይያዛሉ።
ሌሎች ጥናቶችና ግምገማዎች እንደሚያሳዩት ጫማዎች እንደ ኢ.ኮላይ (E.coli) ባሉ አደገኛ ባክቴሪያዎችን ጨምሮ በሌሎች በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ሊበከሉ ይችላሉ።
"በመላው ዓለም የተለያዩ ባክቴሪያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ፈንገሶችም ይኖራሉ... እና ጥገኛ ተውሳኮችም ይኖራሉ" ይላሉ የባዮሜዲካል ሳይንስ ተቋም ፕሬዝዳንት ፒት።
ባክቴሪያዎች ከደጅ ወደ ቤት
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጫማዎች ባክቴሪያዎችን ከውጭ ወደ ቤታችን በፍጥነት ያስተላልፋሉ።
"ተህዋሲያን በቤት ውስጥ በሕይወት ሊቆዩ እንደሚችሉ እና ኢንፌክሽኑን ወደ ሌሎች የቤተሰብ አባላትዎ ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ አለ" ይላሉ ፒት።
በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ለጥቂት ቀናት ወይም ከዚያ በላይ ሞቅ ባለ ምንጣፍ ላይ በሕይወት ሊቆዩ እንደሚችሉም ጨምረው ተናግረዋል።
ከዚያ በኋላም ቢሆን፣ በወለል ላይ መራመድ አንዳንድ ባክቴሪያዎችን "እንደገና ሊያነቃቃ" ይችላል፣ ይህም እንደገና ወደ ሰዎች እንዲተላለፍ ያደርገዋል።
"ከሕፃን ጋር ምንጣፍ ላይ እየተንከባለሉ ከሆነ... ምንጣፉን ሲጫኑ ኢንፌክሽኖቹ እንደገና ያነቃቃሉ" ሲሉ ፒት ያስረዳሉ።
ይህ እንደ ሕፃናት ወይም አረጋውያን ያሉ ደካማ የተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ ላላቸው ሰዎች ከአብዛኞቹ ጤናማ አዋቂዎች የበለጠ አደጋ ነው።
ፒት ለእነዚህ ተህዋሲያን መጋለጥ የበሽታ መከላከያ ለመገንባት እንደሚረዳ ቢያምኑም፣ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከተለያዩ ባክቴሪያዎች ጋር እንድንገናኝ እንደሚያደርገን ጠቁመዋል።
ጫማ ማድረግ ወይስ ማውለቅ?
ፒት እንደገለጹት፣ የጥያቄያችን መልስ የሚገኘው በቤተ ሙከራው ውጤት ላይ ነው።
"በቤት ውስጥ ጫማ ማድረግ ሰቅጣጭ ነው፤ እንዲሁም ለጤናም እውነተኛ አደጋ ነው" ብለዋል።
"በዓለም ላይ የትም ብትሆን፣ ወደ ቤት እንደገባህ ጫማህን ማውለቅ አለብህ።"
ጫማን ማድረግ ከተፈለገ ግን በር ላይ ያለ ምንጣፍን በመጠቀም ጫማን ማጽዳት ወደ ቤት የሚዘልቁትን የባክቴሪያዎች ብዛት ለመቀነስ ይረዳል ሲሉ ያስረዳሉ።
"ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ቤትዎን በደንብ ቢያጸዱ ይመረጣል፤ ይህ ምናልባት ባክቴሪያዎችን፣ አቧራን እና ቆሻሻዎችን ለመከላከል በቂ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
በርካቶች ውጪ የሚያጠልቋቸውን ጫማዎች ቤት ውስጥ ፈጽሞ አያደርጉም። ከዚያ ይልቅ ደግሞ ቤት ውስጥ ብቻ የሚጠቀሙባቸው ቀለል ያሉ ጫማዎችን ለራሳቸውም ሆነ ለእንግዶች አላቸው።