ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ቤቶች እየተገነቡበት ነው የተባለው 'ስሪዲ' ቴክኖሎጂ ምንድን ነው? ምን ያህል የቤት ግንባታ ችግርን ያቃልላል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰኔ 2/2018 ዓ.ም. ዘመናዊ እና ፈጣን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚገነቡ ቤቶች ፕሮጀክትን መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ጎልቶ የታየው የስሪዲ ቴክኖሎጂ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ ቤቶችን በወራት እና በዓመታት ሳይሆን በቀናት ውስጥ "በፍጥነት እና በጥራት" ገንብቶ የሚጨርስ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር ሆነው በጎበኝዋቸው የስሪዲ ዘመናዊ ቤቶች ማምረቻ ስፍራዎች ለተገጣጣሚ ቤቶች የሚያገለግሉ የሕንጻ የተለያዩ ክፍሎች የሚመረቱበት ስፍራ ነው።
በእነዚህ የስሪዲ ኮንስትራክሽን የሚመረቱ ቤቶች "ጥራት ያላቸው ቤቶች በቀናት እና በሳምንታት ውስጥ" ገንብቶ ማስረከብ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ስሪዲ የግንባታ ቴክኖሎጂ ምንድን ነው? በርግጥ በቀናት ውስጥ ቤት ሰርቶ ያስረክባል ሲል ቢቢሲ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ሐብታሙ ጌታቸውን ጠይቋል።
እንደማንኛውም የስሪዲ ሕትመት ላይ እንደሚታየው "ኮንክሪት ፔስት የሚባል ነገር አለ" ይላሉ አቶ ሐብታሙ።
"ፔስት ማለት በተለያዩ ኬሚካሎች የዳበረ ኮንክሪት ቀጠን ብሎ ተዘጋጅቶ ኋላ ላይ ግን ጥንካሬውን ሙሉ በሙሉ የሚያገኝ ነው።"
ይህንንም ሲያስረዱ እያንዳንዱ ግድግዳ መጀመሪያ በሚሰጠው የኮምፒውተር ፕሮግራም መሠረት 'ይጋገራል' ብለዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ግድግዳውም፣ መዋቅሩም እየተጋገረ በስተመጨረሻ ሕንጻ ይሆናል።
ይህ ስሪዲ ኮንስትራክሽን በዋናነት ኮንክሪት በመጠቀም አካፋዩንም ቀድሞ በመሥራት፣ እየተጋገረ ወደላይ የሚወጣበት እና በስተመጨረሻ ሕንጻ የሚሆንበት ቴክኖሎጂ ነው።
ይህ አንድን ሕንጻ ከኮምፒውተር በቀጥታ በሚገነባበት ስፍራ ላይ 'ኮንክሪት ፔስት' በመጠቀም እየተጋገረ መዋቅሩ ራሱን የሚያጠናክርበት መንገድ አለው።
በዚያ መልኩ እየተጋገረ የሚጀራው ቤት ወይንም ሕንጻ እየተጠናከረ በስተመጨረሻ ሕንጻ ሆኖ ይወጣል።
ቤት በሦስት ቀን
የቤቶች ግንባታ ፍጥነት በየጊዜው የተለያዩ ሂደቶችን አልፏል። ብሎኬት ከመደርደር፣ አርማታ ከመቆርቆር፣ ከመለሰን ተሻግሮ የሕንጻውን የተለያዩ አካላት በሌላ ስፍራ አምርቶ በማምጣት መገጣጠም ተችሎ ቆይቷል።
አሁን ደግሞ ሕንጻው በሚሠራበት ስፍራ የስሪዲ ማሽኑን በማምጣት በኮምፒውተር ላይ የተቀመጠውን ቤት መጋገር ተችሏል።
ይህ የስሪዲ ቴክኖሎጂ ምን ያህል ፈጣን ነው? ምን ያህልስ በተቀረው ዓለም ይታወቃል?
አቶ ሐብታሙ ስሪዲ ቴክኖሎጂ በጣም አዲስ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች እየተሠራበት መሆኑን ይናገራሉ።
በእርግጥ ቴክኖሎጂው አንዳንድ ገደቦች አሉበት። ለትላልቅ የግባታ መዋቅሮች እና ለባለብዙ ወለል ሕንጻዎች የመዋል አማራጩ ገና ነው። ነገር ግን እነዚህንም በዚሁ ቴክኖሎጁ ለመገንባት ሙከራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
"አሁን ባለ አንድ እና ባለ ሁለት ፎቅ የሆኑ መዋቅሮች እየተሠሩ ነው። በጠቅላላ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው። በዓለም ገና እየተሞከረ ያለ እና ጥሩ ውጤት እያመጣ ያለ ነው።"
በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሕንጻዎቸን ለመገንባት ፈጣን መሆኑንም ሲያብራሩ "አንድ ቤት በሦስት ቀን ሊያልቅ ይችላል" ይላሉ።
ዲዛይኑ ከተመረጠ እና ቦታው ከተዘጋጀ እንዲሁም መሠረቱ ከተጣለ ከዚያ ተነስቶ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሕንጻውን 'የመጋገር' ሥራ ነው የሚካሄደው ሲሉም ያብራራሉ።
አውሮፓ ውስጥ በተለይ ስካንዴኔቪያን አገራት ውስጥ በብዛት ይተገበራል። አሜሪካ ላይ በስፋት እየተሠራበት ነው። በእርግጥ ስሪዲ የሚያትመው ማሽን ራሱ ገና እየዳበረ ያለ በመሆኑ ቴክኖሎጂው በስፋት ገና አልተስፋፋም።
ከእሳት አደጋ የተጠበቁ፣ እንደ ካምፖች ያሉ መኖሪያዎችን በፍጥነት ለመገንባት፣ በተለይ ረዣዥም ያልሆኑ ፎቆችን ቶሎ ሠርቶ ለማጠናቀቅ ጥሩ አቅም የሚሰጥ ቴክኖሎጂ መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል።
ቴክኖሎጂው ከአራት ፎቅ በላይ ያሉ ቤቶችን ለመገንባት እስካሁ ድረስ ገና አልተሞከረም። ከአራት ፎቅ በታች ያሉ ሕንጻዎች ላይ ግን በሚገባ መሥራት እንደሚችል ታይቷል።
ወጪ ቆጣቢ ነው?
የከተማ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በኢትዮጵያ የስሪዲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ባለአራት ፎቅ ሕንጻ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ "በጣም ባጠረ ጊዜ፣ በጣም ጥራት ያለው፣ የብረት ግብዓትን ወደ 30 በመቶ መቀነስ የሚያስችል፣ የሲሚንቶ ፍጆታንም ከ35 አስከ 40 በመቶ በሚደርስ መጠን የሚቀንስ፣ በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ" ቤቶች እየተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በመጀመሪያ ላይ የስሪዲ ማሽኑን ለመሥራት ገንዘብ የሚጠይቅ ቢሆንም፤ በሂደት ወጪ ቆጣቢ የማይሆንበት ምክንያት አለመኖሩን አቶ ሐብታሙ ያስረዳሉ።
የግንባታው ዘርፍ በርካታ የሰው ኃይል በመቅጠር ይታወቃል።
አናጢ፣ ግንበኛ እና ሌሎች ሙያተኞች በስሪዲ ቴክኖሎጂ የግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸው ስፍራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
"ብክነትን ይቀንሳል። የሰው ኃይል ተሳትፎ ሊቀንስ ስለሚችል የሥራ ቅጥር ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል" ይላሉ አቶ ሐብታሙ።
የግንባታ ዘርፉ በርካታ የሰው ኃይል የሚቀጥር ቢሆንም በስሪዲ ቤቶች ግንባታ ግን ከፍተኛ የሙያ ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ብቻ ሊያስፈልጉ ይችላል።
ባለ አራት ፎቅ ኮንደሚኒየም ለመሥራት ዋና የሚባለው መዋቅሩ በአንድ ወር ውስጥ ያልቃል የሚሉት ባለሙያው፣ ከዚያ ውጪ የፍሳሽ እና ኤሌትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ የቀለም ቅብ እና ሌሎች ወለል ማንጠፍን የመሳሰሉ የማጠናቀቂያ ሥራዎች በሰው ኃይል የሚሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከቤት ልማት ጋር በተያያዘ ግንባታውን ሊያፈጥኑ የሚችሉ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን የሚያነሱት አቶ ሐብታሙ፣ በርካታ ቤቶችን ሠርቶ ለማቅረብ ይህ ስሪዲ ኮንስትራክሽን እንደ አንድ ቴክኖሎጂ መታየት እንዳለበት ያስረዳሉ።
"በተለይ አጭር ቁመት ላላቸው ሕንጻዎች ጥሩ ቴክኖሎጂ ነው።"
ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ሊኖር ስለሚችል መጓተት ሊፈጠር እንደሚችልም ጠቅሰው፤ ይህ ቴክኖሎጂ ጥሩ የመሆኑን ያህል ሌላም ደግሞ መሞከር ጥሩ መሆኑን ይመክራሉ።
"በተለይ ቴክኖሎጂውን ከውጭ አገር ከማስገባት ይልቅ ራሳችንን አበልጽገን መሥራት ከቻልን ብዙ ነገሮችን ሊያቀልን ይችላል የሚል ሃሳብ አለኝ።"