በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች ሞቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የዞኑ ባለሥልጣን እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የዞኑ የፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሚሽነር ዘለቀ አለባቸው ጥቃቱ በተፈጸመበት ተሽከረካሪ ላይ ከነበሩ ተሳፋሪዎች መካከል ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአቀስታ ሆሰፒታል ባልደረባ በበኩላቸው ወደ ሕክምና ተቋማቸው ጉዳት ደርሶባቸው ከመጡ አምስት ሰዎች በተጨማሪ አንድ ግለሰብ ሕይወቱ አልፎ መድረሱን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ "ጽንፈኛ" ሲሉ የጠሯቸው በአካባቢው የሚንቀሰቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች "በንጹኃን ላይ ጥቃትን ፈጽመዋል" ሲሉ ወንጅለዋል።

"ጽንፈኛው ገነቴ አካባቢ ማጥቃት ፈልጎ ስለነበር እንጪፍቱ ላይ ወገን [ተጨማሪ ኃይል] ይመጣል ብሎ አስቦ ዘግቶ ደፈጣ ይዞ ስለነበር ከዚህ አንጻር ንጹኃን ምንም ዓይነት ወታደራዊ ንክኪ የሌላቸው ተሳፍረው ከገነቴ ሲመጡ እንዲገደሉ ተደርጓል" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በተሽከርካሪው ላይ የተፈጸመው ጥቃት "ሆን ተብሎ በሕዝብ ጥላቻ የተሰነዘረ ጥቃት" ነው በማለት ከወታደራዊ ዒላማ ጋር ግንኙነት የለውም ብለዋል።

እኚህ የዞኑ ባለሥልጣን ለግድያው እንደምክንያት ያስቀመጡት "ሕዝብ ላይ ያለ ጥላቻ ነው" ካሉ በኋላ በሁለተኛነት "የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለማሸበር አስበው የሠሩት ሥራ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ረቡዕ ጠዋት ከ1፡30 እስከ 2፡00 ባለው ጊዜው ውስጥ መፈጸሙን የሚናገሩት የዞኑ የፀጥታ ኃላፊ ተሳፋሪዎቹ ከገነቴ ወደ አቀስታ በሚኒባስ ተሳፍረው የሚሄዱ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ተሳፋሪዎቹን የጫነው ሚኒባስ እየሄደ ባለበት ወቅት ተኩስ እንደተከፈተበት የሚናገሩት ኮሚሽነሩ፣ ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ አምስት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ገብተዋል ብለዋል።

ለህክምና ከተወሰዱት ሰዎች መካከል ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ በመሆኑ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አምስት ደርሷል።

የሞቱት እንዲሁም የተጉዱት ግለሰቦች በጥይት መመታታቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ የአካባቢው ፀጥታ ኃይሎች በስፍራው ሲደርሱ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ሸሽተው መሄዳቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱ ገነቴ አካባቢ 12 ሰዓት ላይ "የአማራ ጽንፈኛ ኃይሎች" ተኩስ ከፍተው ስለነበር ድጋፍ እንደዳይመጣ ለማድረግ ማንኛውም መኪና በአካባቢው አንዳያልፍ እና የሕዝብ እንቅስቃሴን ለማገድ የተፈጸመ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ከዚያ በኋላ ስንዋጋቸው ሸሽተው ሄደዋል ያሉት ኮሚሽነሩ መንገዱ አሁን ለእንቅስቀሴ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው በአቀስታ ሆስፒታል ሕክምና እንደተደረገላቸው እና አንድ ተጎጂ አሁንም የሕክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሆሰፒታል ምንጭ ተናግረዋል።

"አሁን እዚህ እኛ ጋር ያለው አንድ የ48 ዓመት ታካሚ ነው። ሆዱን ነው በጥይት የተመታው" ብለዋል።

ግለሰቡ ከፍተኛ የደም መፍሰስ ገጥሞት እንደነበር የሚናገሩት የሕክምና ባለሙያው ሌሎች ጉዳት ደርሶባቸው የመጡ ወደ ደሴ ሆስፒታል ለተሻለ ሕክምና መላካቸውን ጠቅሰዋል።

ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው በዕለቱ ታክመው ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ሲደረግ የእጅ መገጣጠሚያዋ ላይ በጥይት የተመታች እና ጥይቱ ውስጧ የቀረ ተጎጂ ወደ ደሴ ሆስፒታል መላኳን ተናግረዋል።

በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው የመጡ ግለሰቦች በተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች ድጋፍ እንደተደረገላቸው የገለጹት ባለሙያው አንድ ግለሰብ ሕይወቱ አልፎ ሆስፒታል መድረሱን ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ በአካባቢው ከሚንቀሳቀስ ፋኖ ታጣቂ ኃይል ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ግጭት የበርካቶችን ሕይወትን ነጥቋል።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በክልሉ ውስጥ ከፍርድ ውጪ ግድያ፣ በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ ከሕግ ውጪ እስራት፣ አስገድዶ ስወራ፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንደሚፈፀም ይገልፃሉ።

በበርካታ የክልሉ አካባቢ ባለው የፀጥታ ስጋት ምክንያት በተሽከርካሪዎች እና በተጓዦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል።