ሜታ የልጆችን ደኅንነት ባለመጠበቅ 567 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ተወሰነ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሜታ ማኅበራዊ ሚዲያው በልጆች ላይ የደቀነውን አደጋ በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ባለመስጠቱ ተጨማሪ 567 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ፍርድ ቤት ወሰነ።

በአሜሪካ፣ ኒው ሜክሲኮ ፍርድ ቤት የተላለፈው ውሳኔ የልጆችን ደኅንነት ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ትልቁ ብይን ነው።

ዳኛ ብራየን ቢድሻይድ ማኅበራዊ ሚዲያው በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና እንደ የአየር ብክለት ነው ብለዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያው በቅጣት የሚከፍለው ገንዘብ ጉዳቱን ለመቀነስ መዋል አለበት ሲሉም አክለዋል።

ሜታ በቀረበበት ተመሳሳይ ክስ 373 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል የተወሰነ ሲሆን፤ አሁን የተፈረደበት ተጨማሪ ክፍያ ከዚህ ቀደሙ ጋር ሲደመር አጠቃላይ ቅጣቱ 942 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ዳኛው ሜታን ይዘቶቹን ከሚሸቅጥ ፋብሪካ ጋር አነጻጽረዋል። ይዘቶቹ "የሥነ ልቦና ጫና የሚያሳድሩ እና ልጆችን ለወሲብ ብዝበዛ የሚያጋልጡ ስለሆኑ ብክለቱ መገታት አለበት" ብለዋል።

ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዋትስአፕ እና ትሬድስን የሚያስተዳድረው ሜታ ቃል አቀባይ "በውሳኔው አንስማማም፤ ይግባኝ እንላለን" ብለዋል።

"በመተግበሪያችን ሰዎች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ብዙ ሠርተናል። መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙን እና ጎጂ ይዘትን በመለየት ረገድ ያለውን ፈተና በግልጽ አሳውቀናል። ታዳጊዎችን በመጠበቅ ረገድ ባለን ሚና እንኮራለን። እውነታውን የሚያንሸዋርር ውሳኔን እንገዳደራለን" በማለት አክለዋል።

ከዚህ ቀደም 375 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል የተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ይግባኝ እንደሚል ሜታ ገልጿል።

የአሜሪካ ግዛት ሜታን ከልጆች ደኅንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ ከስሶ ውጤታማ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ነው።

ሜታ አሁን ላይ በአሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውበታል።

በአውሮፓውያኑ 2026 መባቻ ላይ በሎስ አንጀለስ በቀረበበት ክስ ተሸንፏል።

ሜታ ልጆችን ለአደጋ በመዳረጉ፣ ለልቅ ወሲባዊ ይዘት በማጋለጡ እና ወሲባዊ ጥቃት አድራሾች ባሉት መድረክ ከለላ ባለመስጠቱ በኒው ሜክሲኮ እንዲከሰስ የተወሰነው በ2023 ነበር።

በክሱ የመጀመሪያ ክፍል ሜታ የኒው ሜክሲኮን የፍትሐዊ ድርጊት ሕግ ጥሶ ተገኝቷል።

የሜታ አልጎሪዝም ታዳጊዎችን ወደ ጎጂ ይዘት እና ሰዎች "የገፋ" ነው ተብሏል።

በሁለተኛው የፍርድ ቤቱ ሂደት ዳኛው ሜታ የሕዝብን ደኅንነት አለመጠበቃቸውን ገልጸዋል።

በጤና እና ደኅንነት ረገድ ጥበቃ ባለማድረጉ ሕዝብን ለአደጋ ማጋለጡ ተጠቅሷል።

ሜታ ከልጆች ደኅንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ የተቀጣው ከፍተኛ ገንዘብ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ለሕዝብ አደጋ የተባለበት የመጀመሪያው አጋጣሚም ነው።

ዳኛውም "የፋብሪካ ብክለት የሕዝቡን ንጹህ አየር የማግኘት መብት እንደሚጋፋው ሁሉ ሜታም ለልጆች ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም" ብለዋል።

"ልጆች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቤተሰቦቻቸው፣ ትምህርት ቤታቸው፣ ሆስሊታሎች እና የሕግ አስከባሪዎች ድረስ የሚዘልቅ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ሜታ የሚቀጣው ገንዘብ ካደረሳቸው ጉዳቶች ለማገገም እንደሚውል ዳኛው ጠቅሰዋል።

በዳኛው ውሳኔ መሠረት 420 ሚሊዮን ዶላር ቅጣቱ ሜታ ካሳደረው "የጤና እና የሥነ ልቦና ቀውስ ለማገገም የሚሠሩ ባለሙያዎች እና መርሃ ግብሮች ላይ" የሚውል ይሆናል።

የተቀረው ገንዘብ ግንዛቤ ለመፍጠት እና መምህራን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ልጆችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ጉዳት የሚጠብቁበት መንገድ ለመዘርጋት ይውላል።

የሜታ መተግበሪያ ዕድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ ተጠቃሚዎችን ለአዋቂዎች ጥቆማ መስጠት እንዳይችል ዳኛው አዝዘዋል።

አዋቂዎች ለታዳጊዎች መልዕክት መላክም እንዳይችሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ተጠቃሚዎች 'ላይክ' መቁጠር እንዳይቻል ተወስኗል።

የድረ ገጹ ጥቆማ ከምሽት እስከ ንጋት ለታዳጊዎች እንዳይላክ እና ከቅዳሜ እና እሑድ ውጭ በትምህርት ሰዓት ጥቆማ እንዳይላክ አግደዋል።

ተጠቃሚዎች በወር ውስጥ ኢንስታግራም እና ፌስቡክ የሚጠቀሙበት ሰዓት ከ90 ተከታታይ ሰዓት እንዳያልፍ ዳኛው ወስነዋል።

በቀጣይ ሜታ ከልጆች ደኅንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ ሌላ ትልቅ ክስ በካሊፎርንያ ይጠብቀዋል።