ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸው በሱዳን ጦርነት መካከል የተወለዱ ልጆች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ማሳሰቢያ፡ ይህ ዘገባ አንዳንዶችን ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው

የ17 ዓመቷ ሱዳናዊት ሕጻን ልጅ አቅፋለች። ሰውነቷን ክብደቱ ተጭኖታል። የወደፊት ሕይወቷ ጉዳይም አጠያያቂ ነው።

"ልጄ አባት የለውም። የልደት ሰርተፍኬት የለውም። መታወቂያ ቁጥር የለውም" ትላለች።

አሚራ (ስሟ ተለውጧል) ልጇን እያየች በስሱ ታወራለች።

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ የገጠማትን ሁሉ የምታሰላስል ይመስላል።

እሷ እና ቤተሰቧ በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ኤል-ፋሽር ይኖሩ ነበር።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) ከተማዋን ከበባ ውስጥ አስገብቷል።

ላለፉት ሦስት ዓመታት አርኤስኤፍ ከሱዳን ጦር ጋር ውጊያ ላይ ይገኛል።

ኤል-ፋሽር ለ18 ወራት በሱዳን ጦር ይዞታ ሥር የነበረች ቢሆንም ባለፈው ጥቅምት በአርኤስኤፍ እና የአረብ ሚሊሻዎች ተቆጣጥረዋታል።

በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች ከከተማው መውጣት አልቻሉም። ሕይወትም ጨለማ ሆኖባቸዋል።

በተከታታይ ጥቃቶች ይፈጸማሉ፤ ግጭት ይነሳል፤ የምግብ እጥረትም ሌላው ፈተና ነው።

አሚራ እና ቤተሰቧ አማራጭ ሲያጡ በአውሮፓውያኑ 2025 መባቻ ከተማውን ጥለው ለመሰደድ ወሰኑ።

በከተማው ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ መንገድ ላይ ሳሉ ሦስት የአርኤስኤፍ ወታደሮች አገቷቸው።

"ዐይኔን ሸፍነው ወደ ታቢት አካባቢ ወሰዱኝ፤ በኤል-ፋሽር ደቡባዊ አቅጣጫ ይገኛል። ለሁለት ወር አንድ ክፍል ውስጥ ተቆልፎብኝ ነበር። በየቀኑ አንዳቸው እየመጡ ይደፍሩኝ ነበር" ስትል ዝግ ባለ ድምጽ ታስታውሳለች።

ለሳምንታት ታግታ ከቆየች በኋላ ማርገዟን አወቀች። በጣም ታመመች ።

አሚራ እንደምትለው ወታደሮቹ አግተው የያዙዋት አካባቢ ወስደው ጣሏት።

ሌሎች ከኤል-ፋሽር እየሸሹ የነበሩ ሰዎች የሕክምና ድጋፍ እንድታገኝ እንደረዷት ትናገራለች።

ከወራት በኋላ አርኤስኤፍ በማይቆጣጠረው ሰብአዊ ድጋፍ መስጫ ሆስፒታል ውስጥ ልጇን ወለደች።

ናዳ አል-አዝሀር ፋውንዴሽን ከተባለ የሱዳን ድርጅት እርዳታ አግኝታለች።

ድርጅቱ ከኤል-ፋሽር የሸሹ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ ውስጥ የአሚራ ቤተሰብ አግኝቶላታል።

ከቤተሰቦቿ ጋር መቀላቀሏ እፎይታ ሰጥቷታል። ቤተሰቧ አሁንም ፈተና ውስጥ ነው።

አሚራ ከወለደች ስምንት ወራት ቢያልፉም ልጇን በብሔራዊ መዝገብ ማስመዝገብ አልቻለችም።

"ከሆስፒታሉ የልደት ሰርተፍኬት ለማግኘት የሚጠይቁት መረጃ የለኝም" ትላለች።

የልጇን አባት አታውቀውም። ስለዚህም ልጇ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ እንዲመዘገብ ማድረግ አልቻለችም።

"ልጄን ማስከተብ አልችልም፤ ትምህርት ቤት ማስገባትም አልችልም" ትላለች።

"ስላልተመዘገበ የወደፊት ሕይወቱ ያሳስበኛል። የኑሮ ሁኔታዬ በጣም አስከፊ ነው። ማሳከም ወይም መንከባከብ አልችልም። በድጋሚ ጥቃት ሊደርስብኝ ይችላል በሚል ፍርሃት ወደ ሥራ መሄድም ተስኖኛል።"

ናዳ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ እንደ አሚራ ያሉ ታሪኮች ብዙ ናቸው። ታሪኳ በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች የሚሰማ እውነታ ነው።

በርካታ ልጆች ውስብስብ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየተወለዱ ነው። የአባታቸው ማንነት አይታወቅም። ስለዚህም መወለዳቸው እንደማይመዘገብ የናዳ የከለላ መርሃ ግብር ዳይሬክተር አቡ ባካር ዩሱፍ ያኩብ ይናገራል።

"ልጅ ሲወለድ ለመመዝገብ የማንነት መግለጫ፣ ብሔራዊ የምዝገባ ቁጥር እና የልደት ሰርተፍኬት መረጃ ያስፈልጋል። አባት ከሌለ ወይም ማንነቱ ካልታወቀ በጣም ከባድ ይሆናል" ይላል።

እናቶች አብዛኛውን ጊዜ ብቻቸውን እንደሚሆኑ ይናገራል።

"አንዳንዶቹ ሴቶች እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ልጆች ናቸው። ለልጆች እንክብካቤ የመስጠት አቅማቸውን ይገድበዋል" ይላል።

ልጆች ከተወለዱ ጀምሮ የሚሰጣቸውን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ክትባቶችን አለማግኘት የጤና ቀውስ እንደሚያስከትልም ያስረዳል።

የሚያሳድረው ጫና በልጆች የለጋ ዕድሜ የተገደበ ሳይሆን በወደፊት ሕይወታቸው ትምህርት ለመከታተል እና በይፋዊ ሰነድ አማካኝነት ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ እንዳይችሉ ያደርጋል።

በሱዳን በመደፈር ሳቢያ የተወለዱ ልጆች ትክክለኛ ቁጥር ማግኘት ቀላል አይደለም።

የናዳ ዋና ኃላፊ ሻዛ አሕመድ እንደምትለው፤ ባለው ማኅበረሰባዊ መገለል ምክንያት የተወለዱት ልጆች ትክክለኛ ቁጥር አልተመዘገበም።

"እንዲህ ዓይነት ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ምቾት ተሰምቷቸው ሪፖርት አያደርጉም" ትላለች።

"የሚያሳዝነው የአብዛኞቹ ልጆች እናቶች እራሳቸው ልጆች መሆናቸው ነው። ከ18 ዓመት በታች ናቸው። ቤተሰብ ሊያጅባቸው ስለሚገባ ወደ ፖሊስ ወይም ፍርድ ቤት ለመሄድ መወሰን አይችሉም።"

ናዳ ከመዘገባቸው ኬዞች 90% በሚሆኑት ቤተሰቦች ልጆቻቸው ላይ ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሞ ማርገዛቸውን ሪፖርት ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም።

"እንደ ሱዳናዊት ሴት ትልቁ ፍርሃቴ እና ስጋቴ ሴቶች ተደፍረው የሚወለዱ ልጆች በመገለል፣ በአደጋ እና በፍርሃት ውስጥ የሚያድግ ትውልድ መሆናቸው ነው" ትላለች።

"እነዚህን ልጆች ማኅበረሰቡ ክብር አይሰጣቸውም። ደኅንነታቸው አይጠበቅም። ከምንም ነገር በላይ መብታቸውን ይነፈጋሉ" ስትል ታስረዳለች።

እነዚህ ልጆች "ሙሉ ሰው" ሆነው ተቀባይነት እንደሌላቸው እና የሱዳን ሕግ ለሁሉም ልጆች ማንነት የማግኘት መብት እንደማይሰጥ ትናገራለች።

ሱዳናዊቷ ጠበቃ ማጂዳ ኢድሪስ እንደምትለው የአገሪቱ ሕግ ከትዳር ውጭ የሚወለዱ ልጆች እንዲመዘገቡ ይፈቅዳል።

ነገር ግን እናቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው የሚገልጽ ሰነድ ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ መሆን አለባቸው።

የምዝገባ ሒደቱ የሚጀምረው ሴቶቹ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ይሆናል።

ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ጉዳዩ ወደ ማኅበራዊ አገልግሎት መሥሪያ ቤት ተወስኖ ይመዘገባል።

ከዚያም ሕጋዊ ሒደቱን ተከትሎ ልጆቹ በእናታቸው ስም ሥር ይመዘገቡና ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ስም ይሰጣቸዋል።

ጠበቃዋ ማጂዳ እንደምትናገረው በጦርነት ወቅት በተለይ በዳርፉር ያለው እውነታ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው።

በግጭቱ ምክንያት ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ መሥሪያ ቤቶችን አስተጓጉሏል። የምዝገባ ቢሮ በመዘጋቱም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልተመዘገቡም።

"ሰነድ የለም ማለት ወረቀት የለም ማለት ብቻ አይደለም። ይህም ልጆች ትምህርት፣ ሕክምና እና ሕጋዊ ዕውቅና እንዳያገኙ ያደርጋል" ትላለች።

ጠበቃዋ እንደምትለው፤ ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች የምዝገባ መሥሪያ ቤቶችን መክፈት ያስፈልጋል።

ልጆች መብታቸው እንዲከበር እና ሕጋዊ ማንነታቸው ዕውቅና እንዲያገኝ መደረግ እንዳለበት ታስረዳለች።

አሚራ እና ልጇ ዳርፉር እየኖሩ ነው። የአካባቢው አስተዳደር ጉዳይ አሁንም ግልጽ አይደለም።

የአሚራ እናት፤ የልጅ ልጇ ሕጋዊ ዕውቅና እንዳለው የሚያሳይ ሰነድ አለመኖሩ አሳስቧታል።

አሁን ላይ ግን ቤተሰቡ መልሶ በመገናኘቱ ደስተኛ ሆነዋል።

ናዳ ለአሚራ የሥነ ልቦና ድጋፍ ሰጥቷል። በዚህም ቤተሰቡ ደስተኛ ነው።

"እስካገኛት ድረስ በጣም ከፍተኛ ጭንቀት ውጦኝ ነበር፤ መብላትም መጠጣትም አልቻልኩም ነበር" ስትል የአሚራ እናት ትናገራለች።

"መልሰን መገናኘታችን የፈጣሪ ተዓምር ነው። ልጃችን ከእኛ ጋር መቀላቀሏ ስጦታችን እና በረከታችን ነው። ፈጣሪን አመስግነን አንጨርስም።"