በሁለቱ የኢሕአፓ ፖለቲከኞች እና በተቃዋሚዎች ጠበቃው አበራ ንጉሥ ላይ 12 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት "በሽብር ወንጀል" የተጠረጠሩት ፖለቲከኞቹ አበበ አካሉ እና ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉሥ ላይ የ12 የምርመራ ቀናት መፍቀዱን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዛሬ አርብ ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም. ረፋድ ላይ የተሰየመው ችሎት የመርማሪ ፖሊስን ጥያቄ የተቀበለው፣ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ለተነሳው ጥርጣሬ በማስረጃነት የቀረቡት ቃለ መጠይቆች ላይ "የሽብር መነሻ ሐሳብ በማግኘታቸው" እንደሆነ ጠበቃው ገልጸዋል።

ሁለቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፖለቲከኞች እና ለተቃዋሚዎች ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት አበራ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኞ ሐምሌ 27 ነበር። በፌደራል ፖሊስ አባላት በተያዙ ሁለተኛው ቀን ረቡዕ ዕለት በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ "በመንግሥት የፀጥታ ተቋማት እና በመንግሥትት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የሽብር ጥቃት" ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለፍርድ ቤት ገልጿል።

ድርጊቱን ሊፈጽሙ የነበሩት "ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ድብቅ ግንኙነት በማድረግ" እንደሆነ የገለጸው ፖሊስ፤ "ጽምዶ [ተ]ብሎ ከሚጠራው ኃይል ጋር በቀናጀት" ምልመላ እና ስለላ ሲያከናውኑ እንደነበር በመጥቀስም ወንጅሏል።

በዚህ ጉዳይ ላይ "ሥራውን አጠናቅቆ መዝገቡን ለሚመለከተው የሕግ አካል ለመላክ" እንዲችልም 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ፣ በሦስቱ ግለሰቦች ላይ የቀረበውን ውንጀላ ለማስረዳት በቀረቡት በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የተደረጉ ቃለ መጠይቆች 'የሽብር ይዘት አላቸው ወይስ የላቸውም' የሚለውን ለመወሰን ለዛሬ አርብ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት በመርማሪ ፖሊስ ቀረቡትን "የሐሰት ፕሮፓጋንዳ" ቪድዮ ሊንኮች መመልከቱን እንደገለጸ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዳኞች በቀረቡላቸው የቪዲዮ ሊንኮች ላይ "የሽብር ይዘት" የሚያገኙ ከሆነ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ሊፈቀድ እንደሚችል፤ ካልሆነ ደግሞ በዋስትና ሊወጡ ይችሉ እንደነበር ጠበቃው አስረድተዋል።

እንደ ጠበቃው ገለጻ፣ ቪዲዮዎቹን የተመለከቱን ዳኞች ለፖሊስ ጥርጣሪ "መነሻ የሚሆኑ ይዘቶችን አግኝተናል" ብለዋል።

ዳኞች "በሰማነው ድምፅ ላይ ድርጊቱ የሽብር ሊመስል የሚችል የመነሻ ሀሳብ አግኝተናል። በተወሰነ መልኩ የመነሻ ሀሳብ ስላገኘን ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል" እንዳሉ ጠበቃው አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ተጠርጣሪዎቹ "ፍርድ ቤት ከቀረቡበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ" መፍቀዳቸውን ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ በቀጣዩ በሚኖረው ቀጠሮ ላይ "ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ" እንዲቀርብ ትዕዛዝ መሰጠቱንም ጠበቃ ሰለሞን ተናግረዋል።