ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን በሩሲያ "የተሰረቀ" እህል ወደ እስራኤል ተጓጉዟል ስትል ከሰሰች
እስራኤል፤ ሩሲያ በወረራ ከያዘችው የዩክሬን ግዛት የተነሳ እህልን ተቀብላለች የሚል ክስ መሰማቱን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ተነስቷል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ "በሩሲያ የተሰረቀ" እህልን የጫነ "ሌላ መርከብ" ወደ እስራኤል ወደብ ደርሶ፤ ጭነቱን ለማራገፍ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ወደ አገራቸው ወደብ የደረሰው መርከብ የያዘው ጭነት ምን እንደሆነ "ላያውቁ አይችሉም" ሲሉ ወቅሰዋል። የእህሉን ጉዞ ለማገድ አለመቻል የሁለትዮሽ ግንኙነትን ያበላሻል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ከዚህ አስቀድሞ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር፤ ዩክሬን ይህንን አይነት ውንጀላ በይፋ ማሰማቷን አንስተው ወቅሰው ነበር። ክሱ "በማስረጃ የተደገፈ" አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ጉዳዩ ግን እንደሚመረመር ገልጸዋል።
የሩሲያ ቤተ መንግሥት ክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔሽኮፍ በበኩላቸው "ስለዚህ ጉዳይ ማንኛውንም አስተያየት መስጠት ወይም በጉዳዩ መሳተፍ እንደማይመርጡ" ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ሩሲያ የዩክሬን እህልን ሰርቃለች መባሉን አስተባብላ ነበር።
በዩክሬን እና እስራኤል መካከል መቃቃር የተፈጠረው የእስራኤሉ 'ሃሬትዝ' ጋዜጣ በዚህ ዓመት ብቻ በወረራ ከተያዘው ዩክሬን ግዛት ተጫነ እህል የያዙ አራት መርከቦች በእስራኤል መራገፋቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።
ይህንን አይነቱን እህል እንደጫነ የተጠረጠረ አንድ መርከብ እሁድ ዕለት ሃይፋ ባሕር ዳርቻ እንደደረሰ እና ወደ ወደብ ለመግባት ተራ እየጠበቀ መሆኑንም ጋዜጣው ዘግቧል።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ስይቢሃ ሰኞ ምሽት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የእስራኤል አምባሳደር ስለ ጉዳይ ማብራሪ እንዲሰጡ መጥራታቸውን አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ የተጠሩት " የተሰረቀ ሸቀጥ ወደ ሃይፋ ያጓጓዘው መርከብን በተመለከተ ዩክሬን ከዚህ ቀደም ላቀረበችው ተገቢ ጥያቄ እስራኤል ምላሽ አለመስጠቷን በተመለከተ ተቃውሞ ለማሰማት" እንደሆነ ገልጸዋል።
"አሁን ሌላ መርከብ ወደ ሃይፋ ደርሷል። እስራኤል የተሰረቀ እህል እንዳትቀበል እና ግንኙነታችን እንዳትጎዳ በድጋሚ አሳስባለሁ" ብለዋል።
ወዲያውኑ ምላሽ የሰጡት የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር በበኩላቸው የሁለቱ ወዳጅ አገራት ግንኙነት በኦንላይን ወይም በመገናኛ ብዙኃን የሚካሄድ አይደለም ብለዋል።
"እስካሁን ድረስ ውንጀላውን የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበም" ብለዋል። ጉዳዩ ግን እንደሚመረመር ገልጸዋል።
ዛሬ ጠዋት እሰጣ ገባውን የተቀላቀሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በበኩላቸው "ይህ ሕጋዊ ንግድ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም" የሚል መግለጫ አውጥተዋል።
ዩክሬን ይህንን ክስተት ለማስቀረት አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ መንገድ በሙሉ እንደተከተለች የገለጹት ዜሌንስኪ፤ ይህም ቢሆን ግን ሌላ መርከብ እንዳይጓዝ አልተደረገም ብለዋል።
"የእስራኤል ባለሥልጣናት ዩክሬንን ያከብራሉ እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነቶቻችንን ከሚያበላሹ ድርጊቶች ይቆጠባሉ ብለን እንጠብቃለን" ሲሉም አክለዋል።
ዩክሬን ከአውሮፓ አገራት ጋር በመሆን የእህል ጉዞን እና ከሽያጩ የሚገኘው ትርፍ ላይ ያነጣጠረ "ማዕቀብ" እያዘጋጀች መሆኑንም ገልጸዋል።