የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኦፔክ ነዳጅ አምራች አገራት አባልነት ልትወጣ ነው

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 60 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ አባል ሆና ከቆየችባቸው እና ዋነኛ የነዳጅ አምራች አገራት ቡድን ከሆኑት ኦፔክ እና ኦፔክ ፕላስ በሚቀጥለው ወር እንደምትለቅቅ አስታወቀች።

የነዳጅ ምርት አቅሟን በቅርቡ ያሳደገችው ኤምሬቶች፤ ይህ ውሳኔዋ እያደገ የመጣውን ዓለም አቀፍ የኤነርጂ ፍላጎት በረጅም ጊዜ ለማዳረስ እንደሚያግዛት ገልጻለች።

ኤምሬት ከአባልነት መውጣቷ ለቡድኑ ትልቅ ኪሳራ ነው። አንድ ባለሙያ ውሳኔውን "የኦፔክ ፍጻሜ መጀመሪያ" ሲሉ ገልጸውታል።

የባሕረ ሰላጤዋ አገር የኤነርጂ ሚኒስትር፤ በቡድኑ ግዴታዎች ስር የማይቀንቀሳቀስ አገር መሆን ብዙ አማራጮችን መከተል እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ኦፔክ በአውሮፓውያኑ 1960 የተመሰረተው ኢራን፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቬንዙዌላን በአባልነት ይዞ ነበር። የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም አባል አገራቱ የማይተጓጎል ገቢ እንዲያገኙ የምርት ቅንጅትን ማሳለጥ ነበር።

በዓመታት ውስጥ የቡድኑ አባል አገራት ቁጥር ተለዋውጧል። ከአምስቱ መስራች አገራት በተጨማሪ አልጄሪያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ሊቢያ፣ ናይጄሪያ እና ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ አባል ሆነዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተቀላቀለችው ከምስረታው ከ7 ዓመታት በኋላ በ1967 ሲሆን አሁን ቡድኑን ስትለቅቅ የአባል አገራት ቁጥር 11 ይሆናል። ኦፔክ ፕላስ በሚለው ጥምረት ውስጥ የታቀፉ 10 የኦፔክ አባል ያልሆኑ አገራት አሉ።

በ'ኤምኤስፒ ፋይናንሻል' የኤነርጂ ምርምር ኃላፊ የሆኑት ሶል ካቮኒክ እንደሚናገሩት ይህ ውሳኔ "የኦፔክ ፍጻሜ መጀመሪያ" ነው። "ኤምሬቶች ስትለቅቅ ኦፔክ ከአቅሙ 15 በመቶውን እና ታዛዥ አባሉን ያጣል" ብለዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈችው የዓለም ባንክ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በታሪክ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዳስከተለ ማስጠንቀቂያ በሰጠበት ወቅት ነው።

በዚህ ምክንያት የኤነርጂ ዋጋ በአማካይ በ25 በመቶ መጨመሩን የገለጸው ተቋሙ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞ ከጦርነት በፊት ወደነበረው ደረጃው ለመመለስ ስድስት ወር ሊወስድበት እንደሚችል አስታውቋል።

የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የተነሳ ኤምሬቶች ከኦፔክ ለመውጣት መወሰኗ በዓለም አቀፍ የኤነርጂ አቅርቦት ላይ ወዲያውኑ የሚታይ ለውጥ አያመጣም። በረጅም ጊዜ ግን ምርት እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል።

የምርት አቅሟን ለማሳደግ በከፍተኛ መጠን ኢንቨስት ያደረገችው ኤምረቶች፤ በረጅም ጊዜ የምታወጣውን ነዳጅ መጨመር እንደምትፈልግ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ተናግረዋል።