ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእራት ግብዣ ላይ ተኩስ የከፈተው ተጠርጣሪ ትራምፕ ላይ የመግደል ሙከራ በማድረግ ክስ ተመሰረተበት
ቅዳሜ ምሽት በዋይት ሐውስ ዘጋቢዎች የእራት ግብዣ ላይ ተኩስ የከፈተው የካሊፎርኒያ ነዋሪ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ ወንጀል ክስ ተመሰረተበት።
የ31 ዓመቱ ኮል ቶማስ አለን ሰኞ ዕለት በዋሽንግተን ዲሲ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት በሁለት የጦር መሣሪያ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል።
ቅዳሜ ዕለት የዋይት ሐውስ ዘጋቢዎች ማኅበር ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ የጸጥታ ፍተሻን ሲያልፍ ከፊል አውቶማቲክ ሽጉጥ፣ አነስተኛ ጠብመንጃ እና ሦስት ቢላዋ ይዞ እንደነበር አቃቤ ሕጎች በክሳቸው ላይ አመለክተዋል።
የደህንነት አባል የሆነ ግለሰብ በጥይት የተመታ ቢሆንም የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰበት ተገልጿል። ክስ የተመሰረተበት ግለሰብ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የእድሜ ልክ እስር ይጠብቀዋል።
ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረበው ተጠርጣሪ ዳኛው ለሚያቀርቡለት ጥያቄዎች ዝግ ባለ ለስላሳ ድምጽ "አዎ፣ ክብሩነትዎ" ወይም "አይ፣ ክብርነትዎ" ብቻ ብሎ ሲመልስ ተደምጧል።
ለፍርድ ቤቱ ዕድሜውን የገለጸው ተጠርጣሪው ሁለተኛ ዲግሪ እንዳለው ተናግሯል።
አቃቤ ሕጎች ክሱን ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርቡ ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች ከኋላው አንዱ ደግሞ ከጎኑ ቆመው ነበር።
ቅዳሜ ምሽት በነበረው የእራት ግብዣ ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ፣ የካቢኔ አባላት እና ሌሎች የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት የተኩስ ድምፅ ከተሰማ በኋላ ከዋሽንግተን ሒልተን ሆቴል አዳራሽ በፍጥነት እንዲወጡ ተደርገዋል።
ተጠርጣሪው የደህንነት ፍተሻ ስፍራውን በፍጥነት በማለፍ ወደ አዳራሹ እየሮጠ መሄዱ ተገልጿል።
ሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ቶድ ብላንቼ "አንድ የደህንነት አባል ደረቱ ላይ በጥይት ተመትቷል፤ ነገር ግን የጥይት መከላከያ በመልበሱ ጉዳት አልደረሰበትም" ብለዋል።
"ይህ ጀግና መኮንን አምስት ጊዜ በአለን ላይ የተኮሰ ሲሆን፣ በጥይት ሳይመታ መሬት ላይ ወድቆ ወዲያውኑ ተይዟል" ብለዋል።
ብላንቼ ተጠርጣሪው ጠመንጃውን ቢያንስ አንዴ መተኮሱ ይጠረጠራል። የደህንነት አባሉ የተመታው በተጠርጣሪው ይሁን ወይም ሌሎች የሕግ አስከባሪዎች በተኮሱት ተባራሪ ጥይት ግልጽ አይደለም።
የደህንነት አባሉ ሆስፒታል ገብቶ ተገቢውን ሕክምና ካገኘ በኋላ ወደ ቤቴ ሄዷል።
የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ለመግደል መሞከር የእድሜ ልክ እስራት ያስፈርዳል።
የጦር መሣሪያን ከግዛት ወደ ግዛት ማጓጓዝ እና የጦር መሳሪያን ለአመፅ ወንጀል መጠቀም ሁለቱም እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣሉ።
ተጠርጣሪው ሐሙስ ዕለት ዳግም ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ትራምፕን ለመግደል የተለያዩ ግዛቶችን ተሻግሮ መምጣቱ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ተጠርጣሪው ትራምፕን ለመግደል እአአ ሚያዝያ 21 በሎስ አንጀለስ አካባቢ ከሚገኘው ቤቱ ተነስቶ በባቡር ወደ ቺካጎ እንደተጓዘ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
እአአ ሚያዚያ 24 ከቺካጎ ወደ ዋሺንግተን በመጓዝ ከእራት ግብዣው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በሒልተን ሆቴል አርፏል።
ተጠርጣሪው ዝነኛ በሆነው የካሊፎርኒያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የተማረ ሲሆን፣ በሎስ አንጀለስ በሚገኘው ፓሳዴና ዩናይትድ ሪፍርምድ ቤተ ክርስትያን አባል ነው።
የፌደራል መንግሥቱ ባደረገው የፋይናንስ ምርመራ እአአ በ2024 ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩትን ካማላ ሃሪስ ለመደገፍ ለዲሞክራቲክ ፓርቲ የፖለቲካ ኮሚቴ 25 ዶላር ማዋጣቱን የሚያሳይ ሰነድ አግኝተዋል።
ሰኞ ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከጥቃቱ በፊት ለቤተሰቡ ጻፈው በተባለ መልዕክት ላይ የተጠርጣሪው ፍላጎት በተቻለው መጠን ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የካቢኔ አባላትን መግደል እንደሆነ ተገልጿል።
ለፍርድ ቤቱ በቀረበ ቃለ መሃላ ላይ ተጠርጣሪው ለቤተሰቡ በጻፈው መልዕክት "የአስተዳደሩን ባለሥልጣናት. . . ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ድረስ ዒላማ እንደሚያደርግ" ጠቅሷል ይላል።
አክሎም "አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ እዚህ ያሉትን አብዛኛዎቹን ዒላማዎቹን አደርግ ነበር" ማለቱ ተጠቅሷል።
አቃቤ ሕግ አለን በቁጥጥር ስር እንዲቆይ ጠይቆ የግድያ ሙከራ ክስ ሽብርተኝነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ሲል ተከራክሯል። የዋሽንግተን ጠበቃ የሆኑት ዣኒን ፒሮ ተጨማሪ ክሶች ሊቀርቡ እንደሚችሉ ጨምረው ተናግረዋል።
የሕግ አስከባሪ ምንጮች ለቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ አለን ለመርማሪዎች ትብብር እያደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የአሜሪካ መርማሪዎች በትራምፕ ላይ የተፈፀመውን ሦስተኛውን የግድያ ሙከራ ሲመረምሩ፣ የደህንነት ባለሥልጣናት ለፕሬዚዳንቱ የሚደረገውን የጥበቃ ፕሮቶኮል መገምገም ጀምረዋል።
ብዙዎች በዋሽንግተን ሒልተን ሆቴል ለፕሬዚዳንቱ የነበረው ጥበቃ ምን ያህል የተጠናከረ እንደነበር እየጠየቁ ነው።
ተሳታፊዎች መታወቂያ እንዲያሳዩ ለምን እንዳልተጠየቁ እና ፕሬዝዳንቱ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ሌሎች ተተኪዎችው በሙሉ በአንድ ቦታ ለምን እንደተሰበሰቡ ጠይቀዋል።
ሰኞ ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ብላንቼ በግብዣው ላይ የተፈጠረውን ለመከላከል "የሕግ አስከባሪዎች ድክመት አልነበረባቸውም" ሲሉ ተከላክለዋል።
አክለውም አንድ "ግልጽ" መሆን ያለበት ተጠርጣሪው ከአንድ ሕንጻ ወለል በታች ነበር "በእርሱ እና በአሜሪካው ፕሬዚዳንት መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌደራል ጸጥታ አስከባሪዎች አሉ" ብለዋል።
ዋሺንግተን ሒልተን ከ45 ዓመት በፊት ጆን ሂንክሊ ጁኒየር በወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሮናልድ ሬገንን ለመግደል ሙከራ ያደረገበት ነበር።
አንድ ከፍተኛ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ትራምፕ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሚጠብቀው የአገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ (ዲኤችኤስ) አካል ከሆነው የጸጥታ አመራር "ጎን" እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
በዚህ ሳምንት የዋይት ሐውስ ኃላፊ የሆኑት ሱሲ ዊልስ "በትልልቅ በዓላት ላይ ስለሚታዩ የደህንነት ሁኔታዎች" ለመነጋገር ስብሰባ እንደሚያካሄዱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።