የአሜሪካው አምባሳደር ህወሓትን "መጠነ ሰፊ ጥቃት" በመክፈት ወቀሱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት በተመለከተ የህወሓት አመራሮችን "መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት" ወቀሱ።

አምባሳደሩ ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ጦርነት መቀስቀሱ መገለጹን ተከትሎ ባወጡት መግለጫ ነው የህወሓት መሪዎችን አጥብቀው የወቀሱት።

የኤምባሲው ድረ ገጽ እና ማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በተሠራጨው የአምባሳደር ማሲንጋ መልዕክት፤ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ የተጣለባቸው የህወሓት መሪዎች "መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመክፈት ባሳለፉት ደካማ ውሳኔ ማዘናቸውን" ገልጸዋል።

አምባሳደሩ ጨምረውም የህወሓት አመራሮች በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሩዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደው ንግግር ውድቅ አድርገው "በማያሸንፉት ጦርነት ውስጥ መግባት ለሕዝቡ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም" በማለት ወቅሰዋል።

አምባሳደሩ ጨምረውም "ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ" በመምከር አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደተሳሳተ መንገድ ለመምራት የሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጩ እንዳላት አመከልተዋል።

ኧርቪን ማሲንጋ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ ችግሮችን ለመፍታት "ምክንያታዊ የፖለቲካ ንግግር ትክክለኛው መንገድ መሆኑን" እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

የአሜሪካው አምባሳደር በህወሓት መሪዎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ውዝግቡ በተባባሰበት ጊዜ በተደጋጋሚ ወደ መቀለ አምርተው ከህወሓት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ለማድረግ መሞካራቸው መዘገቡ አይዘነጋም።

አሁን የተቀሰቀሰው ጦርነት በህወሓት መሪዎች እንደተቀሰቀሰ በመጥቀስ ጠንከር ያለ ወቅሳ መሰንዘራቸው አሜሪካ ከህወሓት አንጻር ያላትን አቋም የሚያመለክት ነው።

ግጭቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እስካሁን ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም የጠቅላይ ሚኒስረሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ እና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የትግራይ ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልል አዋሳን አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ጦርነት መክፈታቸውን ገልጸዋል።

የአፋር ክልልም የትግራይ ኃይሎች ጥቃት እንደከፈቱ በመግለጽ ጥቃቱን እንደሚከላከል በማሳወቅ ህወሓትን ከስሷል።

በህወሓት ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የትግራይ አስተዳደር በበኩሉ ባለፉት ቀናት በፌደራል ኃይሎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ታጣቂዎቹ የመከላከል እርምጃ እንዲወስዱ ማዘዙን እና ጦርነት መቀስቀሱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ይህንን የአሜሪካውን አምባሳደር መግለጫን ተከትሎ የህወሓት ከፍተኛ አመራር እና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ በአምባሳደሩ ወቀሳ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

አቶ አማኑኤል፤ የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር በትግራይ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የአየር ጥቃቶች ሲፈጸሙ በዝምታ ቆይተው አሁን የሰነዘሩት ወቀሳ "ፍትሐዊ አይደለም" ብለውታል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም "የዲፕሎማቶቹን ፍትሐዊነት እና ገለልተኝነትን በተመለከተ በጣሙን የሚረብሹ ሌሎችም የሚያሳስቡ ጉዳዮችም አሉ" ሲሉ ተችተዋል።

የህወሓት ባለሥልጣናት በአሸማጋዮች ላይ ጥርጣሬያቸውን ሲገልጹ ይህ የመጀመሪያቸው አደይለም።

ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ያለው ሁኔታ ወደ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ተከትሎ የሽምግልና ጥረት ሲያደርጉ በቆዩት የአፍሪካ ኅብረት መልዕክተኛ ላይም ተመሳሳይ የእምነት ማጣት ቅሬታ አቅርበው ነበር።

ቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በተደጋጋሚ ወደ መቀለ በመሄድ ከህወሓት ባለሥልጣን ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፣ ተጨባጭ ውጤት ግን ማስገኘት አልቻሉም ነበር።

የአሁኑ ግጭት ከመፈጠሩ ከሳምንታት በፊት ኦባሳንጆ ስለ ገለልተኝነታቸው ለቀረበባቸው ትችት በጽሕፈት ቤታቸው በኩል በሰጡት ምላሽ ከፌደራል መንግሥቱ ትዕዛዝ እንደማይቀበሉ ገልጸው፤ የህወሓት መሪዎችን "ትኩረትን ለማግኘት ጥንቃቄ የሚፈልጉ እና ምሥጢራዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ኃላፊነት የጎደለው" ድርጊት ፈጽመለል ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል።