አሜሪካ ለሱዳኑ መሪ ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን ቪዛ ከለከለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን ወደ ግዛቷ ለመግባት ያቀረቡትን የቪዛ ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ተነገረ።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ የሱዳኑ መሪ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ነበር የአሜሪካን ቪዛ የጠየቁት።

አሜሪካ የቪዛ ክልከላውን በተመለከተ በይፋ የሰጠችው ማብራሪያ የሌለ ሲሆን፣ አንድ ምንጭ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት ቪዛውን የምትሰጠው "አል ቡርሃን ለሦስት ወራት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነትን ሲቀበሉ" እንደሆነ ገልጿል።

ነገር ግን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር በደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የሚገኘው በአል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ኃይል እንዲህ ዓይነቱ ፋታ ተቀናቃኙ መልሶ እንዲደራጅ እና ጥቃቱን እንዲቀጥል ዕድል ይሰጣል በሚል ተቃውሞታል።

የቪዛ ክልከላውን በተመለከተ የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እርምጃው ድርጅቱን እንዳሳሰበው እና ዋና ፀሐፊው አሜሪካን እንደ አስተናጋጅ አገር ያለባትን ግዴታ በመፈጸም አል-ቡርሃን በአካል እንዲሳተፉ ቪዛውን እንድትሰጥ እያሳሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽህፈት ቤት ጉዳዩ እንደተሰማ ወዲያውኑ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገር እንደጀመረ እና ውይይቱም መቀጠሉን ገልጸዋል።

ጄነራል አል ቡርሃን የአገራት መሪዎች በሚሳተፉበት በዓመታዊው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመገኘት ንግግር ለማድረግ ፕሮግራም ተይዞላቸው ነበር።

የሱዳን ጦር ኃይል በጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ከሚመራው የአገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ባለፉት ሦስት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት እያተካሄደ ሲሆን፣ ጄነራል አል ቡርሐን እንደ ሱዳን መሪ ለሁለት ጊዜያት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል።

በጄነራሉ ላይ የተጣለውን የቪዛ ክልከላ በተመለከተ አንድ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደተናገሩት አሜሪካ ቪዛውን አለመስጠቷ "ከተመድ ጋር ያላትን ስምምነት በግልጽ የሚጥስ እርምጃ ነው" ብለዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ ስለ ቪዛው ጉዳይ ባይጠቅስም፣ የሱዳን ጦር ኃይልም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ "እንዲሁም መሪዎቻቸው የሱዳንን ሕጋዊ እና ሕገመንግሥታዊ አስተዳደር አይወክሉም" ብሏል።

ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች አሜሪካ ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ጥሪ ከተቃወሙ በኋላ "ጦርነቱን የሚያቀጣጥሉ ወገኖች እና ተሳታፊዎች የሚገጥማቸውን ቅጣት ማጠናከር እንፈልጋለን" ሲሉ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት ተናግረዋል።

የአሜሪካዋን ኒው ዮርክ ከተማን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት አድርጎ የሚያቋቁመው ስምምነት አሜሪካ በአባል አገራት ተወካዮች ጉዞ ላይ ምንም ክልከላ መጣል እንደሌለባት ይደነግጋል።

የጄነራል ብዱል ፋታህ አል ቡርሃን የቪዛ ጥያቄ ውድቅ በተደረገበት በአሁኑ ጊዜ በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሱዳንን ወክለው የሚገኙት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሂያዲን ሳሌም ናቸው።

አሜሪካ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከግብፅ እና ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር በመሆን አል-ቡርሃንን እና የቀድሞ ምክትላቸውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ሞሐመድ ሃምዳን ዳግሎ ለድርድር እንዲቀመጡ ተደጋጋሚ ጥረቶች ስተዳርግ ቆይታለች።

ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን የሱዳን መንግሥትን የሚመሩት ጄነራል አል ቡርሃን በአውሮፓውያኑ 2021 በጄነራል ዳግሎ ድጋፍ መፈንቅለ መንግሥት ካካሄዱ በኋላ የተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ የእርስ በርስ ጦርነትን አስክትሏል።

ከሦስት ዓመታት በላይ በዘለቀው የሱዳን ጦርነት ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሞቱ የእርዳታ ድርጅቶች ይገምታሉ፤ ግጭቱም በዓለም ላይ ትልቁን የረሃብ እና የሰዎች መፈናቀል ቀውስ አስከትሏል።