ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የትውልድ አገራቸውን የማይወክሉ ተጫዋቾች የተሳተፉበት የዓለም ዋንጫ
በ2026ቱ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ላይ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በበለጠ የተለያዩ አገራትን ወክለው ከሚጫወቱ ተጫዋቾች መካከል ላልተወለዱባቸው አገራት ተሰልፈው የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከፍተኛ ቁጥር አላቸው። ይህም በውድድሩ ከሚሳተፉ ተጫዋቾች መካከል አንድ አራተኛውን ይሸፍናል።
የዓለም እግር ኳስ ውድድር የበላይ አካል ለሆነው ፊፋ የቀረቡ ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉት 48 ቡድኖች መካከል ስምንቱ ብቻ ናቸው ከግዛታቸው ውጪ የተወለዱ ተጫዋቾች ያላሰተፉት።
በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈች ያለችው የካሪቢያን ደሴቷ አገር ኪዩራሳው ለውድድሩ ከመረጠቻቸው 26 ተጫዋቾች መካከል አንዱ ብቻ ነው በደሴቲቱ ውስጥ የተወለደው። ኪዩራሳው የአውሮፓዊቷ ኔዘርላንድስ ንጉሣዊ መንግሥት አካል ስትሆን አብዛኛው የቡድኗ አባላት ኔዘርላንድስ ውስጥ የተወለዱ ናቸው።
ኳታር ደግሞ ለብሔራዊ ቡድኗ ካሰለፈቻቸው ተጫዋቾች መካከል አፍሪካ እስከ አውሮፓ እንዲሁም ደቡብ አሜሪካ ድረስ ካሉ አስር አገራት የመጡ ተጫዋቾችን አካታለች።
ተጫዋቾችም በራሳቸው ምርጫ ለሌሎች አገራት ተሰልፈው የሚጫወቱ ሲሆን፣ ለዚህም ማሳያ ታዋቂው ሚካኤል ኦሊሴ ይጠቀሳል። የጀርመኑ የባየር ሚዩኒክ የክንፍ ተጫዋች የሆነው ኦሊሴ የተወለደው እና ያደገው ለንደን ቢሆንም ለእናቱ የትውልድ አገር ፈረንሳይ መጫወትን መርጧል።
በ2026 የዓለም ዋንጫ የጋራ አስተናጋጅ ለሆነችው አሜሪካ ከሚሰለፉ የውጭ አገር ተወላጆች መካከል አንቶኒ ሮቢንሰን አንዱ ነው። ሮቢንሰን እንግሊዝ ሚልተን ኪይንስ ቢወለድም በአባቱ በኩል ለአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ለመሰለፍ ችሏል።
እንዲህ ያለው ተጫዋቾች የሚሰለፉባቸውን አገራት መቀያየር በአንዳንድ ቤተሰብ አባላት መካከል መከፋፈልን ፈጥሯል። በዚህም ወንድማማቾች ለተለያዩ አገራት ብሔራዊ ቡድኖች የመሰለፍ አጋጣሚን የፈጠረበት ሁኔታም አለ።
ወንድማማቾቹ ዴዚሬ እና ጉኤላ ዱዌ (ለፈረንሳይ እና ለአይቮሪ ኮስት)፣ ኒኮ እና ኢናኪ ዊሊያምስ (ለስፔን እና ለጋና)፣ ሃሪ እና ጆን ሳውታር (ለአውስትራሊያ እና ለስኮትላንድ) እና ግማሽ ወንድማማች የሆኑት ዴሪክ ሉካሰን እና ብራያን ብሮቤይ (ለጋና እና ለኔዘርላንድስ) ተሰልፈዋል።
ከዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በፊት እንዲህ ያለው አጋጣሚ የተፈጠረው ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር። ይህም ግማሽ ወንድማማቾች የሆኑት ጄሮም እና ኬቨን ፕሪንስ ቦአቴንግ ጀርመንን እና ጋናን ወክለው በሁለት የዓለም ዋንጫዎች (በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2014) ላይ በተጫወቱበት ወቅት ነው። በሁለቱም ውድድሮች ወንድማማቾቹ በሜዳ ላይ ተፋጥተው ነበር።
በኔዘርላንድስ በሚገኘው የኢራስመስ ዩኒቨርሲቲ የስደት እና የማንነት ጥናት ባለሙያ የሆኑት የደች ታሪክ ፀሐፊ እና ፕሮፌሰር የሆኑት ጊጅስበርት ኡንክ፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ እየተለወጠ ያለውን ዓለም የሚያንጸባርቅ ነው ይላሉ።
"ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ወደ 4 በመቶ የሚሆነው የሚኖረው ባልተወለደበት አገር ነው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ችሎታ ባላቸው ሠራተኞች እና በኮከብ ስፖርተኞች ዘንድ ከፍ ያለ ነው" በማለት ክስተቱ በዓለም ላይ የሚካሄደው "ፍልሰት አቅጣጫን የሚያንጸባርቅ ነው" መሆኑን አመለክተዋል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዓለም ዋንጫ ቡድኖች ውስጥ የውጭ አገር ተወላጅ የሆኑ ተጫዋቾች ቁጥር ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከፍ እና ዝቅ ሲል ተስተውሏል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት፣ የፖሊሲ እና የማኅበረሰብ ማዕከል ባደረገው ጥናት መሠረት፣አስካለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ድረስ ከትውልድ አገራቸው ውጪ ለሆነ አገር የሚሰለፉ ተጫዋቾች መጠን ከ2 በመቶ እስከ 14 በመቶ ውስጥ ቆይቶ በአውሮፓውያኑ የ2022 ኳታር የዓለም ዋንጫ ወደ 16.5 በመቶ ደርሷል።
በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ የተሳታፊ አገራት ቁጥር ከ32 ወደ 48 ከፍ ያለ ሲሆን፣ አገራቱ ያሰለፏቸው ተጫዋቾችም ቁጥር 1,248 ነው። ከዚህ ውስጥም ከሚጫወቱበት አገር ውጪ የተወለዱ የተጫዋቾች ቁጥር 289 ደርሷል፣ አጠቃላይ መጠኑም ከ23 በመቶ በላይ ከፍ ብሏል።
ፊፋ በአውሮፓውያኑ 1904 የተቋቋመው ቢሆንም በ1960ዎቹ ውስጥ ነበር መደበኛ የተጫዋቾች የዜግነት ደንቦችን ያወጣው። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ተጫዋቾች ለመረጡት የትኛውም አገር ተሰልፈው ለመጫወት ዜግነት አያስፈልጋቸውም ነበር።
ለዚህ ደግሞ በጣም ጎላ ብሎ የሚጠቀሰው ምሳሌ ሉዊስ ሞንቲ ነው። አርጀንቲናዊው አማካይ ተጫዋች በ1930 የዓለም ዋንጫ ለአገሩ ተሰልፎ ቡድኑ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ከዚያም አገር ቀይሮ በ1934ቱ ውድድር ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድን በመሰለፍ ዋንጫ አንስቷል።
በዚህም ሞንቲ በዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ላይ ለሁለት የተለያዩ አገራት የተጫወተ ብቸኛው ሰው ሆኗል።
በአውሮፓውያኑ 1962 ግን ፊፋ በውድድሩ ለሚሰለፉ ተጫዋቾች መስፈርቶችን በማውጣቱ ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ተሰልፈው መጫወት የሚፈልጉት አገር ዜግነት ሊኖራቸው እንደሚገባ እና በዚህም ከአንድ በላይ አገርን መወከል እንደማይችሉ ደንግጓል።
ነገር ግን ዜግነታቸው ያለፈቃዳቸው ለተነጠቁ ተጫዋቾች ብቻ ልዩ ሁኔታዎች የተቀመጡ ሲሆን፣ ይህም ለቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እና ለዩጎዝላቪያ ስፖርተኞች ተፈቅዷል።
በአውሮፓውያኑ በ80ዎቹ እና በ90ዎቹ መጨረሻ ላይ ከአስራ ሁለት በላይ የሚሆኑ የዩናይትድ ኪንግደም ተወላጆች የሆኑ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በአሠልጣኝ ጃክ ቻርልተን አየርላንድ ሪፐብሊክን እንዲወክሉ ተጠርተዋል። ተጫዋቾቹ ለብሔራዊ ቡድኑ የተጠሩት በአየርላንድ ዘመዶች ስላሏቸው ሲሆን፣ በወቅቱም ለቡድኑ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ፊፋ በ2004 ላይ ተጨማሪ ለውጦች በማድረግ ተጫዋቾች በወጣቶች ደረጃ አንድን አገር እንዲወክሉ እና በከፍተኛ የውድድር ደረጃ ለመረጡት ሌላ አገር እንዲሰለፉ ፈቅዶ ነበር።
ይሁን እንጂ፣ አንድ ተጫዋች ለሌላ አገር ለመጫወት የሚፈቀድለት ከዚያ አገር ጋር "ግልጽ ዝምድና" ሲኖረው ብቻ መሆኑን ፊፋ ደንግጓል። ለዚህ ደግሞ አንድ ወላጅ ወይም አያት በአገሪቱ ውስጥ የተወለደ ወይም ቢያንስ ለሁለት ዓመታት እዚያ ነዋሪ መሆን አለበት።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የነዋሪነት መስፈርቱ ወደ አምስት ዓመት ከፍ ያለ ሲሆን፣ ተጫዋቾች ደግሞ ከ21 ዓመት ዕድሜያቸው በፊት ሦስት ወይም ከዚያ በታች የሆኑ የከፍተኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ካደረጉ በኋላ ዜግነት መቀየር ይችላሉ።
የደንብ ለውጡ በርካታ ዜጎች በውጭው ዓለም ላላቸው ሞሮኮን ለመሰሉ አገራት ትልቅ ጥቅም አለው። በአውሮፓውያኑ 2010 ሞሮኮ ብሔራዊ ቡድኗን ለማጠናከር በፈረንሳይ፣ በኔዘርላንድስ እና በቤልጂየም ውስጥ መልማዮችን በማሰማራት ጎበዝ ተጫዎችችን ማደን ጀምራ ውጤት አግኝታለች።
በዚህም በአውሮፓ የሚገኙ ምርጥ ተጫዋች የሆኑ ተወላጆቿን በማሰለፍ ሞሮኮ በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ላይ ስኬታማ ለመሆን ችላለች። ባለፈው የኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ በተደረገው ጨዋታ ለግማሽ ፍጻሜ ውድድር በመድረስ ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር ለመሆን ችላለች።
በወቅቱ በሩብ ፍጻሜው ወቅት ሞሮኮ በፍጽም ቅጣት ምት ስትለያይ ግብ ካስቆጠሩት ሦስት ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ሞሮኮ ውስጥ የተወለዱ አልነበረም።
"ይህም ሞሮኮ ዲያስፖራ ተጫዋቾችን እንደ መጨረሻ አማራጭ ሳይሆን እንደ ብሔራዊ የእግር ኳስ ሥርዓቷ ወሳኝ አካል አድርጋ መያዝን የተማረች አገር ናት" ይላሉ ዶ/ር ማይሪያም ቸርቲ።
ይሁን እንጂ ተጫዋቾቹ "የሚወክሉትን ሰንደቅ ዓላማን መምረጥ" የሚባለው ጉዳይ ያለ ውዝግብ አይመጣም።
ከአውሮፓውያኑ 1998 እስከ 2015 የፊፋ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴፕ ብላተር፣ በሥልጣን ዘመናቸው ተጫዋቾች በተለይም ብራዚላውያን ዜግነታቸውን በፍጥነት የመቀየሩ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ላይ ትችት ሰንዝረው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2007 ላይ የአገራት ቡድኖች "በብራዚል ተጫዋቾች የተሞሉ" በመሆን የዓለም ዋንጫ "እውነተኛ አደጋ" ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር።
ከሕዝብ ዘንድም የሚሰማው ተቃውሞ ከባድ ሊሆን ይችላል። ትውልዱ ብራዚል የሆነው እና የስፔን ብሔራዊ ቡድን አጥቂው ዲዬጎ ኮስታ በብራዚል በተካሄደው የ2014 የዓለም ዋንጫ ላይ በተሳተፈበት ጊዜ ዜግነቱን በመቀየሩ የጩኸት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
የተለያዩ ዜግነት ያላቸውን ተማሪዎች የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ጊጅስበርት ኡንክ፣ ጉዳዩ በትምህርት ክፍሎቻቸው ውስጥ በተነሳ ቁጥር መለያየትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
አንዳንዶች ቡድናቸው በውጭ አገር በተወለዱ ተጫዋቾች ላይ የሚተማመን ከሆነ ደጋፊዎች "ቡድኑን ከራሳቸው ጋር ለማቆራኘት ይቸገራሉ" ሲሉ ይከራከራሉ። ሌሎች ደግሞ "ሰብአዊ መብትን በማንሳት 'ተዋቸው፣ ሥራቸው ነው፣ ገቢያቸው ነው' ይላሉ" ሲል አክለዋል።
ለዶ/ር ቸርቲ፣ እግር ኳስ ከማኅበራዊ ለውጦች ነጻ ሆኖ መቀጠል አይችልም "ብሔራዊ ቡድኖች ከአሁን በኋላ በድንበር ውስጥ ያለ የሕዝብ ነጸብራቅ ብቻ አይደለም። የፍልሰት፣ የታሪክ እና የዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ነጸብራቅ ጭምር እየሆነ መጥቷል።"