ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጫማ ከመስቀል ወደ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ - በድጋሚ ስሙን በደማቁ የጻፈው ሜሲ
በአውሮፓውያኑ 2016 ሌዮኔል ሜሲ ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ራሱን አግልሎ ነበር። በወቅቱ በተካሄደው በኮፓ አሜሪካ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ሜሲ የመለያ ፍጹም ቅጣት ምትን በመሳቱ አርጀንቲና በቺሊ ተሸንፋ ነበር።
አርጀንቲና በዘጠኝ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ለፍጻሜ ደርሳ ስትሸነፍ የተመለከተው ሜሲ ከዚያ በላይ ህመሙን ሊቋቋመው አልቻለም።
"ለእኔ፤ የብሔራዊ ቡድን ጉዳይ አብቅቷል" ሲል በወቅቱ ተናገረ። "የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ። ሻንፒዮን አለመሆን ያማል" ሲል ስሜቱን ገለጸ።
ይህ ከሆነ ከአስር ዓመታት በኋላ ግን አሁን ላይ ሜሲ አገሩ የዓለም ዋንጫ እንድታነሳ በመጫወት ብቻ አላበቃም። 39ኛ ዓመቱን ሊደፍን አንድ ቀን የቀረበው ሜሲ፤ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛ የጎል ብዛት ያስቆጠረ ተጫዋች ሆኗል።
ሜሲ በዓለም አቀፍ ጨዋታ ላይ ጫማ ለመስቀል ያሳለፈውን ውሳኔ መቀልበሱ ለራሱ እና ለአገሩ ወርቃማ የስኬት ዘመን እንዲጽፍ አስችሎታል።
አርጀንቲና ባለፉት ሁለት የኮፓ አሜሪካ ውድድሮች ዋንጫን ያገኘች ሲሆን፣ ከአራት ዓመት በፊት 2022 ላይ ደግሞ በአምበሏ ሜሲ እየተመራች የዓለም ዋንጫን ለሦስተኛ ጊዜ አንስታለች።
አርጀንቲና፤ ሜሲ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረበትን ያለፈውን የዓለም ዋንጫ ስታሸንፍ ከአውሮፓውያኑ 1986 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ሌላኛው አርጀንቲናዊ ኮከብ ዲዬጎ ማራዶና በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዝ ላይ ሁለት ግብ ካስቆጠረ ከ40 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሜሲ ትናንት ሰኞ ምሽት በተካሄደው ጨዋታ ኦስትሪያ ላይ ሁለት ግብ በማስቆጠር በድጋሚ ታሪክ ጽፏል።
የቢቢሲው ኮሜንታተተር ስቲቭ ቦወር "ሌላኛው የሜሲ ህያው ቅጽበት" ሲል ገልጾታል።
ሜሲ በበኩሉ "መጫወት እና ሜዳ ላይ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ያዝናናኛል" ብሏል። "ሰዎችም እንዲህ ሲሆኑ መመልከት፤ ይህንን ዓይነቱን ደስታ መስጠት መቻልም ያዝናናል" ሲል ስሜቱን አጋርቷል።
'ሀውልት ለማቆም ጊዜ የለንም'
በስምንተኛው ደቂቃ ላይ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት መሳቱ የጨዋታው አጀማመር ያማረ እንዳይሆን ቢያደርገውም ከ30 ደቂቃ በኋላ ይህ ክስተት ተረስቷል። ሜሲ የመጀመሪያው አጋማሽ ሳይጠናቀቅ በዓለም ዋንጫ ጨዋታው 17ተኛውን ግብ በማስቆጠር በጀርመናዊው ተጫዋት ሚሮስላቭ ክሎስ ተይዞ የነበረውን የከፍተኛ የግብ ብዛት ክብረ ወሰን ተረክቧል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃዎች እየተቆጠሩ ሳለ ደግሞ በሁለት ኦስትሪያ ተከላካዎች መከካል አሳልፎ በጠባብ ክፍተት መካከል ያስቆጠረው 18ተኛ ግብ ተመዝገቧል።
በቢቢሲ ራዲዮ 5 የቀጥታ ሥርጭት ላይ የነበረው ስፔናዊው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ጉሌም ባላግ "ለሊዮኔል ሜሲ ሀውልት ለማቆም ወይም በጋዜጣ ጥልቅ ትንታኔ ለመጻፍ ጊዜ የለንም። ፍጥነቱን ልንደርስበት አልቻልንም" ብሏል።
ሜሲ የትናንቶቹን ጨምሮ በ28 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች 18 ግቦችን አስቆጥሯል።
ሜሲ የዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ላይ ጫማውን የመስቀል ውሳኔውን ከቀለበሰ በኋላ ለስድስተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ የተሳተፈ ሲሆን 13 ግቦችንም አስቆጥሯል።
በአስገራሚ ሁኔታ፤ በትልቁ የዓለም እግር ኳስ መድረስ ካስቆጠራቸው 18 ግቦች ውስጥ 12 ያህሉን ያስመዘገበው ዕድሜው 35 ከሞላ በኋላ ነው።
ከግቦቹ መካከልም 18ቱን ያስቆጠረው በግራ እግሩ ነው። አራቱን ያስቆጠረው ደግሞ ከፔናሊቲ ሳጥኑ ውጪ ሆኖ ነው።
ስፔናዊው ጋዜጠኛ ባላግ "ሜሲ መሮጥ አያስፈልገውም። ተከላካዮችን ለማለፍ ከባድ ፍጥነት ጭምር አያስፈልገውም፤ የሚጫወተው በእውቀነት ነው። በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥም የምናየው ይመስለኛል" ብሏል።
ሜሲ የምንጊዜም ታላቁ እግር ኳስ ተጫዋች ነው?
ከሜሲ ጋር የተያያዙ ቁጥሮች በየጊዜው አስደማሚ መሆናቸውን ቀጥለዋል። በዚህ የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ያስመዘገበቻቸው አምስቱም ግቦች የተቆጠሩት በሜሲ ነው።
ከኦስትሪያ ጋር በነበረው ጨዋታ ግብ በማስቆጠሩም፤ በስድስት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረ ሦስተኛው ተጫዋች ሆኗል። እስካሁን ድረስ ይህ ዓይነቱ ስኬት የተመዘገበው በአውሮፓውያኑ 1958 በፈረንሳዊው ፎንቴን እና በ1970 በብራዚላዊው ሄርዚንሆ ነው።
ባለፉት ስድስት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች 10 ግቦችን አስቆጥሮ፤ ሁለት ግቦችን ማቀበል ችሏል።
የቀድሞ የዌልስ ተከላከይ የሆነው አሽሊ ውሊያምስ "እየተመለከትን ያለነው የምንጊዜም ታላቁን ተጫዋች ነው? ሊሆን ይችላል፤ ልንከራከርበት የሚገባም ጉዳይ ነው" ሲል ለቢቢሲ ዋን ቴሌቪዥን ቻናል ተናግሯል።
"ምናልባትም እርግ ኳስ ከተመለከተቻቸው [ተጨዋቾች] ሁሉ ታላቁን ተጫዋች እየተመለከትን ነው" ሲልም አክሏል።
የቀድሞው የእንግሊዝ የመሃል ተጫዋች ዳኒ መርፊም በዚህ ሀሳብ ይስማማል። "ሊዮኔል ሜሲ ባለው ነጻ ሚና የተነሳ ወደ እነዚያ ታላቅ ስፍራዎች መግባቱን ቀጥሏል" ብሏል።
"የእግር ኳስ እውቀቱ ከጣሪያው አልፏል። ክፍተት ይፈልጋል፤ የጊዜ አጠባበቁም ከተመለከትኳቸው ምርጥ ተጫዋቶች ሁሉ ይልቃል" ሲል ሀሳቡን ተጋርቷል።
የቀድሞው የፈረንሳይ አጥቂ እና የ2018 የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ኦሊቨር ጅሩ ደግሞ "አካላዊ ጉዳት እየደረሰበት አይደለም፤ ጤናማ የሕይወት ዘይቤውን በጥሩ ሁኔታ እየጠበቀ ነው። ይህንን ማድረግም አለበት ምክንያቱም ያለበለዚያ የዚህን ያህል እየተጫወትክ መቀጠል አትችልም" ሲል ተናግሯል።
"የማይታመን ነው። ጨዋታ በጨዋታ ላይ እያስከተለ እንዲጫወት ተባርኳል" ብሏል።
ይህን እንጂ አርጀንቲና በአምበሏ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ ሆናለች ወይ? የሚለው ጥያቄ ይነሳል።
የቀድሞው የእንግሊዝ አጥቂ ክሪስ ሱተን "በድጋሚ የሊዮኔል ሜሲ አስማል ለአርጀንቲና [ደርሷል]። ግቦቹ ብቻ አይደሉም፤ ለቡድኑ ያለው አስተዋጾ ጭምር እንጂ" ሲል ሚናውን ገልጾታል።
"ነገሮችን የሚያስተሳስርበት መንገድ፤ ለትላልቅ ጊዜዎች [የተፈጠረ] ትንሽ ሰው ነው።"
የአርጀንቲናው አሠልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ "አሉታዊ ጎን ብዬ የማስበው ሌሎች ተጫዋዎችም ግብ እንዲያስቆጥሩ ሊፈልግ ይችላል። ሜሲ ላይ ብቻመተማመን አይችሉም" ብሏል።
'ዞሮ ዞሮ ግን ሰው ነው'
በሽንፈት ውስጥ እንኳ ሜሲ ክብረ ወሰኖችን ይሰብራል። የግብ መረቡ ፊት ለፊት ሲገኝ በሚያሳየው ብቃት አርዕስተ ዜና ቢሆንም፤ ያልተፈለጉ ክብረ ወሰኖችም አስመዝግቧል።
ከኦስትሪያ ጋር በነበረው ጨዋታ ላውታሮ ማርቲኔዝ መጠለፉን ተከትሎ አርጀንቲና ፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቷት ነበር። ሜሲ የመታው ይህ ኳስ ከግብ መረብ ውጪ ሄዷል።
ሜሲ "በፍጹም ቅጣት ምቱ በጣም የተናደድኩበት ጊዜ ነበር፤ ምክንያቱም ስቼዋለሁ። በጣም በመጥፎ ሁኔታ ነው የመታሁት" ብሏል።
"ዕድለኛ ሆነን ያንን ሁኔታ መቀልበስ፤ መምራት እና ሦስ ነጥብ ማግኘት ችለናል" ሲልም ከጨዋታው በኋላ ተናግሯል።
ሜሲ በዚህ ምክንያት በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ፍጹም ቅጣት ምት የሳተ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከመለያ ምቶች ውጪ ሰባት ፍጹም ቅጣቶችን በመምታት እንዲሁም ሦስት በመሳት ሪከርዱን ይዟል።
ለአርጀንቲና ሲጫወት እንዲመታ ከተሰጡት 31 ፍጹም ቅጣት ምቶች ውስጥ በስድስቱ ግብ ማስቆጠር አልቻለም።
ከኦስትሪያ ጋር የነበረውን ጨዋታ ለየት የሚያደርገው ፍጹም ቅጣት ምት ከሳተ በኋላ ግብ ያስቆጠረበት የአንጀንቲና ጨዋታ መሆኑ ነው።
የቀድሞው የእንግሊዝ መሃል ተጫዋች ዳኒ መርፊም "ዞሮ ዞሮ ሜሲ ሰው ነው፤ እንዲሳሳት ይፈቀድለታል" ብሏል።
ምናልባትም ፍጹም ቅጣት ምቱን የሳተው ዕድል በተለመደው የራሱ የግብ ክህሎት በሚያስቆጥረው ግብ ክብረ ወሰኑን እንዲይዝ ሲቀናው ሊሆን ይችላል።
መርፊ፤ "ሆን ብሎ ሊሆን ይችላል የሳተው" ሲል ቀልዷል። "ምናልባት ክብረ ወሰኑን መሰበር የነበረበት በተሻለ ጎል ነው" ሲል ተደምጧል።