ለአሜሪካ 250ኛ ዓመት ልደት የተመረጡ ፓስፖርቶች ላይ የዶናልድ ትራምፕ ፎቶ አባሪ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, US State Department
የፕሬዝዳንት ዶናልድ አስተዳደር የአሜሪካን 250ኛ ዓመት ልደት ለመዘከር በቀረቡ የፓስፖርት ንድፎች ላይ የትራምፕን ፎቶግራፍ አካተተ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አርብ ዕለት በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ አዲሱን የፓስፖርት ገፆች የሚያሳይ ንድፍ ያጋሩ ሲሆን፤ ፓስፖርቱ የአሜሪካን የነፃነት እወጃ ከጀርባቸው ያደረገ የራሳቸውን ፎቶራፍ እና ፊርማን ያካተተ ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳለው ፓስፖርቱ በሚቀጥለው ሳምንት ለዜጎች ይቀርባል።
አዲሱ ፓስፖርት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የፌደራል ሕንፃዎች፣ ድረ ገፆች እና ሰነዶችን ጨምሮ የአገሪቱ ተቋማት ላይ የራሳቸው ስም እና ምሥል በመለጠፍ እያደረጉት ያለው ተከታታይ እርምጃ የቅርቡ ነው።
"የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ አዲስ ፓስፖርት እንኳን ደኅና መጣችሁ፤ ነገር ግን መልካም ሁኑ ይላል" ሲሉ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው ላይ ፅፈዋል። "እንኳን ደኅና መጣችሁ፤ ነገር ግን መልካም ሁኑ" የሚለው ፅሁፍ ትራምፕ ባገሩት የፓስፖርቱ ገፅ ላይ አይታይም።
በኤክስ ገፁ ላይ የትራምፕን ልጥፍ ያጋራው ዋይት ሐውስ አዲሱን ሰነድ "የአርበኛ ፓስፖርት" ብሎታል።
የአዲሱ ሰነድ አቅርቦት አሁን ላይ የተገደበ እና ፓስፖርቱ ለአሜሪካ ዜጎች ብቻ የቀረበ ነው።
ይህን ፓስፖርት ለማግኘት አሜሪካዊያን በበይነ መረብ ወይም በፖስታ ቤት ማመልከት አይችሉም። እንደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ፓስፖርቱ የሚገኘው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ የፓስፖርት ማዕከል በአካል በመቅረብ ብቻ ነው። በተመረጡ የልደት በዓሉን በሚዘክሩ ሁነቶች ላይም ማመልከቻዎች እንደሚከፈቱ ጠቁሟል።
አሁን ጥቅም ላይ ያለው የአሜሪካ ፓስፖርት የአሜሪካን ጨረቃ ላይ ማረፍ እና የነፃነት ሀውልትን የመሰሉ የአገሪቱን ታሪክ የሚያሳዩ ምሥሎችን የያዘ ነው።
በዋሽንግተን የፓስፖርት ማዕከል በአካል ተገኝተው የሚያመልክቱ ሁሉም አመልካቾች ይህን ልዩ ፓስፖርት እንደሚያገኙ ግን ግልፅ አይደለም።
የአሜሪካን የልደት በዓል የሚዘክረው ፓስፖርት የትራምፕን የተለየ ፎቶግራፍ እና ወርቃማ ፊርማ ይዞ ባለፈው ሚያዚያ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው።
በአዲሱ ፓስፖርት በሕይወት እና በሥልጣን ላይ ያሉ ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ፓስፖርት ላይ ምሥላቸው ሲወጣ የመጀመሪያው ይሆናል።
የአሜሪካን 250ኛ ዓመት የልደት በዓል የሚዘክሩ የትራምፕን ምሥል የያዙ የወርቅ ሳንቲሞችም ይፋ ሆነዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ የገንዘብ ኖቶች ላይ ፊርማቸው የታተመ የመጀመሪያው ሥልጣን ላይ ያሉ ፕሬዝዳንት ሊሆኑም ተቃርበዋል።
የአሜሪካን ይፋዊ ሰነዶች ላይ ስማቸውን እና ምሥላቸውን ከመማስቀመጥ ባለፈ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ በቋሚነት ስማቸውን ለመትከል እየሞከሩ ነው።
ለአብነት ያህል በኬነዲ ማዕከል ስማቸው እንዲኖር ካደረጉ በኋላ በፍርድ ቤት እርምጃቸው ተቀልብሷል።















