በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያንን እንቅስቃሴ የገታው ውሳኔ እና የመንግሥት ምላሽ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ኬንያ በአነስተኛ የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የውጭ ዜጎችን ሥራ የምታስቆምበት ቀን ሰኞ ጳጉሜ 2/2018 ዓ.ም. መጀመሩን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የንግድ ቤቶቻቸውን ዘግተው ውለዋል።

ወደ አገራቸው ለመመለስ በመጣደፍ ላይ ያሉ የሌሎች አገራት ዜጎችም በርካታ ናቸው።

የኬንያ መንግሥት በበኩሉ፣ የፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን መመሪያ ተከትሎ የተፈጠረውን ጭንቀት አላስፈላጊ እና ማንንም የሚያሰጋ እንዳልሆነ ለቢበሲ ገልጿል።

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ከዛሬ ሰኞ ጳጉሜ 2/2018 ዓ.ም ጀምሮ በየትኛውም አነስተኛ ንግድ ላይ በተሰማሩ የውጭ ዜጎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ እና ቁጥጥር እንዲደረግ ባለፈው ሳምንት ነበር ያዘዙት።

ይህን ተከትሎ በውጭ አገራት ዜጎች የተያዙ በርካታ የንግድ ተቋማት ከሰኞ ጀምሮ ዝግ ሆነው ሲሆኑ፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተዘጋጁ ያሉም በርካቶች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በብዛት የሚኖሩበት የናይሮቢው ጃምሁሪ መንደር ዛሬ ከወትሮው ተቀዛቅዞ ውሏል።

በኢትዮጵያውያን እና ኤበርትራውያን የተያዙ በርካታ የንግድ ቤቶች ተዘግተው መዋላቸውን በስፍራው ተገኝተን ባደረግነው ቅኝት ተመልክተናል።

ተዘግተው ከነበሩት የንግድ ቤቶች ውስጥ፣ በአማርኛ እና በትግርኛ ጭምር ማስታወቂያ የተጻፈባቸው አነስተኛ ምግብ ቤቶች፣ ካፌ፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች እና ፀጉር ቤቶች ይገኙበታል።

እንደወትሮው ተከፍተው ሥራቸውን የቀጠሉ የንግድ ቤቶች ያሉ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ግን ዝግ ናቸው።

የንግድ ቤታቸውን ከዘጉት የጃምሁሪ መንደር ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን መካከል የሆነ አንድ ግለሰብ፣ የተወሰኑት የንግድ ቤቶች የተዘጉት ከዓርብ ጀምሮ እንደሆነ ተናግሯል።

ለደኅንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን አስተያየት ሰጪው፣ እርሱን ጨምሮ ሌሎችም ንግድ ቤታቸውን የዘጉት፣ የፕሬዝዳንት ሩቶን ውሳኔ ተከትሎ "አጋጣሚውን መጠቀም በሚፈልጉ ግለሰቦች ዘረፋ እንዳይፈጸም በሚል ስጋት ነው" ብሏል።

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተና ኮሚሽን በስደተኝነት ተመዝግቦ ሕጋዊ ፈቃድ በማግኘት በኬንያ መኖር ከጀመረ አራት ዓመታትን ማስቆጠሩን የሚገልፀው ግለሰቡ፣ "የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ኬንያውያን ለምን ትዘጋላችሁ? ምንም አይፈጠርም ሥራችሁን ቀጥሉ እያሉን ነው። ነገር ግን ምን እንደሚፈጠር ስለማላውቅ በስጋት ንግድ ቤቴን ከዓርብ አመሻሽ ጀምሮ እንደዘጋሁ ነው" ብሏል።

ብዙዎቹ የንግድ ቤቶቻቸውን የዘጉ ቢሆኑም፣ እስካሁን ድረስ በውጭ ዜጎች የተያዙ አነስተኛ የንግድ ቤቶችን ለመዝጋት የተንቀሳቀሰ የመንግሥት ኃይል አለመኖሩን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊው በስሩ ሦስት ኬንያውያንን ጨምሮ ሰባት ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሠራ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፣ ይህን ዓይነት አስጊ ሁኔታ ሲገጥመው ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው እንደሆነም ተናግሯል።

"ሆርን ኦፍ ሬፉጂ ቮይስ" የተባለ በስደተኞች ደኅንነት ላይ የሚሠራ ድርጅት አመራር አባል መሆኑን የነገረን ሙሉቀን ወጋ አብዲ፣ እስካሁን በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተናግሯል።

ከአካባቢው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ጋር በመነጋገር የጥበቃ አባላት ተመድበው እየሠሩ መሆኑን የገለፀው ሙሉቀን፣ "የንብረት ዘረፋም ሆነ ጥቃት አልተፈፀመብንም" ብሏል።

ይሁን እንጂ 28 ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግሯል። ፖሊሶች ከዓርብ ጀምሮ ባደረጉት ቅኝት ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የላቸውም ብለው ከያዟቸው 28ቱ ስደተኞች ውስጥ አብዛኞቹ ኤርትራውያን መሆናቸውን ተናግረዋል።

የንግድ ቤቶች የተዘጉት፣ ፕሬዝዳንት ሩቶ ያደረጉትን ንግግር "በተሳሳተ መንገድ የተረዱ እና ዕድሉን ለመጠቀም የሚፈልጉ ለዘረፋ ተዘጋጁ ሰዎች እንዳሉ በስፋት ስለሚወራ ነው" የሚለው ሙሉቀን፣ የፕሬዝዳንቱ ንግግር "ግልፅነት የሚጎድለው መሆኑ" እንደሚያሰጋው አስረድቷል።

"እዚህ ያሉት አብዛኛው ስደተኞች፣ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ናቸው" ካሉ በኋላ፣ ፈቃድ ያላቸው ስደተኞች ደግሞ "በሚኖሩበት አገር አነስተኛም ቢሆን ሥራ ሠርተው እንደሚኖሩ ነው የተባበሩት መንግሥታት ሕግ የሚገልፀው። አሁን ግን የመንግሥት እርምጃ ማንን እንደሚያካትት በግልፅ የተባለ ነገር የለም" በማለት ስጋቱን አብራርቷል።

በተጨማሪም፣ የውጭ ዜጎች የከፈቷቸውን አነስተኛ የንግድ ቤቶች ዘግተው "ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ነው መንግሥት የወሰነው" በሚል "ለዘረፋ የተዘጋጁ እንዳሉ ተረድተናል" ብለዋል።

በመሆኑም ለጥንቃቄ በሚል ብዙዎቹ የንግድ ቤቶቻቸውን ለመዝጋት መወሰናቸውን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ የንግድ ተቋማትን ስለመዝጋት በመንግሥት የተጀመረ እርምጃ አለመኖሩን እርሱም አረጋግጧል።

የኤርትራውያን ስደተኞች ማኅበር የኮሚቴ አባል የሆነው ፊልሞን እዮብ ደግሞ፣ የፕሬዝዳንት ሩቶ ውሳኔ "ለውጭ ዜጎች የተፈቀዱ እና ያልተፈቀዱ የሥራ ዘርፎችን ለመለየት የሚያስችል በመሆኑ" እንደሚደግፈው ገልጿል።

ነገር ግን ውሳኔውን እንደመልካም አጋጣሚ የሚጠቀሙ ይኖራሉ የሚል ስጋት እንዳለበት በማንሳት፣ "እዚህ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያንም ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ ያሉት ለዚህ ነው" ሲል የሌሎቹን ሃሳብ አጠናክሯል።

ነገሮች እስኪረጋጉ ድረስ ስደተኞቹ ሥራቸውን አቁመው ቤታቸው እንዲቆዩ "እኛም እየዞርን ምክር እየሰጠን ነው" ሲል አክሏል።

"ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ኤርትራውያን ስም ዝርዝር በጠበቆቻችን አማካኝነት ለመንግሥት አሳውቀናል" የሚለው ፊልሞን፣ ነገር ግን "አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልጉ" የሕግ አካላት ፈቃድ የሌላቸውን እየያዙ መሆኑን አንስቷል።

የፕሬዝዳንት ሩቶ ውሳኔ፣ ከኢትዮጵያውያን እና ከኤርትራውያን በተጨማሪ፣ እንደ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ሶማሊያ ካሉ የኬንያ አጎራባች አገራት መጥተው በተለያዩ አነስተኛ ንግዶች ላይ የተሰማሩ በርካታ ሰዎችም ላይ ተፅዕኖውን አሳድሯል።

ተዘዋውረን ከቃኘናቸው የናይሮቢ አካባቢዎች አንዱ በሆነው፣ ጊኮምባ የተባለ የገበያ ስፍራ በውጭ ዜጎች የተያዙ አነስተኛ የንግድ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ተመልክተናል። የገበያ ቦታው ከኬንያውያን ውጭ የቡሩንዲ እና የሩዋንዳ ዜጎች በሚበዙበት ነው።

የቡሩንዲ ኤምባሲ ደግሞ፣ ከኬንያ ለመውጣት የሰነድ ጉዳዮችን ለማስጨረስ በሚጎበኙት የአገሪቱ ዜጎች ተጨናንቆ ውሏል። በስፍራው ያናገርናቸው ግለሰቦች፣ ውሳኔው ባሳደረባቸው ስጋት ምክንያት ወደ አገራቸው ለመመለስ መወሰናቸውን ገልፀዋል።

የቡሩንዱ ዜጎች ኤምባሲውን ያጨናነቁት፣ ኤምባሲው ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ዜጎቹ አስቸኳይ እና ነጻ የጉዞ ሰነዶች እንደሚሰጥ ካስታወቀ በኋላ ነው።

ኬንያውያን ሊሠሩ በሚችሉት አነስተኛ ንግዶች ላይ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ፕሬዝዳንቱ ያሳለፉትን ውሳኔ የሚደግፉ ኬንያውያን ብዙዎች ናቸው።

በሌላ በኩል፣ እርምጃው አብረዋቸው በሚሠሩ ሰዎች እና የንግድ ሥራቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን እንዲሁም ከሌሎች አገራት ዜጎች ጋር ትዳር የመሠረቱ ኬንያውያን ላይ እና በውጭ ዜጎች ላይ ስጋት መፍጠሩን በመጥቀስ የሚቃወሙም አሉ።

ውሳኔውን በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የውጭ አገራት ዜጎች ላይ የተፈጠረውን ዓይነት የፀረ-ስደተኞች እንቅስቃሴ ሊያስከትል የሚችል እና ሕዝባዊ ድጋፍ ለማግኘት የተደረገ ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሆነ በመግለፅ የሚተቹም እንዲሁ።

የኬንያ መንግሥት በበኩሉ፣ የፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን መመሪያ ተከትሎ የተፈጠረውን ጭንቀት ለማረጋጋት ሞክሯል። መንግሥት ማንኛውም ሰው ከአገሪቱ እንዲወጣ የሚያዝ ትዕዛዝ እንዳልተሰጠ በመግለጽ፣ የውጭ ዜጎች እና ለኢንቨስተሮች ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን አረጋግጧል።

የኬንያ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ካቢኔ ዋና ፀሐፊ ሊ ኪንያንጁይ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ይህንን ጉዳይ በደቡብ አፍሪካ በሰኔ ወር ከታየው የፀረ-ስደተኞች እንቅስቃሴ ጋር ማነጻጸርን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።

ኪንያንጁይ እንዳሉት፣ መመሪያው የሚተገበረው በመንግሥት እንጂ በሕዝብ አይደለም፤ ከሕግ ውጭ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ሰው፣ ኬንያዊም ሆነ ሌላ፣ ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድበት አስጠንቅቀዋል።

"በኬንያ እና በደቡብ አፍሪካ ባለው ሁኔታ መካከል ምንም ዓይነት ንጽጽር የለም። ጉዳዩ ከአውዱ ውጭ እንዳይወሰድ እንሠራለን። ኬንያ ወደዚህ መምጣት ለሚፈልግ ለማንኛውም የአፍሪካ አገር ዜጋ መኖሪያ መሆኗን ትቀጥላለች። ሕጋዊ በሆነ መንገድ እስከሠሩ ድረስ ከማንም ጋር ለመነጋገር እና ለመሥራት ዝግጁዎች ነን" ብለዋል።

በተጨማሪም ጉዳዩ "በፖለቲካ ወይም በሌሎች ምክንያቶች በተጋነነ መንገድ እየቀረበ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

"ፕሬዝዳንቱ ማንኛውም ሰው ዛሬውኑ አገሩን ለቆ እንዲወጣ ወይም ተመሳሳይ ነገር የሚያዝ መመሪያ አልሰጡም። ያደረጉት ነገር ከሰኞ ጀምሮ የውጭ ዜጎች ያለ ተገቢ ሰነድ በንግድ ወይም በሌላ ሥራ ላይ የሚሳተፉበትን ጉዳይ ከፓርላማው እና ከኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተዋቀረ ቡድን እንዲመረምር መመሪያ መስጠት ነው። የዚህ መመሪያ መነሻም የነጋዴዎች ተቃውሞ ነው" ሲሉ ኪንያንጁይ ገልጸዋል። አክለውም በሳምንቱ ውስጥ ዝርዝር ሪፖርት እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር በኬንያውያን ሊሠሩ በሚችሉ በተለያዩ አነስተኛ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች ላይ ከሰኞ ጀምሮ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ከገለጹ በኋላ በተለይ በዋና ከተማዋ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል።

ምንም እንኳን የፕሬዝዳንቱን ንግግር በይፋ ተግባራዊ ለማድረግ ባለሥልጣናት እርምጃ መውሰድ ባይጀምሩም ኢትዮጵያውያንን እና ኤርትራውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ሰዎች ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ከተለመደው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው ተቆጥበዋል።