የኖርዌይ ልዕልት በወንድማቸው የአገሪቱ ንጉሥ ቀብር ላይ ከተገኙ ከሁለት ቀናት በኋላ አረፉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኖርዌይ ልዕልት አስትሪድ የአገሪቱ ንጉሥ በሆኑት በወንድማቸው ንጉሥ ሃራልድ አምስተኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከተሳተፉ ከሁለት ቀናት በኋላ መሞታቸውን የኖርዌይ ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት አስታወቀ።

ልዕልቲቱ በ94 ዓመት ዕድሜያቸው ያረፉት ታናሽ ወንድማቸው ንጉሥ ሃራልድ አምስተኛ ካረፉ ከሳምንት እንዲሁም ቀብራቸው ከተፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

አዲሱ የኖርዌይ ንጉሥ ሃኮን ስምንተኛ የልዕልቱቱን ኅልፈት ተከትሎ "ልዕልት አስትሪድ በረጅም ዘመናቸው ሁሉ ንጉሣዊ ቤተሰቡን በቀናነት እና በታማኝነት ወክለዋል" ብለዋል።

ንጉሥ ሃራልድ ባለፈው ነሐሴ ወር በ89 ዓመታቸው ከ35 ዓመታት በላይ በንግሥና ከቆዩ በኋላ ነበር ያረፉት። ልዕልቲቱ በመጨራሻ ለሕዝብ የታዩት በወንድማቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት ነበር።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋር ስቶሬ እንደገለጹት፣ በመላው ኖርዌይ ሰንደቅ ዓላማዎች ለሐዘን መግለጫ ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ ተደርገው ለልዕልቷ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

አስትሪድ ከአውሮፓውያኑ 1957 እስከ 1991 ድረስ የኖርዌይ ንጉሥ የነበሩት የንጉሥ ኦላቭ አምስተኛ በሕይወት የቀሩ ልጅ ነበሩ።

በ1954 እናታቸው ዘውዳዊት ልዕልት ማርታ ከሞቱ በኋላ፣ አባታቸው ንጉሥ ኦላቭ ዳግም ሌላ ሚስት ባለማግባታቸው ልዕልት አስትሪድ በ22 ዓመታቸው የኖርዌይ ቀዳማዊት ዕመቤት ሆነው ነበር። በዚህም ልዕልቲቱ ወንድማቸው ንጉሥ ሃራልድ በአውሮፓውኑ 1968 እስኪያገቡ ድረስ ቀዳማዊ ዕመቤት ሆነው ቆይተዋል።

ንጉሥ ሃኮን በመግለጫቸው "ልዕልት አስትሪድ በሥራቸው ሁልጊዜ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሚገኙት ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እንክብካቤ እና ተሳትፎ ልዩ ትኩረት ይሰጡ ነበር" ብለዋል።

የልዕልቲቱ የጤና ሁኔታቸው ከቅርብ ወራት ወዲህ አሳሳቢ እንደሆነ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፣ በመጋቢት ወርም በሳንባ ምች ምክንያት ሕክምና ተደርጎላቸው ነበር።

ረቡዕ ዕለት በተካሄደው የንጉሥ ሃራልድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የዌልስ ልዑልን ጨምሮ ሦስት የኖርዲክ አገራት ነገሥታት፣ በርካታ የአውሮፓ ንጉሣዊ ቤተሰቦች እና የአገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

በዚያው ቀን ከንጉሣዊ ቤተ መንግሥት እስከ ኦስሎ ካቴድራል በተደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰልፍ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ነበር።

ለሟቹ ንጉሥ አክብሮታቸውን ለመግለጽ ከተገኙት መካከል የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ፣ የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ-ዋልተር ስታይንማየር እና አምስት የውጭ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ይገኙበታል።

ንጉሥ ሃራልድ በሕይወት ዘመናቸው የመጨረሻ ወራት፣ የኖርዌይ ንጉሣዊ ቤተሰብ የግል ፈተናዎች እና ውዝግቦች አጋጥሞት ነበር።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የወጡ ሰነዶች አሁን መንበሩን የተረከቡት የንጉሥ ሃኮን ባለቤት ንግሥት ሜቴ-ማሪት ከአሜሪካዊው የወሲብ ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር ተደጋጋሚ ግንኙነት እንደነበራቸው አሳይተዋል። ንግሥቲቱም በኋላ ከዚያ በወንጀል ከተወገዘው ባለሀብት ጋር "በፍጹም ባልተዋወቁ" ሲሉ ጸጸታቸውን ገልጸው ነበር።

በሌላ በኩል፣ ንግሥቲቱ ከቀድሞ ትዳራቸው የወለዱት ምንም እንኳን የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ባይሆንም በቤተሰቡ ውስጥ ያደገል ጃቸው ማርየስ ቦርግ ሆይቢ፣ በሰኔ ወር በሁለት የመድፈር ክሶች የአራት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ሆይቢ በፍርዱ ላይ ይግባኝ እስኪያቀርብ ድረስ በቁም እስር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በንጉሥ ሃራልድ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲገኝ ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር።