ዐቃቤ ሕግ በቤታቸው የወርቅ ጥፍጥፍ የተገኘባቸውን የቀድሞ የሲአይኤ ባለሥልጣን 'የማጭበርበር ልሂቅ' ሲል ከሰሰ

የወርቅ ጥፍጥፎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) የቀድሞ ባለሥልጣን የነበሩት ዴቪድ ረሽ በመኖሪያ ቤታቸው 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የወርቅ ጥፍጥፎች መገኘታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ "የማጭበርበር ልሂቅ" ናቸው ሲል ወነጀለ።

ግለሰቡ ቨርጂኒያ በሚገኘው ቤታቸው በርካታ ጥፍጥፍ ወርቅ ከተገኘ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የ49 ዓመቱ የቀድሞው የሲአይኤ ባለሥልጣን አውሮፕላን አብራሪ እንደሆኑ ለጎረቤቶቻቸው "ሲዋሹ ነበር" ብሏል ዐቃቤ ሕግ።

ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መታየት እስከሚጀምር ድረስም በእስር እንዲቆዩ ውሳኔ ተላልፏል።

ጠበቆቻቸው "የቀረቡት ክሶች ተጋንነዋል። አንዳንዶቹ ትርጉም የማይሰጡ እና ምሥጢራዊም ናቸው" ሲሉ ተከራክረዋል።

የስለላ ሥራ ምሥጢራዊ ስለሆነ ከቀረቡት ክሶች አንዳንዶቹ "ምሥጢራዊ" መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የቀድሞው ባለሥልጣን መኖሪያ ውስጥ ፍተሻ ሲደረግ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ እና በርካታ ቅንጡ ሰዓቶች እንደተገኙ ተገልጿል።

ትናንት በቨርጂኒያ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ዐቃቤ ሕግ "ዴቪድ ረሽን ማመን አይቻልም። ሕግ ለመቀልበስ ፈቃደኛነቱም፣ ችሎታውም አላቸው" ማለቱን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዴቪድ ረሽ ቨርጂኒያ በሚገኘው የአሜሪካ የስለላ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበሩ። በምሥጢር የተያዙ መረጃዎችን እና የፍርድ ቤት ሰነዶችን ማግኘት የሚያስችላቸው የይለፍ ፈቃድ ነበራቸው።

ሲቢኤስ እንደዘገበው፤ ዴቪድ ለሲአይኤ እየሠሩ ሳለ ኤፍቢአይ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ምርመራ አድርጎባቸዋል።

የሕዝብ ገንዘብ በመመዝበር የወንጀልም ክስ ተከፍቶባቸዋል። ባለፈው ወር የቀረበባቸው ክስ በተጭበረበረ ሰነድ 70,000 ዶላር ማግኘትን ይመለከታል።

በአውሮፓውያኑ ከኅዳር 2025 እስከ ሚያዝያ 2026 ድረስ "ከሥራ ጋር ለተያያዙ ወጪዎች ክፍያ" ጥፍጥፍ ወርቅ እና የውጭ ምንዛሬ እንደተሰጣቸው ተገልጿል። ሲአይኤ ጥፍጥፍ ወርቆቹን ማግኘት አልቻለም።

ኤፍቢአይ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ከ300 በላይ የሚደርሱ ጥፍጥፍ ወርቆች ወደ 40 ሚሊዮን ዶላር ያወጣሉ። 2 ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ እና ከ30 በላይ ቅንጡ ሰዓቶችም በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተዋል።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው፤ ዴቪድ ረሽ የተከማቸ ገንዘብን መሸጥ ወደሚቻል ንብረት እየለወጡ እንደሆነ "ጠንካራ ማስረጃ" አግኝቷል። ገንዘቡን በቤታቸው ለመደበቅ መሞከራቸውም ተገልጿል።

ከአሜሪካ ባሕር ኃይል በክብር ከተሰናበቱ በኋላ አጭበርብረው ወታደራዊ እረፍት እንደወሰዱ በፍርድ ቤት ተገልጿል።

ሥራ ሲያመለክቱ ስለ ወታደራዊ አገልግሎታቸው እና የትምህርት ደረጃቸው መዋሸታቸውም ተመልክቷል። ለቀጣሪዎች ባሕር ኃይል ውስጥ አውሮፕላን አብራሪ መሆናቸውን በሐሰት ሲናገሩም ነበር።

ጠበቃቸው ጀሲካ ካረማይክል በበኩላቸው በቤታቸው የተገኘው ጥፍጥፍ ወርቅ "ምንጩ የሚታወቅ ስለሆነ አሳሰቢ ጉዳይ አይደለም" ብለዋል።

ኤፍቢአይ ቤታቸውን ሲፈትሽ ስለ ወርቁ መናገራቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

የኤፍቢአይ ባልደረቦች ወርቁ ወዳለበት ክፍል እንዲገቡ የይለፍ ቃል በመስጠት መተባበራቸውን ጠቅሰዋል።

"ጥፍጥፍ ወርቁ የእሳቸው መሆኑን አልገለጹም። ስለዚህ መንግሥት ወርቁን ማሳየቱ ስህተት ነው" ብለው ተከራክረዋል።

ዴቪድ ረሽ በለይቶ ማቆያ ክፍል ውስጥ የታሰሩ ሲሆን በቀን ለሁለት ሰዓት ብቻ እንዲወጡ ይፈቀድላቸዋል።

ዳኛው በእስር መቆየት እንዳለባቸው ሲገልጹ ግለሰቡ የስለላ ባለሙያ መሆናቸውን በመጥቀስ "ከሌሎች ሰዎች በተለየ ከሕግ የማምለጥ ችሎታ አላቸው" ብለዋል።