ቀጥታ, ኢራን ሠራዊቷ መጠናከሩን ስትገልጽ፣ እስራኤል ደግሞ የኢራን መንግሥት መሠረቱ ተናግቷል አለች

ኢራን የጦር ሠራዊቷ ከጦርነቱ በኋላ የበለጠ መጠናከሩን ስትገልጽ፣ እስራኤል ደግሞ የኢራን መንግሥት ክፉኛ ተዳክሞ ሊወድቅ መቃረቡን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን ሠራዊቷ መጠናከሩን ስትገልጽ፣ እስራኤል ደግሞ የኢራን መንግሥት መሠረቱ ተናግቷል አለች

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ
    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

    ኢራን የጦር ሠራዊቷ ከጦርነቱ በኋላ የበለጠ መጠናከሩን ስትገልጽ፣ እስራኤል ደግሞ የኢራን መንግሥት ክፉኛ ተዳክሞ ሊወድቅ መቃረቡን ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።

    የኢራን ሠራዊት የተኩስ አቁም በተደረገበት ጊዜ በሁሉም መስኩ ለውጊያ ዝግጁ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የአብዮታዊው ዘብ ቃል አቀባይ ገለጹ።

    ሁሴን ሞሄቢ እንደተናገሩት "በተኩስ አቁሙ ወቅት የሠራዊታችን ተልዕኮ የመፈጸም አቅም ጨምሯል፣ በተፈጠረው ዕድልም የውጊያ አቅሙ፣ ጥንካሬው፣ ዝግጁነቱ እና አደጋን የመቋቋም ብቃቱ ተጠናክሯል። በአሁኑ ወቅትም ጦሩ ቀደም ሲል ከነበረው አቋም በተሻላ ሁኔታ ላይ ይገኛል” ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የኢራን መንግሥት በደረሰበት ጥቃት መሠረቱ መናጋቱን እና መውደቁ የማይቀር መሆኑን በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የዚህ የሽብር አገዛዝ መሠረቱ ተናግቷል” በማለት “አገዛዙ ከዚህ በኋላ ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ ፈጽሞ አይመለስም፤ መውደቁ እንደማይቀር እነግራችኋለው” ሲሉ የኢራን መንግሥት መዳከሙን አመልክተዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን አስተያየት የሰጡት የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በተመሳሳይ እስራኤል ክፍኛ መዳከሟን ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ጠቅላይ መሪው በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት “አስራኤል መጪዎቹን 15 ዓመታት አታይም” በማለት ትጠፋለች የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።

    እስራኤል በኢራን ላይ ሁለት ጊዜ ጥቃቶችን የፈጸመች ሲሆን፣ ኢራን በበኩሏ ከባድ የአጸፋ ምላሽ በሚሳዔሎች እና በድሮኖች ፈጽማለች።

    ባለፈው የካቲት እስራኤል ከአሜሪካ ጋር አብራ በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።

    ኢራንም በበኩሏ በእስራኤል እና በአካባቢው ባሉ የአሜሪካ አጋሮች ላይ ተከታታይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን በመፈጸም ከባድ ጉዳትን አድርሳለች።

  2. ፕሬዝዳንት ሩቶ በአሜሪካ የሚቋቋመውን የኢቦላ ህክምና ማዕከልን ሲደግፉ ፍርድ ቤት ዕግዱን አራዘመ

    ሰልፈኛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ የሚከፈተውን የኢቦላ ህክምና ማዕከልን በመቃወም በተካሄደ ሰልፍ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል

    የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተቃውሞ የገጠመውን የኢቦላ ተጠርጣሪዎችን ለመለየት የሚያስችል ማዕከል ለማቋቋም ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ቢደግፉም የአገራቸው ፍርድ ቤት ግን በማዕከሉ ላይ የጣለውን ዕገዳ አራዘመ።

    ላይኪፒያ በተባለችው የኬንያ ማዕከላዊ ግዛት ውስጥ የሚከፈተውን የህክምና ማዕከል በመቃወም ከተካሄደው ሰልፍ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ ጋር የሚቋቋመው የህክምና ማዕከል ኬንያውያንን ጭምር የሚጠቅም የጋራ ስምምነታቸው አካል መሆኑን እና ኬንያ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እንዲሁም ህሙማንን ለማከም የሚያስችላት መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህንን በተናገሩበት ጊዜ የኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከአሜሪካ እና ከሌላ ከማንኛውም የውጭ መንግሥት ጋር በሚደረግ ስምምነት የሚመሠረት እና ሥራ ላይ የሚውል የኢቦላ ህሙማን መለያ ተቋምን የሚያግደውን ጊዜያዊ ውሳኔውን አራዝሟል።

    ፍርድ ቤቱ ዛሬ ባስተላለፈው ውሳኔ የኬንያ መንግሥት በሰባት ቀናት ውስጥ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የተደረሰውን አወዛጋቢ ስምምነት ይፋ እንዲያደርግ አዝዟል።

    በተጨማሪም መንግሥት እና ሌሎች አካላት “ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት እስኪያገኝ ድረስ የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ከመክፈት፣ ሥራ ከማስጀመር፣ ፈቃድ ከመስጠት እና ከማጽደቅ እንዲታቀቡ” ውሳኔውን አጽንቷል።

    የለይቶ ማቆያ ማዕከሉ ይቋቋምበታል በተባለው በማዕከላዊ ኬንያ ናኙኪ ከተማዋ ውስጥ ውጥረት የተፈጠረ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የህክምና ማዕከሉ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ በመጥቀስ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

    በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረው ግጭት ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መሞታቸው ተዘግቧል።

  3. ተመድ እስራኤል የሊባኖስን አምባ መቆጣጠሯን በተመለከተ አስቸኳይ ውይይት አካሄደ

    የፀጥታው ምክር ቤት

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እስራኤል የሊባኖስን ጥንታዊ አምባ - ቢውፎርትን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን በተመለከተ ትናንት አስቸኳይ ውይይት አካሄደ።

    በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫስሊ ነቤንዝ “እስራኤል እና ሊባኖስ በአሜሪካ አሸማጋይነት የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ከለላ ሰጥቷል” ብለዋል። ሊባኖስ የጋዛ ሰርጥ እጣ ፈንታ እንደሚጠብቃትም አክለዋል።

    በተመድ የፈረንሳይ ልዑክ ጀሮም ቦንፎን ውይይቱ እንዲካሄድ አገራቸው ጥሪ ማቅረቧን ጠቅሰው “እስራኤል ራሷን የመለካከል መብት ቢኖራትም ሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት ምክንያታዊ አይደለም” ብለው ንግግር አድርገዋል።

    በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን እንደተጎዱ እና እንደተፈናቀሉ የፈረንሳዩ ተወካይ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ተወካይ ማይክል ጄ ዋልዝ በበኩላቸው፤ድርድርን ጨምሮ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

    “ሕጋዊው የሊባኖስ መንግሥት በቴህራን ከሚደገፈው አሸባሪ አገሪቱን ነጻ ለማውጣት ተነሳሽነት አሳይቷል” ብለዋል።

    የሊባኖስ ተዋካይ አሕመድ አራፋ ደግሞ መንግሥታቸው ነገሮችን ለመቆጣጠር ቢሞክርም “እስራኤል እንደ ሁልጊዜው ቀጣናዊውን ሁኔታ እየተጠቀመችበት ነው” ብለዋል።

    እስራኤል ሐኪሞችን፣ ሆስፒታሎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና የፀጥታ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ “ስልታዊ የውድመት ዘመቻ” መክፈቷንም ጠቅሰዋል።

    በተመድ የእስራኤል ልዑክ ዳኒ ዳኖን “አንድ ቀን ተነስተን ሊባኖስ ለመግባት አልወሰንም። አማራጭ አጥተን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ኢራን ሄዝቦላህን በእጅ አዙር መጠቀም መቀጠሏን ጠቅሰው፤ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም “ሄዝቦላህ ሚሳዔል እና ድሮን መተኮስ” እንዳላቆመ ተናግረዋል።

  4. በቀጣይ ሳምንት ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ትራምፕ ተናገሩ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ለማራዘም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት በቀጣይ ሳምንት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኤቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናገሩ።

    “አሁን ላይ ነገሮች በጣም ጥሩ ናቸው። ውስን ችግር ነበር፤ ነገር ግን እንዳያችሁት በፍጥነት ፈትቼዋለሁ” ሲሉ በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

    ትራምፕ ችግር ብለው የጠቀሱት እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት ኢራንን ማስቆጣቱን ነው።

    ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረስ እንዲያቆም ከአሜሪካ የቀረበለትን ሐሳብ መቀበሉን ሊባኖስ አስታውቃለች። እስራኤልም በሊባኖስ መዲና ቤሩት ጥቃት ላለመፈጸም መስማማቷም ተገልጿል።

    ትራምፕ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከሄዝቦላህ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው “ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል” ብለዋል።

    ትራምፕ “ሄዝቦላህን አትተኩሱ ብያቸዋለሁ። ቢቢ [ኔታንያሁ] እንዳይተኩስም ነግሬዋለሁ። ሁለቱም ተኩስ አቁመዋል” ሲሉም አክለዋል።

    በቀጣይ ሳምንት የሆርሙዝ ወሽመጥ ይከፈታል ብለው እንደሚያምኑም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

  5. ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 16 ሰዎች ተገደሉ

    ሞስኮ የፈጸመችው ጥቃት በነዳጅ ማደያ እሳት አቀጣጥሏል።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሩሲያ በዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 16 ሰዎች እንደተገደሉ እና ብዙዎች እንደቆሰሉ ተገለጸ።

    በዲፕሮ ከተማ 11 ሰዎች ሲገደሉ 25 ሰዎች ተጎድተዋል። ዛሬ ንጋት ላይ በደረሱ ጥቃቶች በመዲናዋ ኪቭ አምስት ሰዎች መገደላቸው እና 51 መቁሰላቸውም ተዘግቧል፤ 35 ያህሉ ደግሞ ሆስፒታል ገብተዋል።

    የኪቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊሽኮ እንዳሉት ሁለት ግዙፍ የመኖሪያ ሕንጻዎች የተመቱ ሲሆን፤ ሰዎች በፍርስራሽ ሥር ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

    ዩክሬን ባለፈው ወር የድሮን ድብደባ በመፈጸሟ በምላሹ “ስልታዊ ጥቃት” ለማድረስ ሞስኮ ስትዝት ቆይታለች።

    ሩሲያ በቁጥጥሯ ሥር ባዋለችው የዩክሬን ሉሀንስክ ግዛት በደረሰው የድሮን ጥቃት 21 ሰዎች ተገድለዋል።

    የኪቭ ከንቲባ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። “ጠላታችን በባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት እየፈጸመ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

    በአብዛኞቹ የዩክሬን ከተሞች የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሎች እየተሰሙ ነው። በማዕከላዊ ኪቭ ጭስ መታየቱም ተገልጿል።

    በሌላ በኩል በሩሲያ ኢልስኪ የነዳጅ ማቀነባበሪያ የደረሰ ጥቃት እሳት ማስነሳቱ ተገልጿል።

    ኪቭ ውስጥ የበርካታ ድሮኖች እና ፍንዳታ ድምጽ እየተሰማ ይገኛል። ሞስኮ የፈጸመችው ጥቃት በነዳጅ ማደያ እሳት አቀጣጥሏል።

    ጥቃት የደረሰበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  6. ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሱን ለማቆም መስማማቱን ሊባኖስ ገለጸች

    ቤሩት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረስ እንዲያቆም ከአሜሪካ የቀረበለትን ሐሳብ መቀበሉን ሊባኖስ አስታወቀች።

    እስራኤልም በሊባኖስ መዲና ቤሩት ጥቃት ላለመፈጸም መስማማቷም ተገልጿል።

    አሜሪካ የሚገኘው የሊባኖስ ኤምባሲ “አሜሪካ ሁለቱም ወገኖች ጥቃት እንዳያደርሱ ያቀረበችውን ምክረ ሐሳብ ሄዝቦላህ ተቀብሏል” ብሏል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ስምምነት ላይ መደረሱን አረጋግጠዋል።

    ሆኖም “ሄዝቦላህ ከተሞቻችን እና ዜጎቻችን ላይ ጥቃት ከፈጸመ ግን ቤሩትን እንደበድባለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኔታንያሁ እና ከሄዝቦላህ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው “ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል” ብለዋል።

    እስራኤል በሊባኖስ የምታደርሰው ጥቃት የኢራን እና አሜሪካን የተኩስ አቁም ስጋት ውስጥ እንደሚጥል ቴህራን መግለጿ ይታወሳል።

    የሊባኖስ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ “ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት ካልፈጸመ እስራኤልም በቤሩት ጥቃት እንደማታደርስ ተስማምተናል” ብሏል።

    የተኩስ አቁሙ በሒደት “ሌሎች የሊባኖስ አካባቢዎችን እንደሚሸፍን” ተገልጿል።

    ኔታንያሁ በበኩላቸው “የእስራኤል መከላከያ ኃይል በታቀደው መሠረት በደቡብ ሊባኖስ ዘመቻውን ይቀጥላል” ብለዋል።

    ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን ትራምፕ ከገለጹ በኋላ የተወሰኑ ግጭቶች መነሳታቸው ተዘግቧል።

  7. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነትን ለማረም ፍላጎት እንዳላቸው ተነገረ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሦት ወራት በፊት የተጀመረውን የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ለመቋጨት የሚያስችለውን ስምምነት ለማስተካከል ፍላጎት እንዳላቸው የዋሽንግተን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ለውጦቹ በሆርሙዝ ወሽመጥ እና የተብላላ የዩራኒየም አወጋገድ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

    ዋይት ሐውስ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።

    የኢራን ዋና ተደራዳሪ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ እሑድ ዕለት የኢራን መብት ሙሉ ለሙሉ እስካልተጠበቀ ድረስ ቴህራን ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም ብለዋል።

    የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም በሚያስችለው ማዕቀፍ ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር አርብ ዕለት ለንግግር ቢቀመጡም፤ ስብሰባው ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ግልፅነት ሳይኖረው ተጠናቋል። ሙሉውን እዚህ ያንብቡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነትን ለማረም ፍላጎት እንዳላቸው ተነገረ