"አባት አልሆንም ብዬ ነበር"- ወላጆች ልጅ እንዲያገኙ የሚያደርገው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ

የዘር ፍሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የወንዶችን የዘር ፍሬ ማግኘት የሚችል አዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ይፋ መደረጉ ለበርካቶች አባት የመሆን ተስፋ ሰጥቷል።

ቴክኖሎጂው የዘር ፍሬ እንደሌላቸው የተነገራቸው ወንዶች ሰውነት ውስጥ የዘር ፍሬ ፈልጎ የሚያገኝ ነው።

አሜሪካ ኒው ጀርሲ ውስጥ የምትኖረው ፔነሎፒ ከሥራ ወደ ቤት እየነዳች ሳለ ከዶክተሯ ተደወለላት።

ለሁለት ዓመት ተኩል ስትጠብቀው የነበረው ዜና ነበር። ነፍሰ ጡር መሆኗን ዶክተሩ ነገራት።

ባለቤቷ ሳሙኤል ከፍተኛ ኤክስ ክሮሞዞም ያላቸው ወንዶችን የሚያጠቃ ሕመም (Klinefelter syndrome) አለበት።

ይህ ሕመም ያለባቸው ሰዎች የዘር ፍሬ የላቸውም አልያም በውስን መጠን የሚገኝ ነው።

የዘር ፍሬ አለመኖር ወይም የመጠን ውስንነት (azoospermia) መውለድ ከማይችሉ ወንዶች 10 በመቶ ያጋጥማቸዋል።

ፔነሎፒ እና ሳሙኤል (ስማቸው ተቀይሯል) ልጅ መውለድ እንደሚችሉ ሲነገራቸው ደስታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም።

"ፊቱ ላይ የደስታ ስሜት ይነበብ ነበር። አለቀሰ። ብዙ የደከምንበት ነገር ነው። አንድ እንቁላል ብቻ ነበረን። ጽንስ በመፈጠሩ ከመጠን ያለፈ ደስታ ነው የተሰማን" ስትል ባለቤቷ ዜናውን የሰማበትን ቅጽበት ትገልጻለች።

የዘር ፍሬን ለመለየት የሚውለው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዘ ስታር (Sperm Track and Recovery) ይባላል።

ቴክኖሎጂውን የፈጠረው ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ነው። "የተደበቁ" የዘር ፍሬዎችን ፈልጎ የሚያገኝ እንደሆነም ተገልጿል።

"ፈርቼ ነበር። ልጆች አይኖሩኝም ብዬ ሰግቼ ነበር። ልጅ መውለድ በጣም እፈልግ ነበር" ይላል ሳሙኤል።

ልጆች የመውለድ ዕድሉ 20 በመቶ እንደሆነ ሲነገረው በጣም አሳዝኖታል።

የዘር ፍሬ ፈልጎ የሚያገኘው ቴክኖሎጂ

የፎቶው ባለመብት, Columbia University Fertility Center

የምስሉ መግለጫ, የዘር ፍሬ ፈልጎ የሚያገኘው ቴክኖሎጂ

በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ልጅ መውለድ አይችሉም።

መውለድ በሚችሉ ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ስድስት ሰዎች አንደኛቸው ችግሩ ይገጥማቸዋል። ከዚህ ቁጥር ውስጥ 50 በመቶው ወንዶች ናቸው።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች ያላቸው የዘር ፍሬ መጠን አነስተኛ ስለሆነ የዘር ፍሬያቸውን ለማግኘት ከባድ ይሆናል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካኝነት ግን የተደበቁ የዘር ፍሬዎችን ማግኘት ተችሏል።

ለአምስት ዓመታት ጥናት የተደረገበት ቴክኖሎጂ ለሁለት አሥርታት ልጅ ለማግኘት ሲሞክሩ የነበሩ ጥንዶች በስተመጨረሻ ወላጆች እንዲሆኑ አስችሏል።

የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ሥነ ተዋልዶ ክፍል ዳይሬክተር ዘቭ ዊልያምስ "ሁሉም ሰው በደስታ ሲዘል ነበር። ያ ሁሉ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ሴት ልጅ ተወልዳለች። ከፈጣሪ ጋር ሌሎችም ልጆች ይወለዳሉ" ይላሉ።

የመጀመሪያዋ ልጅ ከተወለደች በኋላ ቴክኖሎጂው በስፋት እየተተገበረ ነው።

ጽንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመላው ዓለም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወላጆች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም እየተጠባበቁ ነው። እስካሁን 175 ሰዎች በቴክኖሎጂው ተጠቅመዋል።

ዘቭ ዊልያምስ እንደሚናገሩት፤ ከ30 በመቶ በታች በሆኑ ኬዞች ላይ የዘር ፍሬ ማግኘት ችለዋል። እነዚህ ሰዎች የዘር ፍሬያቸውን ተጠቅመው ልጅ መውለድ የሚችሉበት ዕድል ያልነበራቸው ናቸው።

የሕክምና ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም የዘር ፍሬ ከሚፈልጉበት መጠን ጋር ሲነጻጸር ቴክኖሎጂው 40 እጥፍ የተሻለ ነው።

በአንድ ሚሊ ሊትር የዘር ፍሬ ናሙና ውስጥ በአሥር ሚሊዮን የሚቆየሩ የዘር ፍሬዎችን ማግኘት ይቻላል።

በአጉሊ መነጽር የዘር ፍሬ ናሙናው መጠን እና ጤናማነት ይመረመራል።

የዘር ፍሬ አለመኖር ወይም የመጠን ውስንነት (azoospermia) ባለባቸው ሰዎች ላይ አንድ የዘር ፍሬ ብቻ ሊገኝ ይችላል። በብዙዎቹ ናሙናዎች ከነጭራሹ የዘር ፍሬ አይኖርም።

ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ከዋክብትን ማግኘት እንደሚቻል በአውሮፓውያኑ 2020 ዜና ከወጣ በኋላ ቴክኖሎጂውን የዘር ፍሬ ፍለጋ ለማዋል ማሰባቸውን የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ሥነ ተዋልዶ ክፍል ዳይሬክተር ዘቭ ዊልያምስ ይናገራሉ።

በቴሌስኮፕ የሚታዩ ከዋክብት ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር በሰው ኃይል ለይቶ ለመጨረስ ከባድ ስለሆነ ነበር የሰው ሠራሽ አስተውሎት እርዳታ ያስፈለገው።

የዘር ፍሬ ቆጠራ

የፎቶው ባለመብት, Columbia University Fertility Center

የምስሉ መግለጫ, ቴክኖሎጂው በሰከንዶች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥሎችን ተመልክቶ የዘር ፍሬ ማግኘት ይችላል።

"ሰማይ ላይ ከዋክብት ሲፈለጉ ያለው ምሥል የወንዶችን የዘር ፍሬ ስንፈልግ ካለው ጋር ይመሳሰላል" ይላሉ።

ናሙናዎችን የሚመለከቱት ከፍተኛ ጥራት ባለው ቴክኖሎጂ ነው። በሰከንዶች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥሎችን ተመልክቶ የዘር ፍሬ ማግኘት ይችላል።

የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ሥነ ተዋልዶ ክፍል ባለሙያዎች ከሰው ፀጉር ጋር የሚስተካከል መጠን ያለው የጠርሙስ መስታወት ውስጥ የዘር ፍሬ ናሙናዎችን አስቀምጠው ይመረምራሉ።

ናሙናው በመስታወቱ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ምሥሎች መውሰድ ስለሚቻል የያዘውን የዘር ፍሬ መጠን ለመፈተሽ ይውላል።

የዘር ፍሬዎች ሲገኙ ቴክኖሎጂው ለይቶ በማውጣት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይከላከላል።

አይቪኤፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዘቭ ዊልያምስ እንደሚሉት የዘር ፍሬው በመስታወቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ሳለ በአንድ ሰከንድ 300 ፎቶዎች ያነሳሉ።

"አብዛኛው የምናየው ስብርባሪ ነው። ስለዚህ በስብርባሪው ውስጥ የዘር ፍሬዎችን ለማግኘት እንሞክራለን" በማለት ያስረዳሉ።

በዘር ፍሬ ናሙና ውስጥ የዘር ፍሬ የማግኘት ዕድል አንድ በመቶ ቢሆንም እንኳን የቴክኖሎጂው ፈልጎ የማግኘት መጠን 100 በመቶ እንደሆነ ይናገራሉ።

"ከዚህ ቀደም ማየት የማንችለውን ነገር ፈልጎ ማግኘት ማለት ነው" ይላሉ።

የዘር ፍሬው ከተገኘ በኋላ በሚሊ ሰከንዶች ውስጥ የዘር ፍሬው ተለይቶ በሮቦች እንዲወጣ ይደረጋል።

"ሮቦቱ የሚያወጣው የዘር ፍሬ ያለበትን ቦታ ለይቶ ነው" ይላሉ።

ሳሙኤል የዘር ፍሬ ናሙና ውስጥ የዘር ፍሬ ለማግኘት ስላልተቻለ የሕክምና ባለሙያዎች የብልቱ ፍሬ ውስጥ ገብተው የዘር ፍሬ መፈለግ ነበረባቸው። ይሄ ስኬታማ እንዲሆን ለዘጠኝ ወራት የሆርሞን ሕክምና ተደርጎለል።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሥነ ተዋልዶ ጤና ዘርፍ የቤተ ሙከራ ክፍል ዳይሬክተር ኤሪክ ፎርማን እንዳሉት፤ የሳሙኤል የዘር ፍሬ ናሙና ለምርመራ ሲላክ የባለቤቱ ፔነሎፒ እንቁላልም እየተሰበሰበ ነበር።

የዘር ፍሬ በተሰጠበት ቀን ከእንቁላል ጋር ቢገናኝ ጽንስ የመፈጠር ዕድሉ ይጨምራል።

ስምንት የዘር ፍሬዎችን ከሳሙኤል የዘር ፍሬ ናሙና መለየት ተችሏል። ከፔነሎፒ እንቁላሎች መካከል አንደኛውን ወደ ሽል (embryo) ማሳደግም ተችሏል።

ልጃቸው የፊታችን ሐምሌ ላይ ይወለዳል ተብሎ ይጠበቃል።

"አሁን እውነት መሆኑ እየተሰማኝ ነው። የልጅ እንቅስቃሴ ይሰማኛል። ጤናው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለም ተነግሮኛል" ትላለች ፔነሎፒ።

ከፍተኛ መጠን ያለው እንቁላል እንዲመረት በሚረዳው የአይቪኤፍ ሕክምና ውስጥም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ ይውላል።

የዘር ፍሬ ፈልጎ የሚያገኘው ቴክኖሎጂ ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ሙከራዎች መደረግ ይኖርባቸዋል። ስሱ የሆኑ የሕክምና መረጃዎችን ከመጠበቅ አንጻር ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ተገልጿል።

በዩናይትድ ኪንግደም የዋርዊክ ዩኒቨርስቲ መምህር ሲባሀን ኩዌንቢ "መውለድ ለማይችሉ ወንዶች በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘ የሕክምና መፍትሔ መገኘቱ አስደናቂ ነው። ሕክምናው ሙሉ በሙሉ ከመተግበሩ በፊት ተጨማሪ ሙከራዎች መደረግ አለባቸው" ይላሉ።

ሳሙኤል የረዥም ጊዜ ልጅ የማግኘት ጥያቄው በቴክኖሎጂው ምላሽ ማግኘቱን ይናገራል።

"ለወደፊት በዚህ ቴክኖሎጂ ተጨማሪ ልጅ ብናገኝ ደስ ይለናል። እስከዚያው ድረስ እንቁላል ጠብቀን ማቆየት እንችላለን። በዚህ ሒደት በድጋሚ ማለፋችን አይቀርም።"