በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን እህል ላይ ሰዎችን ደርቦ የጫነ 'አይሱዙ' ተገልብጦ 19 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

በአማራ ክልል፣ በደቡብ ጎንደር ዞን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከእህል ጋር 80 ሰዎችን ደርቦ የጫነ 'አይሱዙ' ተሽከርካሪ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ የ19 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ ለቢቢሲ ተናገረ።

የጭነት ተሽከርካሪው ከደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ከተማ ተነስቶ ወደ ሰቆጣ በመጓዝ ሳለ ዳሃና ወረዳ "ነጋሲ" በተባለ አካባቢ ላይ መገልበጡን የዋግ ኽምራ ዞን የመንገድ ትራፊክ ዋና ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮማንደር መላኩ አሻግሬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አደጋው የደረሰው እሁድ ሚያዚያ 18 2018 ዓ.ም. ሲሆን፣ ኃላፊው "ከሚገባው በላይ ጭነት በመጫኑ" ተገልብጦ የ19 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 61 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

አይሱዙው 60 ኩንታል እህል ጭኖ የነበረ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ኮማንደሩ፣ ከላይ ደግሞ 80 ሰዎችን ደርቦ ስለማሳፈሩ መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሕይወታቸው ካለፉት መካከል ሕጻናት እና እናቶች እንደሚገኙበት የተናገሩት ምክትል ኮማንደሩ፣ በአደጋው የተጎዱት እና የሞቱት የአንድ አካባቢ ሰዎች መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

ፖሊስ አደጋው ያጋጠማቸው የጻግብጂ ነዋሪዎች መሆናቸው ተናግረው፤ ለሥራ በብዛት ወደ እብናት እንደሚጓዙ ጠቅሰዋል።

"ትናንት [እሁድ] ብቻ ወደ አንድ አካባቢ የሸኘነው አስከሬን 17 ነው" ያሉት ኃላፊው ከሟቾቹ መካከል የአንድ ቤተሰብ አባላት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

"ሦስት አራት ልጅ የያዘ አለ፤ እስከ አምስት ስድስት ቤተሰብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ናቸው" ሲሉ አብዛኞቹ ሟቾች የአንድ ቤተሰብ አባላት እና የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተው ከነበሩ 62 ሰዎች መካከል አንድ ሰው በሕክምና ላይ እያለ ሕይወቱ በማለፉ የሟቾቹ ቁጥር ወደ 19 ከፍ ማለቱን ምክትል ኮማንደሩ አስረድተዋል።

አካባቢው ባለፉት ሦስት ዓመታት በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር መሆኑን የተናገሩት ምክትል ኮማንደር መላኩ፣ ስለዚህም የአደጋውን መንስዔ ወደ ሥፍራው ሄዶ ለማጣራት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አካባቢው ዳገታማ መሆኑን የሚያስረዱት ኃላፊው "መኪናው ተንሸራቶነው ወይስ ተገልብጦ" የሚለውን ለማጣራት አለመቻሉን ተናግረዋል።

ከአደጋው በኋላ ወደ ወደ ስፍራው በመሄድ አስከሬን እና ቁስለኛ ማምጣት የተቻለው በመከላከያ ድጋፍ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ ስፍራው መሄድ ካቆሙ ሦስት ዓመት እንደሆናቸው የተናገሩት ኃላፊው "መንገዱ ችግር ያለበት በመሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ አይደለም" ብለዋል።

በአካባቢው ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት መንገዱ ስለተዘጋ ስምሪት ተሰጥቶት የሚሰራ የሕዝብ ማመላለሻ የለም ያሉት ኃላፊው "ለቁጥጥርም የሚመች" አለመሆን ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዋግ ኽምራ "ሁሉም ወረዳዎች ሊባል በሚችል ደረጃ" በነዳጅ እጥረት ምክንያት የሕዝብ ትራንስፖርት መቆሙን ገልጸው አሽከርካሪዎች ነዳጅ "ከጥቁር ገበያ" እየገዙ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

ምክትል ኮማንደሩ አደጋው የደረሰበት አካባቢ ግን ነዳጅ ቢኖርም እንኳ በጸጥታ ችግር ምክንያት መሄድ እንደማይቻል በአፅንኦት ያስረዳሉ።

የሟቾች አስከሬን መነሳቱን እና ቁስለኞቹን ወደየአካባቢያቸው መላካቸውን የሚናገሩት ምክትል ኮማንደሩ ሹፌሩ በሕይወት ስለመትረፉ ሆነ ስለመሞቱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል።

ከሰቆጣ ወደ ባሕርዳር ከዚህ በፊት የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው ይህ ግን ከጸጥታ ጋር በተያያዘ መቆሙን ተናግረዋል።

በሕገ ወጥ መልኩ በጭነታቸው ላይ ሰዎችን በመደረብ ከሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች በስተቀር ሌላ የመጓጓዣ አማራጭ በአካባቢው አለመኖሩን ጨምረው ገልጸዋል።

በአካባቢው አልፎ አልፎ አደጋ እንደሚከሰት ለቢቢሲ ያስረዱት ምክትል ኮማንደር መላኩ፣ ይህንን ያህል ሰው ሲሞት ግን የመጀመርያው መሆኑን ይናገራሉ።

በአማራ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የክልሉ ነዋሪዎች የትራንስፖርት መስተጓጉል ገጥሟቸዋል።

ይህንም ተከትሎ ባለፈው ዓመት በሰሜን ወሎ ዞን እንዲሁ በሲኖትራክ ሲጓዙ የነበሩ 40 የሚሆኑ ሰዎች መኪናው በመገልበጡ ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።