የአሜሪካው ልዑክ ከኤርትራ፣ ከግብፅ እና ከሶማሊያ ሚኒስትሮች ጋር ስለ ቀጣናው ደኅንነት መወያየታቸው ተገለጸ

የአረብ እና የአፍሪካ አገራት ጉዳዮች የአሜሪካ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቦሎውስ ከኤርትራ፣ ከግብፅ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የአፍሪካ ቀንድን ደኅንነት "በማጠናከር" ዙሪያ መወያየታቸው ተገለጸ።
ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፣ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ እንዲሁም ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሳላም አብዲ አሊ ጋር ካይሮ ውስጥ የተናጠል ውይይት ያደረጉት የአሜሪካው ከፍተኛ አማካሪ፤ ስለ አፍሪካ ቀንድ "ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት" ማንሳታቸውን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አስታውቀዋል።
የግብፅ እና ኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ካይሮ ላይ ከተገናኙ በኋላ የቀይ ባሕር "ደኅንነት እና አስተዳደር የሚመለከተው የጠረፉን አገራት ብቻ" እንደሆነ መግለጻቸው አይዘነጋም።
የአሜሪካው ልዑክ እሁድ ሐምሌ 12/2018 ዓ. ም. በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ጋር ያደረጉትን ውይይት "ፍሬያማ" ብለዋል።
ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ስለ ቀጣናው "ደኅንነት" መወያየታቸውን ጠቅሰው፤ ስለ ሁለትዮሽ ትብብር እንዲሁም በቀጣናው "መረጋጋትን ለማስፈን በጋራ ስለመሥራት" መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።
የሶማሊያ "ውስጣዊ የፖለቲካ ውይይት" ከአጀንዳዎቻቸው መካከል መሆኑን አመልክተዋል።
ከኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት "በአብዛኛው ፈታኝ ስለሆነው የቀጣናው ሁኔታ" ማንሳታቸውን ተናግረዋል።
"በንግድ፣ በቀጣናዊ የምጣሄ ሃብት እድገት እና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትስስራችን ለማጠናከር ያሉትን ዕድሎች ቃኝተናል" ሲሉም አክለዋል።
ከመቼውም ጊዜ በላይ "የጋራ ጥረት" አስፈላጊ የሆነበት ወቅት መሆኑን የተናገሩት የአሜሪካ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቦሎውስ "ገንቢ በሆነ ሁኔታ በጥምረት መሥራት ያለውን ዋጋ እንገነዘባለን" ብለዋል።
ከኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት "ቀጣናዊ ግጭቶችን ለመፍታት፣ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን፣ ቀይ ባሕር እንዲሁም መላው የአፍሪካ ቀንድ እንዲበለጽግ በጋራ ለመሥራት" መነጋጋራቸውን ጠቅሰዋል።
ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የሁለቱን አገራት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ስለማጠናከር ማንሳታቸውን ተናግረዋል።
"በጋራ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ቀጣናዊ ጉዳዮች" በንግግራቸው ማካተታቸውን የገለጹት የአሜሪካ ከፍተኛ አማካሪ "በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት ለማስፈን እንዲሁም ብልጽግናን ለማረጋገጥ ግብፅ ቁልፍ አጋር ናት" ብለዋል።
ግብፅ እና አሜሪካ ከአፍሪካ ቀን በተጨማሪ በሊቢያ፣ በሱዳን እና በሊባኖስ ጉዳይ ላይም "የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው" አመልክተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ "በተሻለ ሁኔታ የተረጋጋ እና የበለጸገ እንዲሆን" አሜሪካ እና ግብፅ ተቀራርበው መሥራት እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነትም ተናግረዋል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በካይሮ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ በአገሮቻቸው መካከል ያለውን "ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስለ ማጠናከር" እንዲሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋም እንዴት "ማስተባበር" እንዳለባቸው መምከራቸውን ይፋ አድርገዋል።
ያለፈው ግንቦት ወር ላይ በቀይ ባሕር ላይ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እና የወደብ ትስስርን የተመለከተ ስምምነት የተፈራረሙት ግብፅ እና ኤርትራ፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ የሚመለከተው "የቀይ ባሕር ጠረፍ አገራትን ብቻ" እንደሆነ መግለጻቸው አይዘነጋም።
ሁለቱ አገራት፤ ቀይ ባሕር ከዳርቻው አገራት "ብሔራዊ ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር" እንዳለው በመጥቀስ "የቀይ ባሕር አጎራባች ያልሆነ አካል ቀይ ባሕርን በሚመለከቱ ጉዳዮች መግባት የለበትም" ማለታቸውም ይታወሳል።
ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና የደኅንነት ትስስራቸውን ማጠናከራቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ግብፅ "ከበባ በሚመስል መልኩ" እየተንቀሳቀሰች ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው መናገራቸውም አይዘነጋም።
ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ከሁለት ዓመት በፊት የጋራ ትብብር አሥመራ ላይ የመሠረቱ ሲሆን፣ በወቅቱ ግብፅ ኢትዮጵያ በገነባቸው የሕዳሴ ግድብ፣ ኤርትራ ኢትዮጵያ ባነሳችው የባሕር በር ጥያቄ እንዲሁም ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት ተቃቅረው ነበር።
አሁን ሦስቱ አገራት ካይሮ ላይ የተገናኙበት ጉዳይ ዋና ዓላማ በይፋ ባይታወቅም የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ጉዳይ ግን ኢትዮጵያ የደኅንነቴ እና የኅልውናዬ አጀንዳ ነው በማለት ታነሳዋለች።















