ድርቅ በተከሰተበት አበርገለ በአንድ ጊዜ አምስት ልጆችን ወልዳ ሦስቱ የተረፉላት እናት

በአንድ ጊዜ አምስት ልጆችን ተገላግላ ሦስቱ የተረፉላት እናት ከሦስቱ ልጆቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, YECHELA CLINIC

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ፀጋ አስጠራው እና ባለቤቷ ክብሮም ንጉሠ በጋራ ጎጆ ቀልሰው መኖር ከጀመሩ ሁለት ዓመታቸው ነው።

በትግራይ ክልል፣ ማዕከላዊ ዞን፣ አበርገለ ወረዳ፣ ስምረት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት እነዚህ ጥንዶች ነሐሴ 24/ 2018 ዓ.ም. የመጀመሪያ ልጃቸውን ለመታቀፍ የሚጠባበቁባት ዕለት ነበረች።

ፀጋ 25 ዓመቷ ሲሆን፣ ባለቤቷ ክብሮም ደግሞ 27 ዓመቱ ነው።

ፀጋ በእርግዝናዋ ስድስተኛ ወር ላይ ባደረገችው የሕክምና ምርመራ ሦስት ሕፃናትን እንደምትገላገል ተነግሯት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ወደ ሆስፒታል ሄዳ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ በሆዷ ውስጥ አምስት ሕፃናት ስለመኖራቸው አታውቅም ነበር።

ፀጋ በወሊድ ወቅት ያሳለፈችውን ሁኔታም "በጣም ከባድ ነበር፤ ተቸግሬ ነበር" ስትል ትገልጸዋለች።

ጥንዶቹ ከተወለዱት አምስት ልጆች ውስጥ ሦስቱን ብቻ በጤና ለመታቀፍ በቅተዋል። ፀጋ ምጡ የጀመራት ቤት ሳለች ሲሆን በአምቡላንስ ወደ ሕክምና ከተወሰደች በኋላ በየጭላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በምጥ ተገላግላለች።

ፀጋን ያዋለዷት ሐኪም ገብረዮሐንስ ንጉሠ፣ ከአምስቱ ሕፃናት ሦስተኛውና አምስተኛው ሞተው መወለዳቸውን ገልጸዋል።

ሐኪሙ እንደሚያብራሩት፣ ሦስተኛው ፅንስ ማህጸን ውስጥ ባለበት ወቅት በተፈጠረ የእድገት መስተጓጎል ምክንያት መትረፍ አልቻለም። አምስተኛው ፅንስ ደግሞ ማህጸን ውስጥ እያለ አምስተኛው ወር ላይ እድገቱ በመገታቱ በሕይወት እንዳልወጣ ጨምረው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን በሕይወት ያሉት ሦስቱ ሕፃናት ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት ናቸው። ፀጋ ይህም ቢሆን ሕፃናቱን ማየቷ እንዳስደሰታት ተናግራለች።

እነፀጋ የሚኖሩበት ስምረት ቀበሌ ከፍተኛ ድርቅ ያለበት አካባቢ ሲሆን ቤተሰቡ የሚተዳደረው በእርሻ ነው። በአካባቢው ያለው ድርቅ ምርት እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ይህም ፀጋ በእርግዝናዋም ወቅት ሆነ ከወለደች በኋላ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዳታገኝ ማድረጉን ትገልጻለች።

ክብሮም ሦስት ልጆች ሊወልዱ እንደሆነ ከተነገራቸው በኋላ ቤተሰቡ በጣም ተጨንቆ እንደነበር ያስታውሳል። የሚኖሩበት አካባቢ የጤና ተቋማት በቅርብ የማይገኙበት በመሆኑ የፀጋን የእርግዝና ክትትል አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበርም አንስቷል።

ፀጋ በእርግዝናዋ ወቅት የደም ማነስ እንዳጋጠማት እና በአካባቢው ያለው ድርቅም በእርግዝናዋ ወቅት ከባድ ችግር እንድታሳልፍ እንዳደረጋት ይናገራል። "ክረምቱ አልሆነልንም፣ በቆሎ ነበር ልናመርት ያቀድነው፣ በቆሎ ግን ሳይሆን ቀረ" ብሏል።

በዚህም ምክንያት ቤተሰቡ ያመረተው ምንም የግብርና ምርት እንደሌለ ያስረዳል።

ሦስት ሕፃናትን በድርቅ ውስጥ ለማሳደግ የሚያስችል ገቢ የሌለው ቤተሰቡ አሁን ከሌሎች ሰዎች እርዳታ እየጠበቀ ነው።

ክብሮም እንደሚለው፣ ከወረዳው የአምስት ሺህ ብር ድጋፍ አግኝተዋል። ከዚህ ውጪ ግን እስካሁን ተጨማሪ እርዳታ አላገኙም።

በመሆኑም ክብሮም በስምረት ጣቢያ ያለው የድርቅ ሁኔታ በወረዳና በዞን ደረጃ የሚታወቅ በመሆኑ፣ መንግሥት ለቤተሰባቸውና ለአካባቢው እርዳታ እንዲያደርግ ይጠይቃል።

"ወደሚቀጥለው ጊዜ በጥሩ እስከምንሸጋገር፣ አካባቢያችን በጣም ድርቅ ስለሆነ፣ እርዳታ እንዲደረግልን እንጠብቃለን" ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

ፀጋ በሆስፒታል ለስምንት ቀናት ከቆየች በኋላ ከልጆቿ ጋር ወደ ቤት መመለሷን የሚናገረው ክብሮም፣ አሁን ላይ እናት እና ሦስቱም ሕፃናት በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

የሕክምና ባለሞያው ገብረዮሐንስ አካባቢው ላይ ካለው ድርቅ በተጨማሪ ለትራንስፖርት የሚሆን ነዳጅ እንደልብ ባለመገኘቱ ነዋሪዎች ሕክምና ለማግኘት ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠብቃቸው ይገልጻል።

በዚህ ምክንያት በሆስፒታሉ ለመውለድ የሚመጡ እናቶች ቁጥር በእጥፍ እየቀነሰ መምጣቱን የሚናገሩት ባለሞያው አካባቢው ላይ በቤት ውስጥ መውለድ እየተለመደ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ለመውለድ የሚመጡ እናቶች ቁጥር በወር እስከ 180 ይደርስ እንደነበር አንስተው አሁን ግን በአማካይ 90 የሚሆኑ እናቶች ብቻ ወደ ጤና ተቋሙ እንደሚመጡ ይናገራሉ። ይህም የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና እየጎዳው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የነፀጋ ቤተሰብ ሁኔታ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተከሰተ ካለው የአየር ንብረት እና የሰብዓዊ ቀውስ ጋር የተያያዘ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት በነሐሴ ወር ባወጣው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የአየር ንብረት ክስተቶችና ግጭቶች በምግብ ዋስትና ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ጠቁሟል።

በተለይም በማዕከላዊ፣ በሰሜናዊ፣ በሰሜን ምሥራቅና በምሥራቅ ኢትዮጵያ የክረምት ዝናብ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል አመልክቷል።

በትግራይ ደግሞ የግጭት ሁኔታዎች የግብርና ወቅቶችን በማደናቀፋቸው፣ 21 ወረዳዎች ከፍተኛ የረሃብ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል። በክልሉ 2.45 ሚሊዮን ሰዎችም የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

ቢቢሲ በክልሉ ባነጋገራቸው አርሶ አደሮች እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ገለጻም፣ በተለይ በሦስት ወረዳዎች የዝናብ እጥረቱ በግብርና ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

በተከሰተው የአየር ሁኔታ ለውጥ በደቡባዊ፣ በደቡብ ምሥራቅ እና በመካከለኛው ዞኖች (በከፊል) ድርቅ እና በአንዳንድ ዝናብ በጣለባቸው ወረዳዎች ደግሞ ከባድ የበረዶ ዝናብ እና ጎርፍ ተከስቷል።

የዝናብ እጥረቱ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ድርቅን ያባባሰ ሲሆን፣ በአንዳንድ ዝናብ በጣለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ከባድ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ እና ጎርፍ መከሰቱ ተገልጿል።

በትግራይ የተፈጠረው ይህ ችግር ከዝናብ እጥረት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። የግጭት ተፅዕኖ፣ የግብርና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች አለመሟላት እና የእርዳታ አቅርቦት ችግር የአርሶ አደሮችን ለችግር ተጋላጭነት እያባባሱ እንደሆነ የክልሉ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

ከዚህ በፊት የተሻለ ኑሮ እንደነበራቸው የምትናገረው ፀጋ፣ አሁን ግን ድርቁ ሁኔታቸውን እንዳባባሰው ገልፃለች።

ቤተሰቡ የሚተዳደርበት እርሻ በድርቅ በመጎዳቱ አሁን ለሦስቱ ሕፃናት የሚያስፈልገውን ማሟላት እንደተሳነው ተናግራለች።

"ኑሮው ከባድ ነው፣ ቦታችን ድርቅ ነው፣ ቆላ ቦታ ነው። በአንዲት ጎጆ ውስጥ ነን፣ ምንም የለንም።" ስትል ያለችበትን ሁኔታ ታስረዳለች።

በአካባቢው ከዚህ በፊት ድርቅ ሲከሰት አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን ይዘው ዝናብ ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች መሄድ የተለመደ እንደነበር አርሶአደሮች ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን አሁን ግን የሰላም ሁኔታው አለመረጋጋቱ ይህንን አማራጭ እንዳሳነሰ ገልጸዋል።

የክልሉ የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለምበርሃን ሃሪፌዮም የትግራይ የግብርናና የምግብ ዋስትና ችግር አሳሳቢ መሆኑንና የክልሉ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ችግሩ ለቀጣይ ዓመታት ሊዘልቅ እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከጦርነቱ በኋላ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች በበቂ ሁኔታ አለመካሄዳቸው የግብርናውን ዘርፍ አዳክሞታል፤ ይህም አርሶ አደሮችን ለድርቅ የበለጠ ተጋላጭ እያደረጋቸው ነውም ብለዋል።

ይህ ሁኔታ በኤል ኒኖ ከሚመጣው የአየር ሁኔታ ለውጥ ጋር ሲደራረብ፣ በምሥራቅ አፍሪካ የድርቅና የጎርፍ አደጋን ጨምሮ ከባድ የአየር ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ተመራማሪዎች ያስጠነቅቃሉ።