የፕሬዝዳንት ትራምፕ አማካሪ ካይሮ ውስጥ ያደረጉት ውይይት "ፀረ ኢትዮጵያ" ይዘት የለውም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ከአንድ ሳምንት በፊት ካይሮ ውስጥ ከግብፅ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ፀረ ኢትዮጵያ ይዘት እንደሌለው አመለከቱ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአረብ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪው ማሳድ ቡሎስ ውይይቱ ከተካሄደ ከሳምንት በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ከአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ደያረጉት ንግግር "ተገቢ ያልሆነ ገጽታ ተሰጥቶት" ተዘግቧል ብለዋል።
ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፣ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ እንዲሁም ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሳላም አብዲ አሊ ጋር ካይሮ ውስጥ በተናጠል የተገናኙነት ከፍተኛ አማካሪው፤ ስለ አፍሪካ ቀንድ "ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት" መነጋገራቸውን በወቅቱ ገልጸው ነበር።
በዚያው ወቅት የግብፅ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ካይሮ ላይ ከተገናኙ በኋላ የቀይ ባሕር "ደኅንነት እና አስተዳደር የሚመለከተው የጠረፉን አገራት ብቻ" እንደሆነ በመግለጽ ኢትዮጵያ ካነሳችው የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ አንጻር አቋማቸውን አሳውቀው ነበር።
ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት የምትወዛገበው ግብፅ፣ የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ስጋት የፈጠረባት ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከደረሰች በኋላ ውዝግብ ውስጥ ገብታ የነበረችው ሶማሊያ ከሁለት ዓመት በፊት የጋራ ትብብር ፈጥረው እንደነበረ ይታወሳል።
የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ካይሮ ላይ መገናኛኘታቸውን ተከትሎ የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ማሳድ ቡሎስ፤ ከሚኒስትሮቹ ጋር መገናኘታቸውን በመጥቀስ ውይይቱ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የተደረገ መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎች ተሰምተዋል።
ነገር ግን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ በኤክስ ገቸጻው ላይ ዛሬ ባሰፈሩት መልዕክት ዘገባዎቹን "ሐሰተኛ እና አሳሳች" በማለት የአሜሪካን ዲፕሎማሲ "ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ" አቅርበዋል ብለዋል።
ዘገባዎቹ "አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ 'ፀረ ኢትዮጵያ ትብብርን' ለመደገፍ ሙከራ እንደምታደርግ" ተደርጎ መቅረባቸው የተዛባ መሆኑን በመግለጽ ይህም "ትክክል ያልሆነ እና አላስፈላጊ ማጋጋል" ነው በማለት ወቅሰዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ እና የአረብ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪው ጨምረውም አገራቸው "ከኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በቀይ ባሕር ቀጣና ከሚገኙ ሁሉም አገራት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ" እንደምትሠራ ገልጸዋል።
በዚህም ከአንድ የቀጣናው አጋር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከሌላው አገር ጋር መቃረን ማለት እንዳልሆነ የጠቀሱት ማሳድ ቡሎስ "የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ተቀናቃኝ ቡድኖችን መፍጠር ወይም ልዩነቶችን ማስፋት ሳይሆን ግጭቶችን በማስወገድ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር በገንቢ ሁኔታ መሥራት ነው" ብለዋል።
የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ቡሎስ ከግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ከተገናኙ በኋላ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም. በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከባለሥልጣናቱ ጋር ያደረጉትን ውይይት "ፍሬያማ" ብለዋል።
ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ስለ ቀጣናው "ደኅንነት" መወያየታቸውን ጠቅሰው፤ ስለ ሁለትዮሽ ትብብር እንዲሁም በቀጣናው "መረጋጋትን ለማስፈን በጋራ ስለመሥራት" መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።
የሶማሊያ "ውስጣዊ የፖለቲካ ውይይት" ከአጀንዳዎቻቸው መካከል መሆኑን አመልክተዋል።
ከኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት "በአብዛኛው ፈታኝ ስለሆነው የቀጣናው ሁኔታ" ማንሳታቸውን ተናግረዋል።
"በንግድ፣ በቀጣናዊ የምጣሄ ሃብት እድገት እና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትስስራችን ለማጠናከር ያሉትን ዕድሎች ቃኝተናል" ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አማካሪ ካይሮ በተገኙበት ጊዜ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኤርትራ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ የሚገኘው የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ "ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስለ ማጠናከር" እንዲሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ አቋማቸውን "ለማቀናጀት" መምከራቸውን ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ይፋ መሆንን ተከትሎ ሁለቱ አገራት፤ ቀይ ባሕር ከዳርቻው አገራት "ብሔራዊ ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር" እንዳለው በመጥቀስ "የቀይ ባሕር አጎራባች ያልሆነ አካል ቀይ ባሕርን በሚመለከቱ ጉዳዮች መግባት የለበትም" ማለታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ግብፅ "ከበባ በሚመስል መልኩ" እየተንቀሳቀሰች ነው ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋ መግለጹ ይታወቃል።
ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ከሁለት ዓመት በፊት የጋራ ትብብር አሥመራ ላይ የመሠረቱ ሲሆን፣ በወቅቱ ግብፅ ኢትዮጵያ በገነባቸው የሕዳሴ ግድብ፣ ኤርትራ ኢትዮጵያ ባነሳችው የባሕር በር ጥያቄ እንዲሁም ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት ተቃቅረው ነበር።















