ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ መሪዎች ለግጭቶች ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጠየቁ

ዶ/ር ቴድሮስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ክልላዊ መሪዎች በአገሪቱ ላሉት ግጭቶች በንግግር ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቀረቡ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ የጤና እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ቴድሮስ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚካሄዱ ያሉት ግጭቶች በኢትዮጵያውያን ላይ መከራ እያመጡ መሆናቸውን በመጥቀስ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግቸላው ጠይቀዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በይፋዊ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጥሪ በአማራ፣ በኦሮሚያ የሚካሄዱ ግጭቶች መቀጠላቸውን አፋር እና ቤኒሻልጉል ጉሙዝም ግጭቶች እንዳሉባቸው አመልክተዋል።

"ለሦስት ዓመታት እየተካሄደ ያለው የአማራ ክልል ግችት የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል። ኦሮሚያም እየደማች ነው" በማለት በሁለቱ ክልሎች እየተካሄደ ያለው ግጭት እያስከፈለ ያለውን ዋጋ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም "ትግራይም ወደ ግልጽ ውጊያ እየተንሸራተተች ሲሆን፣ አፋር ወደዚያው ተስቧል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝም በግጭት ውስጥ" መሆኑን በማንሳት የአገሪቱ ዋና ዋና ክልሎች በግጭት ውስጥ እና ወደ ግጭት በሚያመራ አቅጣጫ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግጭት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የገለጹበትን ይህንን መልዕክታቸውን ያጋሩት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት ወቅት ነው።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሐምሌ 25 ሸረሪና በሚባለው ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ስፋራ ግጭት መቀስቀሱ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ስለክስተቱ በይፋ ያለው ነገር የለም።

የህወሓት መሪዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ ለጦርነት መዘጋጀታቸውን እና በብልጽግና የሚመራውን መንግሥት መጣል ዓላማቸው መሆኑን በይፋ ሲገልጹ ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፌደራል መንግሥቱም የህወሓት መሪዎችን ከአገሪቱ ጠላቶች ጋር በመተባበር ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን በመግለጽ በመገናኛ ብዙኃኑ አማካኝነት ተከታታይ ዘመቻዎችን እያካሄደ ነው።

በአሁኑ ወቅት ያለው የጦርነት ስጋት ያሳሰባቸው የመንግሥታቱ ድርጅት የጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ

ሁሉም ወገኖች ከግጭት ተቆጥበው ንግግር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚካሄደው ግጭትን "ይበቃል" ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ ጦርነት ሞትን፣ ውድመትን እና ችግርን ብቻ የሚስከትል መሆኑን በመጥቀስ "የፌደራል መንግሥቱ እና ሁሉም የክልል መሪዎች ከጠብመንጃ ይልቅ ንግግርን በመምረጥ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ" ጠይቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ቀንድ አማካሪ የሆኑት እና የቀድሞው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ህወሓት ለወራት ከፌደራል መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ጋር የፈጠረውን ወዳጅነት ሲክድ ቆይቶ አሁን በይፋ ከኤርትራ ጋር እየሰራ መሆኑን አምኗል ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

አቶ ጌታቸው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የገባውን አለመግባበት ለመፍታት "ምንም ሰላማዊ መንገድ የለም" በማለት ግጭት ለመቀስቀስ ተዘጋጅቷል ሲሉ ከስሰዋል።

ህወሓት ዓላማው ዳግም ምዕራብ ትግራይን መቆጣጠር አይደለም ያሉት አቶ ጌታቸው የብልጽግና መንግሥትን መጣል መሆኑን አመራሮች በግልጽ ተናግረዋል ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

ከዚህ ለሁለት ዓመት በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ሲካሄድ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ሊቋጭ ችሏል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ አራት ዓመት ሊሞላው በቀረበት በአሁኑ ወቅት በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በሸረሪና የተከሰተው ግጭት ዳግም ጦርነት ይከሰታል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል።

የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ሌላ ዙር ጦርነት በመቀስቀስ እርስ በእርሳቸው ሲካሰሱ የአፍሪካ ኅብረት እና የተለያዩ አካላት ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር "በየቀኑ በርካታ ውጊያ፣ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች ትግራይ ውስጥ ባሉ ኃይሎች በየጊዜው ይፈጸማል" በማለት ህወሓትን ወንጅለው ነበር።