ከአማራ ክልል ቀውስ ጋር በተገናኘ በሽብር ለተከሰሱት የቀረበው የይቅርታ ሰነድ ምን አካቷል? ተከሳሾቹስ ምን ምላሽ ሰጡ?

የፎቶው ባለመብት, sm
በአማራ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ በሽብር ለተከሰሱት ከሦስት መቶ በላይ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ግለሰቦች በይቅርታ እንዲለቀቁ ሂደት ላይ ይገኛሉ።
ለሽብር ተከሳሾች የቀረበው የይቅርታ ሰነድ በክልሉ ለተፈፀሙ ግድያዎች እና ጉዳቶች ተከሳሾቹ ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚጠይቅ መሆኑን ቢቢሲ የተመለከተው ሰነድ ያሳያል።
የሕዝብ ተወካዮችን እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ በአማራ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር በተገናኘ በተለያዩ መዝገቦች የሽብር ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾች፣ ይቅርታ ጠይቀው ክሳቸው እንዲቋረጥ እና ከእስር እንዲለቀቁ በመንግሥት ለቀረበላቸው ጥያቄ የተለያየ ምላሽ መስጠታቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።
ሦስት ዓመት እና ከዚያም በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሽብር ተከሳሾች፣ ይቅርታ ጠይቀው ከእስር እንዲለቀቁ የሚጠይቀው ሰነድ (ፎርም) የደረሳቸው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አማካኝነት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ ከሰኔ 1/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በተከሳሾቹ እና በመንግሥት መካከል የማደራደር ተግባር ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ ተከሳሾቹ ይቅርታ የሚጠይቁበት እና ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተበት ሰነድ ለየግላቸው እንደደረሳቸው ታውቋል።
በአቶ ብርሃኑ አዴሎ መሪነት ተካሄደ ከተባለው ድርድር በኋላ ሰነዱ የቀረበላቸው የሽብር ተከሳሾች ቁጥር ከ300 በላይ እንደሆነ ምንጮቻችን ገልፀዋል።
በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ከሚገኙት ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል አብዛኛው የቀረበላቸውን ሰነድ ሲፈርሙ ያልፈረሙም ስለመኖራቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ቅድመ ሁኔታውን አንቀበልም በማለት ለመፈረም ፈቃደኛ ካልሆኑት መካከል ፖለቲከኛ እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ 30 ተከሳሾች ተጠቃሽ ናቸው።
ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበው ክስ፣ በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ በተፈፀሙ የሰዎች ግድያዎች፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት እንዲሁም በሌሎችም የሽብር ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚዘረዝር ነው።
የይቅርታ መጠየቂያ ሰነዱ፣ በየክስ መዝገባቸው በሽብር የቀረበባቸውን ወንጀል አምነው ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚጠይቅ ይዘት ያለው ስለመሆኑ ቢቢሲ የተመለከተው እና ሰነዱን አንፈርምም ካሉት የሽብር ተከሳሾች መካከል ሠላሳዎቹ የፈረሙበት ደብዳቤ ያመለክታል።
ፈርሙ የተባሉበት ሰነድ "በአማራ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ፣ በቀውሱ ለሞቱ እና ለቆሰሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች (በየክስ መዝገቡ ቁጥሩ ይለያያያል) ኃላፊነት ውሰዱ፤ በቢሊዮኖች የተገመተውን የንብረት ውድመት ፈፅመናል ብላችሁ እመኑ" የሚሉ ነጥቦችን ያካተተ እንደሆነ በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም "አገሪቱ በአማራ ትውፊቶች እና እሳቤ መመራት አለባት" የሚል አቋም ማራመዳቸው ተጠቅሶ ይህም ወንጀል መሆኑን እንዲያምኑ ስለመጠየቃቸው አስፍረዋል።
እንዲሁም "ያለ አግባብ የተወሰዱ የአማራ ርስቶች መመለስ አለባቸው" ስለማለታቸው እና ይህም ወንጀል መሆኑን እንዲያምኑ በሰነዱ መካተቱን ገልፀዋል።
በሰነዱ ላይ "ጽንፈኛ ኃይሎች" ተብለው የተጠቀሱትን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን እንዲያወግዙም ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን አመልክተዋል።
ተከሳሾቹ የተጠቀሱትን ወንጀሎች ስለመፈፀማቸው አምነው፣ ዳግመኛ የእንደዚህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ ላለመሳተፍ ቃል እንዲገቡ እና የሚሳተፉ ከሆነ ደግሞ መንግሥት "አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድባቸው" እንዲስማሙም ሰነዱ ይጠይቃል።
ሆኖም፣ ይህን ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በሰነዱ ላይ አለመፈረማቸውን በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
"ወንጀለኛ ነን ብለን አንፈርምም። [ይህ] በሕግም፣ በሞራልም፣ በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም" የሚሉት ሠላሳዎቹ ተከሳሾች "የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችም ሕጋዊ ናቸው ብለን እናምናለን" ሲሉም አክለዋል።
የተከሰሱበትን ክስ "አንቀበልም" ብለው በፍርድ ቤት እየተከራከሩ ባሉበት ሁኔታ፣ "ወንጀለኞች ነን" ብለው ለመፈረም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ስለመግለፃቸው ሦስት ጉዳዩን የሚከታተሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመሆኑም፣ ከሦስት ዓመት በላይ ያለ ፍትሕ መቆየታቸውን እና "ቤተሰቦቻቸውም ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን የሚገልፁት እነዚህ ተከሳሾች፣ መንግሥት "ክሱን አቋርጦ በፖለቲካዊ መንገድ በምህረት ይፍታን" የሚል አቋም አላቸው።
ተከሳሾቹን እና መንግሥትን አደራድሯል ከተባለው ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ስለ ጉዳዩ አስተያየት ጠይቀን ነበር። ሆኖም የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ቢሆንም ኮሚሽኑ እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ በራሱ መንገድ ከሚሰጠው መግለጫ ውጭ መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ከሌሎች የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመሆን በታኅሣሥ ወር በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማዕከል ጉብኝት አድርገው ነበር። በጉብኝታቸውም ከተከሳሾቹ ጋር በሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገው መመለሳቸው በወቅቱ ተገልጿል።
ምንጮቻችን እንዳሉት፣ ዋና ኮሚሽነሩ ብርሃኑ አዴሎ ከሽብር ተከሳሾቹ ጋር ውይይት ካደረጉ ከስድስት ወራት በኋላ ነው በድጋሚ አግኝተዋቸው የማደራደር ተግባር የጀመሩት።
ስለ ይቅርታው ጉዳይ ከተከሳሽ ጠበቆች በኩል አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ለጊዜው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም።
ይሁንና ይቅርታ የመጠየቅ እና የመስጠት ሂደት ከሕግ አንፃር እንዴት እንደሚታይ የጠየቅናቸው አንድ የሕግ ባለሙያ፣ አንድ ተከሳሽ ወንጀለኛ ተብሎ ካልተፈረደበት በስተቀር በይቅርታ ሂደት ውስጥ ማለፍ እንደማይችል ተናግረዋል።
በጥብቅና ሥራ ላይ የተሰማሩት የሕግ ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ ጥላሁን፣ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 229 መሠረት፣ ይቅርታ ለመስጠት "በግልፅ የተወሰነ የቅጣት ውሳኔ መኖር አለበት" ይላሉ።
በተመሳሳይ ይቅርታ መጠየቅም የሚቻለው ውሳኔ ባገኘ ወይም ፍርድ በተሰጠው ጉዳይ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። የይቅርታ አቀራረብ ድንጋጌዎችን የያዘው የይቅርታ አዋጅ 840/2006 በአንቀፅ 15 ላይ፣ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የመጨረሻ ቅጣት የተወሰነበት ማንኛውም ሰው የይቅርታ ጥያቄውን ራሱ ወይም በቅርብ ዘመዱ ወይም በሚወክለው ጠበቃው አማካኝነት ማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል። በመሆኑም የፍርድ ውሳኔ ሳይሰጥ የይቅርታ ጉዳይን ማንሳት እንደማይቻል አቶ ኤርሚያስ አብራርተዋል።
ምርጫ 97ን ተከትሎ በነበረው ሁኔታ ታስረው የነበሩት እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን እና ብርትኳን ሚደቅሳን ጨምሮ ሌሎችም እስረኞች ከተፈረደባቸው በኋላ ጉዳያቸው በይቅርታ ታይቶ መፈታታቸውን፣ እንዲሁም በ2010 ከነበረው "የመንግሥት ለውጥ" በኋላ በተመሳሳይ መልኩ የተፈቱ ሰዎች መኖራቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ተፈርዶበት በይግባኝ ላይ የሚገኝ ተከሳሽ እንኳን ይቅርታ መጠየቅ አይችልም።
በኢሰመኮ አደራዳሪነት ቅድመ ሁኔታዎችን ተቀብለው ይቅርታ እንዲጠይቁ የፊርማ ሰነድ የቀረበላቸው የሽብር ተከሳሾች፣ ገና ፍርድ ያላገኙ እና የክስ ሂደታቸው በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኝ ናቸው።
በመሆኑም በሕጉ መሠረት ከእስር መለቀቅ የሚችሉት ክሳቸውን በማቋረጥ እና በምህረት እንደሆነ የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።















