ኤርትራ ግለሰቦች እና ተቋማት በሚይዙት የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ጣለች

የኤርትራ ገንዘብ ናቅፋ የሚቆጥር ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኤርትራ ግለሰቦች እና የንግድ ተቋማት ከባንክ ሥርዓት ውጭ ለተወሰነ ጊዜ መያዝ የሚችሉትን የጥሬ ገንዘብ መጠን የሚገድብ አዲስ መመሪያ ማውጣቷን የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ረቡዕ ጳጉሜ 4/2018 ዓ.ም. በአገሪቱ መንግሥታዊ የሕግ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ይፋ በተደረገው መመሪያ ማንኛውም ዓይነት የኤርትራ ገንዘብ፣ ናቅፋ ዝውውር በባንኮች እና በገንዘብ ተቋማት ብቻ መሆን እንዳለበት አዝዟል።

በአዲሱ መመሪያ መሠረት ግለሰቦች ከ25 ሺህ ናቅፋ በላይ የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ከ15 ቀናት በላይ በእጃቸው ማቆየት አይችሉም።

እንዲሁም በተለያዩ ሦስት ደረጃዎች የተመደቡ የንግድ ተቋማትም በ50 ሺህ፣ በ100 ሺህ እና በ150 ሺህ ናቅፋ መጠን የተገደበ ጥሬ ገንዘብ ለሁለት ሳምንታት ብቻ መያዝ እንዲችሉ ተፈቅዷል።

ነገር ግን ይህንን መመሪያ ተላልፈው ከተፈቀደላቸው የጥሬ ገንዘብ መጠን እና ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በላይ ተቀባይነት ካለው ምክንያት ውጭ ይዘው የተገኙ ተቋማት እና ግለሰቦች ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠንቅቋል።

አሁን የኤርትራ ማዕከላዊ ባንክ ያወጣው በግለሰቦች እና በተቋማት ይዞታ ስር ሊቀመጥ የሚችልን የገንዘብ መጠንን የሚገድበው መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ነው።

የመዋዕለ ነዋይ ዘርፍ በመንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር ሥር በሚገኘባት ኤርትራ በጥሬ ገንዘብ መገበያየት ዋነኛው እና በስፋት ጥቅም የሚውል ነው። በተጨማሪም የባንክ አገልግሎቶች በመላዋ አገሪቱ የተስፋፋ አይደለም።

የኤርትራ መንግሥትም በገበያ ውስጥ እና በግለሰቦች ይዞታ ሥር የሚገኝን የተከማች ጥሬ ገንዘብ እና የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር በተያዩ ጊዜያት እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ሐምሌ ወርም የአገሪቱ ዜጎቹ እና ተቋማት በእጃቸው የሚገኝ መገበያያ ገንዘብ (ናቅፋ) በሙሉ ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ማዕከላዊ ባንኩ አዝዞ ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል።

በወቅቱም ባንኩ ባወጣው መግለጫ ሁሉም ዜጋ እና ተቋማት የመጠቀም መብት ያለባቸው የአገሪቱ ብሔራዊ ገንዘብ የሆነውን ናቅፋ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ ለየትኛውም ልውውጥ በናቅፋ ብቻ የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው አሳስቦ ነበር።

ጨምሮም ግለሰቦች እና ተቋማት ያላቸውን ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ከዚያ ውጭ ግን ገንዘብን በይዞታቸው ውስጥ ማቆየት ሕገ ወጥ መሆኑን አስጠንቅቋል።

ይህ መመሪያ የኤርትራ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ተመን፣ በገንዘብ ዝውውር እና በፍጆታ እቃዎች ላይ ለአስርታት ሲያካሂድ ከቆየው ጥብቅ ቁጥጥር ጋር የሚዛመድ ነው።

ከአስር ዓመት በፊት የኤርትራ መንግሥት አዲስ የመገበያያ ገንዘብ አሳትሞ ባሠራጨበት ጊዜ በለውጡ ሂደት በሕዝቡ እጅ የነበረውን ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወደ ባንክ እንዲገባ አድርጎ ነበር።

በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት የገንዘብ ለውጡን ያደረገው "ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር እና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማረጋጋት ነው" ሲል ምክንያት ሰጥቶ ነበር።

በገንዘብ ለውጡ ሂደት ወደ ባንክ የገባውን ገንዘብ መቆጣጠር የቻለው መንግሥት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የኤርትራ ዜጋ በሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ላይ ጥብቅ ገደብ ለመጣል ችሏል።

በዚህም መሠረት በኤርትራ ውስጥ በሚገኝ ባንክ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ከባንክ ሂሳባቸው በአንድ ወር ውስጥ ማውጣት የሚችሉት አምስት ሺህ ናቅፋ ብቻ እንዲሆን ገድቧል።

ይህ ከባንኮች በሚወጣው የገንዘብ መጠን ላይ የተጣለው ገደብ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ በብዙ ገጽታዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ግዢዎች እና ለሌሎች ወጪዎች ገንዘብ የሚፈልጉ ኤርትራውያን በወጣው ጥብቅ ገደብ ምክንያት ለበርካታ ወራት ገንዘብ ከባንክ በማውጣት ለማጠራቀም ይገደዳሉ።

በተጨማሪም እንደ ሰርግ ላሉ ከፍተኛ ወጪን ለሚጠይቁ አንዳንድ ጉዳዮች ከተቀመጠው ወርሃዊ አምስት ሺህ ናቅፋ በላይ ከባንኮች ገንዘብ ለማውጣት ከአካባቢያቸው ባለሥልጣን የፈቃድ ደብዳቤ ማግኘት አለባቸው።

ባለፉት ሁለት ወራት የኤርትራ መንግሥት ዜጎች በእጃቸው የሚገኝ ገንዘብን ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ካደረገ በኋላ አሁን ደግሞ ግለሰቦች እና ተቋማት በእጃቸው ማቆየት የሚችሉት የጥሬ ገንዘብ መጠን እና ጊዜ ላይ አዲስ ገደብ አውጥቷል።

ኤርትራ በአፍሪካ በመንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የባንክ ሥርዓት ካሏቸው አገራት አንዷ ስትሆን፤ በአገሪቱ ዘመናዊ የገንዘብ ዝውውር እና የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ አብዛኛው የገንዘብ ዝውውር እና ግብይት በጥሬ ገንዘብ ብቻ ይካሄዳል።