ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ የቀድሞ የኩባ ፕሬዚዳንት ራውል ካስትሮ ላይ ክስ ልትመሠርት ነው
የአሜሪካ የፍትሕ ቢሮ የቀድሞው የኩባ ፕሬዚዳንት ላይ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ተመትተው ከተከሰከሱ ሁለት አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ በሚቀጥሉት ቀናት ክስ ለመመስረት እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ።
ክሶቹ እንደሚመሰረቱ የተገለጸው የአሜሪካ የስለላ ኃላፊ ወደ ሃቫና ተጉዘው የኩባ ባለሥልጣናትን ካነጋገሩ በኋላ ነው።
የ94 ዓመቱ ካስትሮ እአአ ከ2021 ጀምሮ ከኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ መሪነታቸው ተነስተዋል።
ወንድማቸው ፊደል ካስትሮ ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ ለ15 ዓመታት ኩባን አስተዳድረዋል።
አሜሪካ ኩባ ላይ በርካታ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን በተጨማሪም የነዳጅ ዘይት አንዳታገኝ አግዳለች።
በራውል ካስትሮ ላይ የሚቀርቡት ክሶች እአአ በ1996 በአሜሪካዊ አክቲቪስት ባለቤትነት የተያዙ ሁለት አውሮፕላኖች ተመትተው ከመከስከሳቸው ጋር የተያያዘ ነው።
በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ባለሥልጣን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ክሶቹ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ድረስ እንደሚመሰሰረቱ ተናግረዋል።።
አርብ ዕለት ከቻይና ጉዟቸው እየተመለሱ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ክሶቹ ሲጠየቁ "የፍትሕ ቢሮ አስተያየት እንዲሰጥበት አደርጋለሁ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም "ነገር ግን እንደምታውቁት [ኩባውያን] እርዳታ ይፈልጋሉ። እና የምናወራው እያሽቆለቆለች ስለላች አገር ነው። እውነቱን ለመናገር እያሽቆለቆለች ያለች አገር ናት።"
ትራምፕ ወደ ኩባ የሚሄድ የነዳጅ ዘይትን በማገዳቸው በአገሪቱ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ተከስቷል። በዚህ ሳምነት የአገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስቴር የአገሪቱ ነዳጅ ተሟጥጦ ማለቁን አስታውቋል።
በራውሎ ካስትሮ ላይ ሊቀርብ ስለሚችለው የክስ ዝርዝር በይፋ የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን ባለሥልጣናት ምርመራው ያተኮረው እአአ የካቲት 24 1996 ራውል የጦሩ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ተመትተው በወደቁት ሁለት አነስተኛ አውሮፕላኖች ዙሪያ ነው።
ተከስክሰው በወደቁት አውሮፕላኖች ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎች ወዲያውኑ ሞተዋል።
'ብራዘርስ ቱ ዘ ሬስኪዉ' የተባለው ቡድን በስደት የሚኖሩ ኩባውያን የተመሰረተ ሲሆን በባሕር ወደ አሜሪካ ለማቋረጥ የሚሞክሩ ኩባውያንን የሚያግዝ ድርጅት ነው። አውሮፕላኖቹ ተመትተው ከመውደቃቸው በፊት በኩባ የባሕር ዳርቻ ጸረ መንግሥት በራሪ ወረቀቶችን ጥለው ነበር ተብሏል።
እአአ በ2016 የሞቱት ፊደል ካስትሮን ጨምሮ የኩባ መንግሥት 'ብራዘርስ ቱ ዘ ሬስኪዉ' በተደጋጋሚ የኩባን የአየር ክልል መጣሱን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ ሲቪል አቪየሽን ግን ጥቃቱ የተፈጸመው የዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ ነው ሲል በወቅቱ አስታውቋል።
በመጋቢት ወር በፍሎሪዳ የሚገኘው የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከአውሮፕላኖቹ መከስከስ ጋር በተገናኘ ራውል ካስትሮ ያላቸወን ሚና ለመመርመር መዝገቡን ዳግም ማንቀሳቀሱን አስታውቋል።
የፍሎሪዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ሮን ዴሳንቲስ አርብ ዕለት በራውል ካስትሮ ላይ የሚመሰረተውን ክስ "ለረዥም ጊዜ የቆየ" በማለት አሞካሽተውታል።
ኩባ ክሱን በተመለከተ በይፋ ምላሽ ባትሰጥም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ብሩኖ ሮድሪጌዝ ግን አርብ ዕለት ጠንከር ያለ አስተየየት ሰጥተዋል።
ሮይተርስ ሚኒስትሩ "አሜሪካ የጣለችው እገዳ፣ ማዕቀብ እና ኃይል ለመጠቀም ዛቻዎች ባሉበት ኩባ ወደ ሶሻሊስት ልማቷ ሉዓላዊነት ጎዳና ላይ መጓዟን ትቀጥላለች" ማለታቸውን ዘግቧል።
ክሱን ለመመስረት አቃቤ ሕጎች ከሕዝብ ተውጣጥተው የሚሰየሙትን የሕዝብ ዳኛዎች (ጁሪዎች) ወንጀል ተፈጽሟል በሚል ማሳመን ይጠበቅባቸዋል።
የአሜሪካ ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሆኑት ታድ ብላንቼ ክሱ ሊመሰረት ስለመሆኑ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ብላንቼ ለፎክስ ኒውስ "ጊዜው ከሆነ እና ሲሆን ብቻ እንናገራለን" ብለዋል።
ትራምፕ የኩባ ኮሚኒስት አመራሮችን ለመክሰስ አሜሪካ ፍላጎት አንዳላት ገልጸው ነበር።
ሐሙስ ዕለት የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ በሃቫና በሚገኘው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኩባ አቻቸው ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
አንድ የሲአይኤ ባለሥልጣን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት አሜሪካ "ኩባ መሠረታዊ ለውጦችን ካደረገች ብቻ በኢኮኖሚ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነች" ብለዋል።
አሜሪካ በአገሪቱ ላይ የጣለችውን የነዳጅ ዘይት እገዳ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት የፈጠረ ሲሆን በዚህም የተነሳ ሆስፒታሎች መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሰሩ እና ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት ቢሮዎች እንዲዘጉ አስገድዷል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ትናንት በተለያዩ የሐቫና አካባቢዎች የኃይል መቆራረጥ ያማረራቸው ነዋሪዎች ተቃውሞ ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል።
አሜሪካ "የኩባ ኮምኒስት ሥርዓት ትርጉም ያለው መሻሻል ካሳየ" 100 ሚሊዮን ዶላር ለአገሪቱ እንደምትልክ በዚህ ሳምንት አስታውቃለች።
የኩባ ኢነርጂ ሚኒስትር "ድፍድፍ ነዳጅ አልቋል፣ ጋዝ አልቋል፣ ናፍጣ አልቋል። ደጋግሜ እየተናገርኩ ነው። የቀረን ጥቂት ጋዝ ብቻ ነው" ብለዋል።
አሜሪካ በጣለችው ማዕቀብ ምክንያት በሐቫና ከ20 እስከ 22 ሰዓታት ድረስ መብራት እየጠፋ ይገኛል።