በርካታ ሴቶችን ለችግር እያጋለጠ ያለው አደገኛው የሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና

ኒኪታ ሞርጋን የዐይን ሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።
"ሁሉም ሰው ቀላል ነው ብሎኝ ነበር። ቀዶ ሕክምናው ሲደረግ ፊቴ በእሳት እንደተያያዘ ተሰማኝ፤ የሚቃጠል ቆዳም ሸተተኝ" ስትል ትገልጸዋለች።
በዐይን ሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና (ወይም በእንግሊዘኛው blepharoplasty) ከዐይን በላይ የተወሰነ ቆዳ ይነሳል።
ኒኪታ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቪድዮዎች ካየች በኋላ ነው ቀዶ ሕክምናውን ያደረገችው። ማደንዘዣ ቢሰጣም ሕመም ተሰምቷታል።
በዐይን ዙርያ ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉ ሐኪሞች እንደሚሉት በርካቶች የሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና በርካሽ ካደረጉ በኋላ ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
የፊት ቆዳን ለመሰብሰብ እና ለማለስለስ በሚል ቀዶ ሕክምናውን የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በእስያ ከተደረጉ የሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ የጤና እክሎች መከሰታቸው ይነገራል።
ቀዶ ሕክምናው ከተደረገ በኋላ ተገቢው እንክብካቤ አለመደረጉ የሚያስከትለውን ጉዳት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
እንደ ኒኪታ ሁሉ በርካቶች ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ችግር ገጥሟቸዋል።
ከሽፋሽፍቷ ላይ ብዙ ቆዳ በመነሳቱ ምክንያት ለመተኛት ተቸግራ ዐይኗን በፕላስተር ያጣበቀች ሴት ለዚህ ማሳያ ናት። ሌላ ሴት ደግሞ ዐይኔ ይጠፋል ብላ ትፈራለች።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ብዙዎች ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ዐይናቸውን መጨፈን አልቻሉም።
ደብሊን የተወለደችው ኒኪታ በአየርላንድ ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ አልነበራትም። ሽፋሽፍቷን ለማስተካከል 4,000 ዩሮ መክፈል ይጠበቅባት ነበር።
የ31 ዓመቷ ኒኪታ 'ፌስላንድ' የተባለ የጀርመን ድርጅት ቀዶ ሕክምናውን በ750 ዩሮ እንደሚሰጥ የሰማችው ቲክቶክ ላይ ነው።
ሕክምናው የሚሰጥበት ክፍል ጠባብ እንደሆነ ታስታውሳለች። ድርጅቱ በኔዘርላንድስ፣ ጀርመን እና ስዊትዘርላንድ ባሉ ቅርንጫፎቹ ውስጥ 2,950 ለሚደርሱ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ቀዶ ሕክምና ማድረጉን ይገልጻል።

ድርጅቱ የሚሰጠው ሕክምና "ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ" እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።
"ቅሬታ የቀረበባቸው ቀዶ ሕክምናዎች ከአንድ በመቶ በታች ናቸው" ብሏል። ይህ ግን ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ በገጠማቸው ችግር በድጋሚ ሌላ ዙር ቀዶ ሕክምና የተደረገላቸውን አይጨምርም።
ከቀዶ ሕክምና በኋላ ችግር እንደገጠማቸው ለቢቢሲ የገለጹ በአጠቃላይ ወደዚህ ድርጅት መሄዳቸውን ተናግረዋል። በአጠቃላይ ምን ያህል ታካሚዎች ቅሬታ እንዳቀረቡ ግን አይታወቅም።
ኒኪታ በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2025 ላይ ነበር ቀዶ ሕክምናውን ያደረገችው። ምን ያህል ዘላቂ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ሕክምና እንደሆነ አላወቀችም ነበር።
"የከንፈር ቀዶ ሕክምና ዓይነት ነበር የመሰለኝ" ትላለች።
ማደንዘዣ ቢሰጣችም ሐኪሞቹ ስስ የሆነው የዐይኗን ሽፋሽፍት ሲቆርጡት ከዚያ በፊት ተሰምቷት የማያውቅ ሕመም ገጠማት።
"እጅግ ደነገጥኩኝ፤ በጣም አስቀያሚ ነበር። ሐኪሟ ቆዳዬን ስትሰፋው መርፌው ይሰማኝ ነበር" ትላለች።
ፌስላንድ የተባለው ድርጅት በበኩሉ ሁሉም ሕሙማን ከሐኪም ጋር እንደተማከሩ እና ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ ፈቃዳቸውን እንደሰጡ ገልጿል።
የኒኪታ ሐኪም "ስለ ቀዶ ሕክምናው እርግጠኛ አልነበረችም፤ ፈርታም ነበር። ይህም ሕመም የገጠማት እንዲመስላት አድርጓታል" ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
ኒኪታ ከቀዶ ሕክምናው ከሰዓታት በኋላ አውሮፕላን ተሳፍራ ወደ ቤቷ ተመለሰች። ቀዶ ሕክምና በተደረገበት ቀን አውሮፕላን መሳፈር አይመከርም።
ነገር ግን ቀዶ ሕክምናውን ያደረጉ ሰዎች አውሮፕላን ሲሳፈሩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስላየች ኒኪታ ወደ ቤት ለመሄድ ወሰነች።
"ለማየት ተቸግሬ ነበር። ወደላይ ስመለከት የተሰፋው ቆዳ ይደማል። ደም እያለቀስኩ ይመስል ነበር።"
ቀዶ ሕክምናው በተደረገላት ቀን አውሮፕላን መሳፈሯ ይቆጫታል። ሌሎችም እንዲህ እንዳያደርጉ ትመክራለች።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በዩናይት ኪንግደም በአራት ዋነኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የዐይን ሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምናን የተመለከቱ መረጃዎች ወደ 150 ሚሊዮን ጊዜ እንደታዩ ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል። ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው አምስት እጥፍ ይበልጣል።
አንዲት ሴት ለቢቢሲ እንደገለጸችው ሽፋሽፍቷ ዕይታዋን እየጋረዳት እና በራስ ምታትም እየተሰቃየች ነበር። በፌስላንድ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ችግሯ መቀረፉን ተናግራለች።
የድርጅቱ ድረ ገጽ "ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው፣ ተደራሽ እና በከፍተኛ ጥራት የሚሰጥ ሕክምና" እንዳለው ይገልጻል።
ሕክምናው የሚሰጠው ዕውቅና በተሰጣቸው ዶክተሮች እንደሆነ እና ባለሙያዎቹ በፌስላንድ ተጨማሪ የቀዶ ሕክምና እንደሚያገኙም ይጠቁማል።
የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና እስከ ሦስት ሰዓታት ይወስዳል። ይህም ቅድመ ዝግጅት እና ከቀዶ ሕክምና በኋላ የሚደረግ እንክብካቤን ይጨምራል።
የፌስላንድ ታካሚዎች ግን አንድ ሰዓት ብቻ እንደወሰደ ይናገራሉ።
ድርጅቱ እንደሚለው ግን በአነስተኛ ዋጋ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቀዶ ሕክምና ይሰጣል።

'አብዛኛውን ቆዳዬን አንስተውታል'
ላውራ (ስሟ ተለውጧል) በፌስላንድ ቀዶ ሕክምና ካደረገች ከስምንት ቀናት በኋላ ዐይኗ አልገለጥ ስላላት ወደ ድንገተኛ ሕክምና ክፍል አመራች።
በ40ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኘው ላውራ ወደ ፌስላንድ የድንገተኛ ጊዜ ጥሪ ማዕከል ብትደውልም ምላሽ አላገኘችም።
ቀዶ ሕክምናውን አምስተርዳም ስታደርግ ምንም ችግር አልገጠማትም። ወደ ዩኬ ከተመለሰች በኋላ የጨረቃ ቅርጽ ያለው ጠባሳ ተመለከተች።
ሽፋሽፍቷ ላይ ያለው ቁስል ሲለቅም ኢንፌክሽን ያዛት። የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት በባለሙያዎች ቀዶ ሕክምናው ቢካሄድ ኖሮ ይህ አይከሰትም ነበር።

ላውራ "ዐይኔን ለረዥም ጊዜ ስጨፍን ቁስሉ እንደ አዲስ ይከፈታል። መተኛት ፈራሁ፤ ሁሉንም ሰዓት በጭንቀት አሳልፍ ጀመር" ትላለች።
ፌስላንድ ሕክምና ከሰጧት ሐኪሞች ጋር ስትነጋገር ወደ አምስተርዳም ተመልሳ ድጋፍ እንዲያደርጉላት ትማጸናቸው ነበር።
"እያለቀስኩ ለመንኳቸው። እንደዚህ ሆኜ አትተውኝ አልኳቸው።"
ሆኖም ግን በቅራቢያዋ ያለ ሕክምና ጣቢያ እንድትሄድ ተነገራት። የዐይን ሐኪሞች ስታማክር ከሽፋሽፍቷ ብዙ ቆዳ መነሳቱን ገለጹላት።
በአነስተኛ ዋጋ ባደረገችው ቀዶ ሕክምና ምክንያት ወደ እንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት በመሄዷ "ጥፋተኛነት እንደሚሰማት" ትናገራለች።
"ጥፋተኛነት ይሰማኛል። ሰዎች ጥፋቱ የእኔው እንደሆነ ነው የሚያስቡት። ይሄ እንደሚፈጠር ባውቅ ኖሮ አልሄድም ነበር።"
ፌስላንድ የላውራ ጉዳይ በፍርድ ቤት የተያዘ ስለሆነ ስለ ሕክምናው አስተያየት መስጠት እንደማይችል ለቢቢሲ ገልጿል።
ከፌስላንድ ጋር የሚሠራ ተቋም ለላውራ 275 ዩሮ ካሳ ለመክፈል ቢጠይቅም ፈቃደኛ ስላልሆነች በፍርድ ቤት ድርጅቱን ከስሳለች።

'ዐይኔ ሊጠፋ ነው ብዬ ፈራሁ'
የዩኬ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና ካደረጉ በኋላ ችግር የገጠማቸው ሰዎች ከአገር ውጭ ሕክምናውን ያገኙ ናቸው።
ቢቢሲ 63 አባላት ካሉት የዐይን ሐኪሞች ማኅበር ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ አብዛኞቹ ታካሚዎች ዐይናቸውን በአግባቡ ለመጨፈን ይቸገራሉ።
የዐይን ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ኮሊን ቪልዝ "ብዙ የቆዳ ክፍል ከሽፋሽፍት ሲነሳ አደገኛ ነው። ዐይንን ለአደጋ ያጋልጣል። ይሄንን ለማስተካከል መሞከር ከባድ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው" ይላል።
የዐይን ሽፋሽፍት እንደ መጋረጃ ሁሉ ሲከፈት እና ሲዘጋ የሚያግዘው በቂ ቆዳ ሊኖረው እንደሚገባ ይናገራል።
የሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና ያደረጉ ሰዎች ዐይናቸውን ለመጨፈን ከመቸገራቸው ባሻገር ሕክምናው ዐይናቸው ላይ ጠባሳ ጥሎ እንዳለፈ ይናገራሉ።
ዐይናቸውን ሲገልጡ መቁሰሉ እና ዐይናቸው መጠኑ መለያየቱም ሌላው እክል ነው።

ክሬይን ሀርት በአውሮፓውያኑ 2024 የገና በዓል ቀን ከእንቅልፏ ስትነሳ ለማየት መቸገሯን ታስታውሳለች።
በአምስተርዳም በሚገኘው የፌስላንድ ቅርንጫፍ የሽፋሽፍት ቀዶ ሕክምና ባደረገች በማግስቱ ነበር የተቸገረችው።
ከእንቅልፏ ስትነሳ ግራ ዐይኗ አብጦ፣ ደም ይፈስ ነበር። ሁለቱም ዐይኖቿ ላይ ያለው ቁስል መከፈትም ጀመረ።
"ትንሽ ቆዳ ከዐይኔ ላይ ለማስወገድ ብዬ ባደረግኩት ቀዶ ሕክምና ዐይኔን ላጣ ነው ብዬ ፈራሁ።"
ወደ ድንገተኛ ሕክምና ክፍል ካመራች በኋላ ሐኪሞች ዐይኗ እንደማይጠፋ ነገሯት። ፊቷ ግን ክፉኛ ተጎድቶ ነበር።
ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት ከተሰጣት በኋላ ሕክምና እንድትከታተል ተነገራት።
የገጠማትን ችግር ለፌስላንድ በኢሜል ብትገልጽም መልስ የተሰጣት ከ12 ቀናት በኋላ ነበር። ከዚያ በኋላ ምንም የተሰጣት መረጃም አልነበረም።
ድርጅቱ በበኩሉ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ታካሚዋን "ያለ ድጋፍ እና ክትትል አለመተዉን" ይገልጻል።
ታካሚዎች በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው እንደሚያዝንም ድርጅቱ አስታውቋል።
ክሬይን፣ ላውራ እና ኒኪታ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ያወጡት ጥቂት ገንዘብ ነው። ነገር ግን ከባድ የጤና እክል ገጥሟቸዋል።
የዐይን ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ኮሊን እንደሚለው፤ ከሕክምናው በኋላ ባሉት ቀናት ታካሚዎች የቅርብ ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል።
በአነስተኛ ገንዘብ ሕክምና የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎታቸው አስተማማኝ እንዳልሆነም ያስጠነቅቃል።
ኒኪታ ቀዶ ሕክምና ባደረገች በሳምንቱ ቲክቶክ ላይ የተጫኑ ቪድዮዎች እያየች ዐይኗ ላይ ያለውን ስፌት ፈትታለች።
"የሆነ ነገር ከቆዳዬ የማላቅቅ ነው የመሰለኝ፤ ሕመሙ ያደክማል" ትላለች።
ፌስላንድ ታካሚዎቹ እንዴት ስፌቱን ማላቀቅ እንደሚችሉ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ቢገልጽም ኒኪታ ግን ምንም መረጃ እንዳልተሰጣት ትናገራለች።
የዐይን ቀዶ ሕክምና ባለሙያው "ታካሚዎች ስፌቱን በራሳቸው መንገድ ሲያነሱ ጉዳት ያስከትላል" ይላል።
ያለ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ወይም ነርስ ስፌትን መፍታት ለኢንፌክሽ የሚያጋልጥ ሲሆን ቁስሉ ጠባሳ ጥሎም ሊያልፍ ይችላል።
ኒኪታ ገንዘብ ቢኖራት እና ቲክቶክ ላይ የሰማችውን ሁሉ ባትቀበል ኖሮ ይሄ ሁሉ እንግልት እንዳማይገጥማት ትናገራለች።
ክሬይን ቀዶ ሕክምናውን ካደረገች ሁለት ዓመት ቢያልፋትም አሁንም ድረስ የዐይን ብዥታ ያስቸግራታል።
ላውራ ደግሞ ዐይኗ ላይ ያለው ጠባሳ እስከወዲያኛው አብሯት እንደሚኖር ትሰጋለች።
"ችግር ሳይኖርብኝ መፍትሔ መፈለግ አልነበረብኝም። የባሰ ችግር ይዤ ነው የተመለስኩት። ያመጣሁትን ችግር ለማስተካከል ቀዶ ሕክምና ቢያስፈልገኝም ገንዘቡ የለኝም።"




































